ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሠረት በማድረግ በሳምንቱ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች ላይ አንፃራዊ ጥሩ አቋም ያሳዩ 11 ተጫዋቾችንም እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው። 

አሰላለፍ፡ 3-5-2


ግብ ጠባቂ

ሚኬል ሳማኬ (ፋሲል ከነማ) 

የፋሲል ከነማው ግብ ጠባቂ ባለፈው ሳምንት የፈፀመው ስሕተት ቡድኑን ዋጋ ቢያስከፍለውም በዚህ ሳምንት ቡድኑ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ ጥሩ ብቃቱን ማሳየት ችሏል። በተለይ በመልሶ ማጥቃት ጎል ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት አዲስ እና ሀብታሙ ያደረጓቸውን ሙከራዎች በማክሸፍ ጥሩ ቀን ያሳለፈ ሲሆን በሳምንቱ ከታዩ ሌሎች ግብ ጠባቂዎች አንፃራዊ ጥሩ ብቃት በማሳየቱ በምርጥ 11 ለመጀመርያ ጊዜ ሊካተት ችሏል።

ተከላካዮች

መሐመድ ዐወል (ወልቂጤ ከተማ)

ግዙፉ ጋናዊ ተከላካይ ቡድኑ ወደ ድል በተመለሰበት የትላንቱ ጨዋታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በሦስት ተከላካዮች ጥምረት የቀረበው የወልቂጤን የመከላከል አደረጃጀት ከመምራት ባለፈ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች በነበረው የበላይነት ቡድኑ በጨዋታው መረቡን ሳያስደፍር እንዲወጣ አድርጓል። በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥም ለመጀመርያ ጊዜ መካተት ችሏል።


ኤድዊን ፍሬምፖንግ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዘንድሮ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ጋናዊው ተከላካይ በአስደናቂ ፍጥነት ላይ የተመረኮዘውን የባህር ዳር ከተማ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴን በማቋረጥ ረገድ ውጤታማ ነበር። በጨዋታው ላይ ግዙፉ የባህር ዳር ከተማ አጥቂ ማማዱ ሲዲቤን (በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ) ከተቀረው ቡድን እንዲነጠል በማድረጉ ረገድ ምርጥ ብቃቱን አሳይቷል። በምርጥ ቡድን ውስጥ ተጠባባቂነት ሁለት የተለያዩ ሳምንታት ላይ የገባው ኤድዊን በምርጥ 11 ሲካተት የመጀመርያው ነው።


ፈቱዲን ጀማል (ኢትዮጵያ ቡና)

በዚህ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ወደ መቐለ አምርቶ ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ሲጋራ ጥሩ ብቃት ያሳየው ፈቱዲን ጀማል ጥሩ ሳምንት ካሳለፉት የመሐል ተከላካዮች አንዱ ነው። በቡድኑ አጨዋወት ወሳኝ ሚና ካላቸው ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀሰው ፈቱዲን በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በርካታ በሊጋችን ብዙም ያልተለመዱ የተሳኩ ሸርተቴዎችም አድርጓል። በግሉ እና ከአጣማሪው ወንድሜነህ ደረጀ የነበረው ብቃት እና ጥሩ መናበብም በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ እንዲገባ አስችሎታል።

አማካዮች

ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)

በመጀመርያዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ከራቀ በኃላ በዘጠነኛው ሳምንት ወደ ጅማ ተጉዘው ጅማ አባጅፋርን መርታት በቻሉበት ጨዋታ ከጉዳቱ አገግሞ ከተሰለፈ በኃላ ለክለቡ ውጤታማነት ጉልህ ተሳትፎን ማድረግ ጀምሯል፡፡ ተጫዋቹ በዚህኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ በሜዳው መቐለን ሲረታ በጨዋታው ላይ በርካታ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ከመፍጠሩ በዘለለ አሸናፊ የሆኑበትንም ብቸኛ ግብ ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን ሙሉ ሦስት ነጥብ እንዲጨብጥ ማድረግም ችሏል፡፡ ይህም በምርጥ 11 ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ እንዲካተት አስችሎታል።


አዲስ ህንፃ (አዳማ ከተማ)

አዲስ አዳማ ከተከታታይ ጨተታዎች በኋላ ወደ ድል እንዲመለስ ጥሩ አበርክቶ ከነበራቸው ተጫዋቾች አንዱ ነበር። ልምዱን ተጠቅሞ የቡድኑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከመምራት ጀምሮ ቡድኑ ጫና ውስጥ በሚገባበት ሰዓት በማረጋጋት ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ወሳኝ ሚና መጫወት ችሏል። በሳምንቱ ምርጥ 11 ውስጥም ለመጀመርያ ጊዜ መካተት ችሏል።


አለልኝ አዘነ (ሀዋሳ ከተማ)

ምንም እንኳን ቡድኑ ቢሸነፍም ወደ ግራ በተለጠጠ አቋቋም ላይ በሚገኘው መስፍን ታፈሰ ፍጥነት ላይ የተመሰረተውን የቡድኑ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በመምራት ረገድ ጎልህ አስተዋጽኦ ነበረው። የማጥቃት እንቅስቃሴውን ከማሳለጥ በዘለለ የቡድኑን የኳስ ስርጭት የሚመራበትና የተመጠኑ ረጃጅም ኳሶቹ እጅግ ድንቅ ነበሩ። በዚህ ሳምንት ያሳየው አንቅስቃሴም በምርጥ 11 ለመጀመርያ ጊዜ እንዲካተት አስችሎታል።


እድሪስ ሰዒድ (ወላይታ ድቻ)

በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተጫወተ ቢሆንም በእስካሁን ቆይታው እያሳየ የሚገኘው መልካም እንቅስቃሴ ለሊጉ አዲስ መሆኑን ያስረሳነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን መካተት የቻለው ተጫዋቹ ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን በዚህ ሳምንት በሜዳው ሲያስመዘግብ በርካታ የጎል አጋጣሚነት የተቀየሩ ኳሶችን ወደፊት ከማሻገር ጀምሮ የማጥቃት እንቅስቃሴውን በሚገባ መርቷል። የጨዋታዋ ብቸኛ ጎል የተገኘችውም ከማዕዘን ምት ባሻማት ኳስ መነሻነት ነበር።


ጋዲሳ መብራቴ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ዘንድሮ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎች እያሳየ የሚገኘው ጋዲሳ ከወትሮው በተለየ የታታሪነት ደረጃ ላይ ይገኛል። በትላንቱ ጨዋታ ጊዮርጊሶች የተሻለ በተንቀሳቀሱበት የቀኝ መስመር በኩል በተደጋጋሚ ለወጣቱ ተከላካይ ሳሙኤል ተስፋዬ ፈተና ሲጋርጥበት ውሏል። ምንም እንኳን በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ወደ ጎልነት መቀየር ባይችሉም የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

አጥቂዎች

ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ)

በሒደት ወደ ድንቅ አጥቂነት የተቀየረው ሙጂብ በዚህ ሳምንትም ጎል በማስቆጠር ተከታዮቹን መራቅ ችሏል። ተጫዋቹ ጎሏን ያስቆጠረበት መንገድ ድንቅ የነበረ ሲሆን ከቡድኑ የማጥቃት ተጫዋቾች ጋር የነበረው መናበብ መልካም የሚባል ነበር። በጨዋታው ላይም ተጨማሪ ጎሎች ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርግ የዋለው ሙጂብ በሳምንቱ ምርጥ 11 ለሦስተኛ ጊዜ መካተት ችሏል።


ዳዋ ሆቴሳ (አዳማ ከተማ)

ከቡድኑ በተቃራኒው በገረሉ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ዳዋ ሆቴሳ በዚህ ሳምንት አዳማ በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕናን 2-0 እንዲረታ ትልቁን ድርሻ መወጣት ችሏል። አጥቂው የመጀመርያውን ጎል ሲያስቆጥር አሸናፊነታቸውን ያረጋገጠች ጎል ደግሞ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ከጎሎቹ ባሻገር በጨዋታ እንቅስቃሴ ባሳየው አቋምም የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ መካተት ችሏል።

ተጠባባቂዎች

ዳንኤል አጃይ (ሰበታ ከተማ)

ሰለሞን ወዴሳ (ባህር ዳር ከተማ)

ፍቅረሚካኤል ዓለሙ (ባህር ዳር ከተማ)

ኤልያስ መሐመድ (ጅማ አባ ጅፋር)

ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

እዮብ ዓለማየሁ (ወላይታ ድቻ)

ሳዲቅ ሴቾ (ወልቂጤ ከተማ)