የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 7ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 7ኛ ሳምንት 16 ጨዋቻዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተከናውነዋል። እኛም በዚህ መልኩ ጠቅለል አድርገን አቅርበነዋል።

ምድብ ሀ

(አምሀ ተስፋዬ)

ጥር 15 (አርብ) መቐለ ላይ ደደቢት ከገላን ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳዎቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የደደቢትን ሁለቱንም የድል ጎሎች ማስቆጠር የቻለው ክብሮም አስመላሽ ነው።

አዲስ አበባ መድን ሜዳ ላይ አቃቂ ቃሊቲ የምድቡን መሪ ለገጣፎ ለገዳዲን አስተናግዶ 2-1 ሽንፈት አጋጥሞታል። የገጣፎ ለገዳዲን የድል ጎሎች አንዋር ያሲን እና ዘካሪያስ ከበደ ሲያስቆጥሩ ለአቃቂ ከመሸነፍ ያላዳናቸውን ግብ አብዱልቃድር ናስር አስቆጥሯል።

በምድቡ ዛሬ የተደረጉት ሌሎች ጠዋታዎች ማለትም ፌዴራል ፖሊስ ከ ሰሎዳ ዓድዋ፣ ወልዲያ ከ ደሴ ከተማ እንዲሁም ኤሌክትሪክ ከሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ወሎ ኮምበልቻ ከ አክሱም ከተማ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል።


ምድብ ለ

(አምሀ ተስፋዬ)

የምድቡ መሪ ነቀምቴ ከተማ እና ተከታዩ ሻሸመኔ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ወለጋ ስታዲየም ላይ ተከናውኖ ነቀምቴ 3-0 አሸንፏል። የነቀምቴን ጎሎች ኢብሳ በፍቃዱ በ11ኛው ደቂቃ፣ ውብሸት ሥዩም በ29ኛው ደቂቃ እንዲሁም ደረጄ ፍሬው በ75ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል።

ሱልልታ ላይ ያያ ቪሌጅ እየተሻሻለ የመጣው አዲስ አበባ ከተማ ሀምበሪቾን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል። ረጅም ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠርበት በዘለቀው የሁለቱ ጨዋታ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ተክሉ ተስፋዬ የአዲስ አበባን የማሸነፊያ ግብ አስቆጥሯል።

አዲስ አበባ መድን ሜዳ ላይ ኢኮሥኮን ከካፋ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል። ጨዋታው ያለምንም ሊጠናቀቅ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ አብዱልለጢፍ ሙራድ አስቆጥሮ ኢኮሥኮን ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ አድርጓል።

ሀላባ ላይ ሀላባ ከ ቤንች ማጂ ቡና ያደረጉትን ጨዋታ በርበሬዋቹ 2-1 አሸንፈዋል። አቡሽ ደርቤ በ55ኛው እና 73ኛው ደቂቃ የሀላባእ ጎሎች ሲያስቆጥር ቤንች ማጂን ከሽንፈት ያላዳነ ግብ ተዘራ ጌታቸው አስቆጥሯል ።

ጅማ ላይ ጅማ አባቡና ወላይታ ሶዶን አስተናግዶ በአቡበከር ኸይረዲን እና ፉአድ ተማም ጒሎች 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ለወላይታ ሶዶ በረከት ወንድሙ አስቆጥሯል።

አዲስ አበባ ላይ መከላካያ በሜዳው ከጋሞ ጨንቻ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። ለመከላከያ ዘነበ ከበደ ሲያስቆጥር ዘላለም የእንግዶቹን ጎል አስቆጥሯል።


ምድብ ሐ

(ቴዎድሮስ ታከለ)

ሀዋሳ ላይ በተከታታይ ድል ርቆት የቆየው ደቡብ ፖሊስ በአጥቂው የኃላሸት ፍቃዱ ሐትሪክ ታግዞ አዲስ አዳጊው ባቱ ከተማን 3ለ1 ረቷል፡፡ ደቡብ ፖሊሶች በአመዛኙ ብልጫ ወስደው በተጫወቱበት በዛሬው መርሐ ግብር ከወትሮ በተለየ በመስመር አጨዋወት ላይ ትኩረት በማድረጋቸው በተሻጋሪ ኳሶች የባቱ ተከላካዮችን ሲረብሹ የታዩ ሲሆን እንግዳው ቡድን በበኩላቸው ከየትኛውም አቅጣጫ ረጃጅም ኳሶች ሲያዘወትሩ ታይተዋል።

ባቱዎች 16ኛው ደቂቃ አቤል ሀብታሙ በቀጥታ መቶ የግቡ ብረት ሲመልስበት ዳግም አምበሉ ክንዳለም ፍቃዱ ቢመታትም ለጥቂት በወጣችበት ሙከራ ጎል ለማግኘች ጥረት ሲያደርጉ ከዚህ ሙከራ በኋላ በይበልጥ በቀኝ በኩል ተሰላፊው ያሬድ መሀመድ አማራጭ ማጥቂያ መስመርን የከፈቱት ቢጫ ለባሾቹ በርካታ አጋጣሚን መፍጠር ችለዋል። ይሁን እና ገና በጊዜ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚዎች ቢያገኙም የያሬድ መሀመድ ብኩን መሆን አግዷቸዋል፡፡ ከኃላሸት ፍቃዱ፣ ብሩክ ኤልያስ እና ጌታሁን አየለ አስቆጪ ሙከራዎች በኃላ 43ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ያሬድ መሀመድ ሲያሻማ ዘነበ ከድር ተቆጣጥሮ ለኃላሸት አመቻችቶለት የኃላሸት ፍቃዱ በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ በኋላ ለመነቃቃት የሞከሩት ባቱዎች በጭማሪ የዕረፍት መውጫ ሰአት አቻ የሆኑበትን ግብ በሚሊዮን ይስማይ አማካኝነት አስቆጥረው 1ለ1 በመሆን ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ወደ ቅብብል ጨዋታ የገቡት ፖሊሶች ገና የዳኛው ፊሽካ እንደተነፋ በኃላሸት ፍቃዱ እና ያሬድ መሀመድ ማስቆጠር የሚችሉበትን ግልፅ ዕድል አግኝተው መጠቀም አልቻሉም፡፡ ሆኖም ያሬድ መሀመድ በሚገርም ሁኔታ ያሻገረለትን የኃላሸት ፍቃዱ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ዳግም መሪ አድርጓቸዋል፡፡ በድጋሚ አሁንም ወደ ባቱ ግብ ክልል ለመድረስ ያልተቸገሩት ደቡብ ፖሊሶች 59ኛው ደቂቃ ላይ ሶስተኛዋን ግብ አግኝተዋል፡፡ ያሬድ መሀመድ በቀኝ በኩል በረጅሙ ወደ ግብ ሲያሻግር ኢኮስኮን ለቆ ደቡብ ፖሊስን የተቀላቀለው አጥቂው የኃላሸት ፍቃዱ በግንባር በመግጨት ለራሱ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ደቡብ ፖሊስም 3ለ1 ማሸነፉን ያረጋገጠበትን ግብ አክሏል፡፡ በተቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ተጠናቋል፡፡


ቡታጅራ ከተማ በሜዳው ኢትዮጵያ መድንን አስተናግዶ 3-0 በማሸነፍ መሪነቱን አስጠብቋል። ለፈረሰኞቹ አዲሱ አሥራት እና ድንቅነህ ከበደ (ሁለት) ግቦቹን አስቆጥረዋል።

አርሲ ነገሌ ላይ ነገሌ አርሲ ከየካ ክፍለ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በነገሌ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የነገሌን የአሸናፊነት ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው አብዱላዚዝ አብደላ ነው።

ሺንሽቾ ላይ ሺንሺቾ ከ ኮልፊ ያደረጉት ጫዋታ በሺንሺቾ 2-1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ወራቤ ላይ ስልጤ ወራቤ ከ ቂርቆስ 2-2 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል። ለወራቤ ከድር ታረቀኝ እንዲሁም በፍፁም ቅጣት ምት ሮባ ዱካሙ ግቦችን አስቆጥረዋል።

ጌዲኦ ዲላ ከ አርባምንጭ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በጌዲኦ የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ