አዳማ ከተማ የከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ ተጫዋቾችን ውል ሊያቋርጥ ነው

አዳማ ከተማ ባጋጠመው የፋይናስ ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ የሆኑት የክለቡ ነባር ተጫዋቾችን ውል ሊያቋርጥ እንደሚችል ተሰምቷል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን በመስራት እና ከታች በሚያሳድጋቸው ወጣት ተጫዋቾች መልካም ስም ያተረፈው አዳማ ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ያጋጠመው የፋይናስ ችግር የክለቡን ቀጣይ ጉዞ እየተፈታተነው ይገኛል። ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት እየተቸገሩ ያሉት የክለቡ የበላይ ጠባቂዎች እንደ መፍትሔ ያስቀመጡት አቅጣጫ የተወሰኑ የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋቾችን ውል በማቋረጥ የተፈጠረው የፋይናስ ቀውስን ማረጋጋት ላይ መሆን እንዳለበት ሰምተናል።

ውላቸው ሊቋረጥ የታሰቡ ተጫዋቾችን ለጊዜው ስማቸውን የማንጠቅስ ቢሆንም በቡድኑ ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ ያገለገሉ ተጫዋቾች እንደሆኑ ታውቋል።

ክለቡ ምንም እንኳን የመፍረስ አደጋ የሚያጋጥመው ባይሆንም በአነስተኛ ደሞዝ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና ከታችኛው ታዳጊ ቡድን ተጫዋቾችን በማሳደግ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በውድድሩ ላይ ለመቆየት ዕቅድ እንዳለው ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ