ወደ ሳውዲ አረቢያው አል አንዋር ካመራ ሁለት ሳምንታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ስፍራ ተጫዋች ጋቶች ፓኖም ክለቡ ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወደ አሸናፊነት በተመለሰበት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ተጫዋቹ የግብፁ ክለብ አራስ ኤል ሁዳድን በመልቀቅ ወደ ሳውዲ አረቢያ ዲቪዥን ሁለት (ሦስተኛ የሊግ እርከን) ክለብ አል-አንዋር በጃንዋሪ ወር አጋማሽ ላይ ካመራ ወዲህ ሁለት ጨዋታዎችን ለክለቡ ማድረግ ችሏል። በምድብ ለ የሚገኘው ክለቡ በ11ኛ ሳምንት በሜዳው አል ድራይ ሽንፈት ሲያስተናግድ በአሰላለፍ ውስጥ ተካቶ በአዲሱ ክለቡ መለያ የመጀመርያ ጨዋታውን ያደረገ ሲሆን ለ62 ደቂቃዎችም መጫወት ችሏል። በጨዋታውም የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል።
በዚህ ሳምንት ክለቡ ከሜዳው ውጪ ከአል-ካይስማ ክለብ ጋር ባደረገው የ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ቡድኑም 2-1 አሸንፎ መመለስ ችሏል። ይህ ድል ጥሩ ጉዞ ላይ ላልነበረው አል-አንዋር ከአምስት ተከታታይ ጨዋታ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘ ድል ነበር።
በቀጣይ ዓርብ በ13ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ በሜዳው አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አል አራቢን የሚገጥመው አል አንዋር በሁለት ምድቦች ተከፍሎ እየተካሄደ በሚገኘው የሳውዲ ዲቪዥን ሁለት ከ12 ጨዋታ 12 ነጥቦች ሰብስቦ በ9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሊጉ ከየምድቡ አንደኛ የሚወጡት በቀጥታ ወደ ዲቪዥን አንድ ሲያድጉ ሁለተኛ የሚወጡት ደግሞ መለያ ጨዋታ አድርገው አሸናፊው ቡድን የሚያድግ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ግዙፉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ቡናማዎቹን ከለቀቀ በኋላ ወደ ሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ አምርቶ ብዙም ቆይታን ሳያደርግ ወደ ሀገር ውስጥ ተመልሶ በመቐለ 70 እንደርታ ስድስት ወራትን ከቆየ በኋላ በግብፆቹ ኤል ጎውና እና ሀራስ ኤል ሁዳድ መጫወት ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ