ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፩) | ክለብ ትኩረት

በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ የ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪው መቐለ 70 እንደርታ ሽንፈትን ሲያስተናግድ ተከታዩ ፋሲል ከነማ በሜዳው አሁንም በአልቀመስ ባይነቱ ቀጥሏል፤ በወራጅ ቀጠናው ወልቂጤ ድል ሲያደርግ ሆሳዕና ተሸንፏል። በጥቅሉ በ10ኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር ላይ ትኩረት ሳቢ የሆኑ ክለብ ነክ ጉዳዮች በተከታዩ መልኩ ቀርበዋል።


👉 መቐለ 70 እንደርታ እና አማኑኤል

ከሰሞኑ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ይገኙ የነበሩት የዐምናው የሊጉ አሸናፊዎች ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኃላ በዚህ ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ ወደ ወላይታ ሶዶ አምርተው ሽንፈትን አስተናግደዋል።

ከፍተኛ የነጥብ መቀራረቦች የተለመዱ በሆኑበት የሀገራችን የሊግ ውድድሮች መቐለ አሁንም በቅርብ ርቀት እየተከተሉ ከሚገኙት ፋሲል (18) እና ቅዱስ ጊዮርጊስ (17) በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ ሊጉን በ19 ነጥብ እና በአራት የጎል ልዩነቶች እየመራ ይገኛል።

ያለ ወሳኝ አጥቂያቸው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ወደ ሶዶ ያመሩት መቐለዎች በድቻ የ1ለ0 ሽንፈት ያስተናገዱበት ይህ ጨዋታ 10 ሳምንት ባስቆጠረው የዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ማስቆጠር ያልቻሉበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል። ቡድኑ ዘንድሮ ባሳካቸው የሜዳ ውጪ ድሎች ላይ የአማኑኤል ሚና ከፍተኛ እንደመሆኑ የአጥቂው አለመኖር ምዓም አናብስቱ ላይ ክፍተት እንደፈጠረ እሙን ነው።

ምንም እንኳን ገና በአንድ ጨዋታ የመቐለን ጉዳይ ማንሳት ከባድ ቢሆንም የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በአማኑኤል ላይ የተገነባ በመሆኑ የተጫዋቹ አለመኖር ክፍተት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ቡድኑ በጨዋታዎች ላይ እንደቡድን በሚቸገርበት እና ጎል በሚያስፈልግበት ሁሉ ወሳኝ ጎሎችን የሚያስቆጥረው አጥቂያቸውን ግልጋሎት በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ማግኘት አስፈላጊ ነው።


👉 የባህር ዳር ከተማ አደገኛ መልሶ ማጥቃት  እና ተስፋ ሰጪው የመሐል ተከላካዮች ጥምረት

ምንም እንኳን በዚህ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1ለ0 ሽንፈት ቢያስተናግዱም በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻልን እያሳየ የሚገኝ የተጠና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን እያስመለከተን ይገኛል።

አስደናቂ ብቃት ላይ በሚገኘውና ከማሊያዊው አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ጀርባ በነፃነት በሚንቀሳቀሰው ፍፁም ዓለሙ የሚመራው የባህር ዳር ከተማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በሁለቱ ፈጣን የመስመር አማካዮች ግርማ ዲሳሳ እና ዜናው ፈረደ ፍጥነት በመታገዝ ተጋጣሚዎች በማጥቃት ሽግግር ወቅት የሚከፈቱትን የሜዳ ክፍሎች ለመጠቀም የሚሞክሩበት መንገድ ትኩረት የሚስብ ነው።

ባለፉት ሳምንታት ቡድኑ ብዙ ግቦችን ቢያስቆጥርም በተቃራኒው በርካታ ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል። ለዚህም እንደ አጠቃላይ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ችግር የጎላ ቢሆንም በተለይ ከፍጥነት ጋር ጥያቄ ይነሳበት ለነበረው የመሐል ተከላካዮች ጥምረት መልካም ነበር የእሁዱ የሄኖክ አቻምየለህና ሰለሞን ወዴሳ ጥምረት ጥሩ ተስፋ የሚሰጥ ነበር። በተለይ ከተከላካይ ጀርባ ባሉ ክፍት ቦታዎች ላይ እንደልባቸው መሮጥ የሚችሉት የጊዮርጊስ አጥቂዎችን እንቅስቃሴ በማቆም ረገድ ስኬታማ ነበሩ። ምንም እንኳን በሀይደር ሸረፋ የግል ብቃት የታገዘች ግብ ቢያስተናግዱም አሰልጣኝ ፋሲል ጥልቀትን ማጥቃት ተቀዳሚ አማራጫቸው ካደረጉ ቡድኖች ጋር የትላንቱን ጥምረት እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ እንቅስቃሴን መመልከት ችለናል።


👉 ያለ አሰልጣኝ ልምምድ ሲሰሩ የሰነበቱት አዳማዎች ድል

ከደሞዝ ጋር በተፈጠረ ውጥንቅጥ ያለፉትን ቀናት ያለ አሰልጣኝ በተናጥል ልምምድ ሲሰሩ የሰነበቱት አዳማ ከተማዎች ሀዲያ ሆሳዕናን 2-0 በመርታት ያልተጠበቀ ድልን ተቀዳጅተዋል። እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ጨዋታውን ያደረጉት የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ዳዋ ሆቴሳ በመጀመሪያው እንዲሁም ፉአድ ፈረጃ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ግቦች ድል ማድረግ ችለዋል።

ቡድኖች በችግር ውስጥ መገኘታቸውን ለውጤታማነት በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ ሲያስተናግዱ መመልከት የተለመደ ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች (ብዙዎች በካልቺዮ ፖሊ ቅሌት መሐል የዓለም ዋንጫን ያነሳው የጣልያን ብሔራዊ ቡድን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ) አሰልጣኞች የሚፈጠሩ ችግሮችን እንደ መነሳሻ ሲጠቀሙባቸው በአመዛኝ አጋጣሚዎች ግን የሚከሰቱ ችግሮች አሉታዊ ጥላቸውን ሲያጠሉ ይስተዋላል። በዚህ መሐል የአዳማ ከተማ ሰሞነኛ ውጥንቅጥ እንደ ቡድን ልምምድ ከማድረግና ለጨዋታ ከመዘጋጀት ቢያግደውም ቡድኑ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በጥሩ ተነሳሽነት ተጫውቷል።

ከአዳማ ከተማ ድል ጋር በተያያዘ ብዙ የስፖርት ቤተሰቦችን ሲያነጋግር የነበረው ሌላው ጉዳይ ያለ በቂ ዝግጅት ጨዋታ አድርጎ በድል መወጣቱ ከሊጉ ድክመት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚያሳይ እንደሆነ ለመግለፅ አስገድዷቸዋል። መዘጋጀትም ሆነ እንደነገሩ ሆኖ ወደ ሜዳ መግባት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ያለው ለውጥ እምብዛም ነው ለሚሉም ጥሩ መከራከሪያ ሆኖላቸዋል። (ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ጅማ አባ ጅፋር ልምምድ ሳያደርግ ወደ አዳማ ተጉዞ ከአዳማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ተመልክተናል።)


👉 ወልቂጤ ከተማ

ተስፋ ሰጪን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በውጤት ማጀብ ተስኗቸው የሰነበቱት ወልቂጤ ከተማዎች በዚህኛው ሳምንት በሜዳቸው ድሬዳዋ ከተማን አስተናግደው በሳዲቅ ሴቾ ብቸኛ የመጀመሪያ አጋማሽ ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ጠንካራ የመከላከል መስመር እንዳለው ቁጥሮች የሚመሰክሩለት ቡድኑ አሁንም ቢሆን ተስፋ ሰጪ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በጎሎች ማጀብ የሚችሉ ከሆነ በመጀመሪያው ዓመት የሊጉ ቆይታቸው የተሻለን ነገር ማስመስገብ የሚችሉ ይመስላል።

ከአምስት ጨዋታዎች በኃላ ከተገኘው በዚህም ድል ወልቂጤዎች ነጥባቸውን ወደ 11 ከፍ በማድረግ ወደ ከበላያቸው ከሚገኘው ጅማ አባጅፋር ጋር በነጥብ ተስተካክለው በግብ ክፍያ ተበልጠው 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።


*የሆሳዕና ተጫዋቾች 

ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉት ሆሳዕናዎች በዲሲፕሊን ጉዳይ ርዕሰ ዜና ሲሆኑ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከዚህ ቀደም በፋሲል ከተማ በሰፊ የጎል ልዩነት በተሸነፉበት ጨዋታ በተመሳሳይ 8 የቡድኑ አባላት ቢጫ ካርድ የመመልከታቸው ጉዳይ እንዲሁ መነጋገርያ የነበረ ክስተት መሆኑ ይታወሳል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሩትና በውዝግቦች በተጀበው በዚሁ ጨዋታ ላይ እንዲሁ የሀዲያ ሆሳዕና ተጫዋቾች እንዲሁም ደጋፊዎች ጨዋታው በመሩት ዳኞች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል። ይህም ሒደት በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት አንድ የሆሳዕና ደጋፊ በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ ሆስፒታል እስከማምራት የደረሰ ጉዳትን አስከትሏል።

በዳኞች የተወሰነ ውሳኔ ሊለወጥበት በማይችልበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እንደመገኘታችን ከልክ ያለፉ ተቃውሞዎች የስታዲየሞችን ፀጥታ ከማደፍረስ በዘለለ ለደጋፊዎች ጉዳት መንስኤ ስለሚሆኑ ሁሉም አካላት በሀላፊነት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል።

ውጤት ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚገኙት የሆሳዕና ተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ተበድለናል በሚል መንፈስ የተጫዋቾችን የመጫወት ፍላጎት በአሉታዊ መልኩ ከመጉዳት ይልቅ ካሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እስከመጨረሻው የዳኛው ፊሽካ ድረስ ታግሎ ውጤት ለመቀልበስ መታተሩ የተሻለው መንገድ ስለመሆኑ ተገንዝበው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።


👉ወልዋሎ በሜዳው?

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንታት በተሻለ መነቃቃት ነጥቦችን በመሰብሰብ ሊጉን እየመሩ የሰነበቱት ወልዋሎዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሜዳቸው ነጥብ ለማስመዝገብ እየተቸገሩ ይገኛል።

በእርግጥ ቡድኑ ካለፈው ዓመት መጀመርያ ጀምሮ ከከተማው ርቆ ጨዋታውን እያደረገ መገኘቱ በራሱ በሜዳው ማግኘት የሚገባውነ ነጥብ እንዳያገኝ እንዳገደው የማይካድ ነው። ሆኖም በቡድኑ አጥቂዎች ፍጥነት ላይ የተገደበው የቡድኑ የማጥቃት አማራጭ ባለሜዳ ሆነው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በሊጉ እንደተለመደው ተጋጣሚዎች ከሜዳቸው ውጭ ሲጫወቱ ጥንቃቄን መርጠው ወደ ሜዳ በመግባት በአብዛኛው የቡድናቸውን ተጫዋቾች በራሳቸው ሜዳ ክፍል ጠቅጠቅ ባለ ርቀት በመደርደር የቡድኑ አጥቂዎች የሚፈልጉትን በቂ የመሮጫ ቦታዎች ስለማያገኙ ቡድኑ በጣም ሲቸገር ይስተዋላል።

ቡድኑ የቀደመው የጨዋታ እቅዳቸው እክል ሲገጥመው ተግባራዊ ሊያደርገው የሚችላቸው አማራጭ የማጥቂያ መንገዶች ስለሌሉትም እየተቸገረ ይገኛል። ይህም በዚህ ሳምንት ከሌሎች እንግዳ ቡድኖች የተለየ አቀራረብ ከነበራቸው ቡናዎች ጋር ባደረጉት ጨዋታ ታይቷል።

በአንፃሩ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ከባለሜዳው ቡድን አንፃር ሁለተኛ የማሸነፍ ግምትን ይዞ ወደ ሜዳ ስለሚገባና በተመሳሳይ ባለሜዳው ቡድን ጨዋታውን ለማሸነፍ ማጥቃት ላይ በሚያተኩሩበት ወቅት በሚገኙ ክፍተቶች በፈጣን አጥቂዎቻቸው ብቃት ጨዋታዎችን ሲወስኑ እየተስተዋለ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ