ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፪) | ተጫዋች ትኩረት

በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የባህር ዳር ከተማው ግብጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ ከጨዋታው መጀመር በፊት በቀይ ካርድ በመሰናበቱ እንዲሁም የጌታነህ ከበደ ድርጊት ትኩረት ስበዋል። ተጫዋቾች ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሱበት እና ጉዳት ያስተናገዱበት ሳምንትም ሆኖ አልፏል። በዚህኛው ሳምንት ጨዋታዎች ትኩረት ሳቢ የነበሩ የተጫዋቾች ጉዳይም እንደሚከተለው ቀርቧል።


👉 የሀሪስተን ሄሱ አስገራሚ ክስተት

የባህር ዳር ከተማው ተቀዳሚ ተመራጭ ግብ ጠባቂ ቤኒናዊው ሀሪስተን ሄሱ በዚህ ሳምንት ቡድኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈበት ጨዋታ መጀመር ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቀጥታ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።

የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች ልምምዳቸውን አጠናቀው ወደ መጫወቻ ሜዳ ለመግባት እየተጠባበቁ የነበሩት የሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች መሀል የነበረው ሀሪስተን ጨዋታውን በመሩት ኢንተናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ከለበሰው መለያ ስር ያደረገው ትጥቅ ከተጋጣሚው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ቁምጣ ቀለም ጋር ስለሚመሳሰል እንዲያወልቅ በነገሩት ወቅት በነበረው የቃላት ልውውጥ ደስተኛ ያልነበሩት አርቢትሩ ተጫዋቹ ወደ ሜዳ ሳይገባ እዛው ኮሪደር ላይ በቀጥታ ቀይ ካርድ እንዲወገድ አድርገውታል። ይህም ያልተለመደ አጋጣሚ ሲሆን በምትኩም ፅዮን መርዕድ ግቡን የመጠበቅ ተልዕኮ ተሰጥቶት ወደ ሜዳ ሊገባ ችሏል።

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሁለት ግብ ጠባቂዎች ከ90 ደቂቃው ውጪ ቀይ ካርዶች ተመልክተዋል። ጊኒያዊው የወልዋሎ ግብ ጠባቂ አብዱላዚዝ ኬይታ በመቐለ ከተሸነፉበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ ከዳኛው (በላይ ታደሰ) ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ የቀይ ካርድ ሲመለከት ትላንት ደግሞ ሀሪስን ሄሱ ከጨዋታው መጀመር ቀደም ብሎ ተወግዷል።

የሀገራችን ተጫዋቾች እና የዳኞች ግንኙነት ለዓመታት በአሉታዊ ጎኑ የሚነሳ እና ደጋፊዎውን ለሁከት የሚያነሳሳ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን አሁን አሁን የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ከዳኞች ጋር የሚፈጥሩት ሰጣ ገባ እየጎላ መምጣት ጀምሯል።


👉 ደጉ ደበበ እና መስፍን ታፈሰ

ዐምና የውድድር ዓመቱ ከሀዋሳ ተስፋ ቡድን አድጎ አስደናቂ ጊዜ ከሀዋሳ ጋር ያሳለፈው መስፍን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ሲሶ ጉዞ ውስጥ ከአሁኑ ሁለተኛ ጊዜ ጉዳት አጋጥሞታል። በሰበታ ከተማ 2-1 በተሸነፉበት የቅዳሜው ጨዋታ ለቡድኑ ከባዶ መሸነፍ ያዳነችውን ግብ በ81ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው መስፍን በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ራሱን ስቶ ወደ ሆስፒታል ለተጨማሪ እርዳታ ሊያመራ ችሏል። የተጫዋቹ ወሳኝነት ክለቡ የጉዳቱን መጠን እና የማገገምያ ጊዜ በትኩረት እንዲመለከት የሚያደርግ ነው።
እንደ መስፍን ሁሉ በተመሳሳይ ወቅት ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው አንጋፋው ደጉ ደበበም በዚህ ሳምንት መቐለን በረቱበት ጨዋታ ጉዳት አስተናግዷል። በመደበኛነት እየተጫወተ የሚገኘው የቡድኑ አምበል ጉዳት የከፋ ከሆነ እምብዛም አስተማማኝ አማሳጭ በሌለው የወላይታ ድቻ የኋኃየላ ክፍል ጥንካሬ ላይ ያለው ተፅዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።


👉 የጌታነህ ከበደ ተቃውሞ 

በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህር ዳርን ባሸነፈበት ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ አሰልጣኙ ላይ ተቃውሞውን በአደባባይ አሳይቷል።
በ57ኛው ደቂቃ ሀይደር ላስቆጠራት ግብ ኳሷን አመቻችቶ ያቀበለው ምንተስኖት አዳነ ከግቧ መቆጠር በፊት አሰልጣኝ ሰርጂዮ ተጫዋቹን በመስመር አጥቂው አሜ መሐመድ ለመቀየር ዝግጅታቸውን አጠናቀው በመጠባበቅ ከግቧ መቆጠር በኋላ ቅያሬው እንዲቀጥል ቢያዙም በጌታነህ ተቃውሞ ቅያሬው መዘግየቱ የሳምንቱ ትኩረት ሳቢ ገጠመኝ ነበር።

ጌታነህ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የሚያሳያቸው ተግባራት የመወያያ ርዕስ ሲሆኑ ይስተዋላል። ተጫዋቹ በሀገሪቱ ስም ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ መሆኑ በቀላሉ ትኩረት ውስጥ መግባቱ የሚጠበቅ ሲሆን ድርጊቶቹ የስፖርት ቤተሰቡን ለሁለት ሲከፍል ይስተዋላል። ገሚሶቹ በአሉታዊ ጎኑ የተጫዋቹን ድርጊቶች ከሥነ-ምግባር ጉድለት ጋር ሲያያይዙት ገሚሶቹ ደግሞ በአዎንታዊ ጎኑ በከፍተኛ ስሜት እና የማሸነፍ ፍላጎት ከመጫወት የሚመጣ ስሜታዊነት ነው ይላሉ። እርስዎስ ከየትኛው ወገን ነዎት?


👉 የተመስገን ካስትሮ እና አንተነህ ተስፋዬ መመለስ

ዐምና አርባምንጭን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመራውና በሊጉ ጨዋታ ከአስቻለው ግርማ ጋር ተጋጭቶ ጉዳት እስካስተናገደበት የጅማ አባጅፋር ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ክስተት የነበረው ሁለገቡ ተከላካይ ተመስገን ካስትሮ ከአንድ ዓመት በኃላ በኢትዮጵያ ቡና የቡድን ስብስብ ውስጥ መካተት ችሏል። ረዘም ላለ ጊዜ በጉልበት ጉዳት ከሜዳ ርቆ የሰነበተው ተመስገን ኢትዮጵያ ቡና ከወልዋሎ ጋር በትግራይ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ ጨዋታውን አሳልፏል። ከረጅም ጊዜ ጉዳት እንደመመለሱ በሂደት የጨዋታ ዝግጁነት ሲያገኝ በቅርቡ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ አይቮሪኮስትን ባሸነፈችበት ጨዋታ ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ ከድሬዳዋ ከተማ ሰበታን ከተቀላቀለ ወዲህ አዲሱን ክለቡን በይፋዊ ጨዋታ ማገልገል ያልቻለው አንተነህ ተስፋዬም በተመሳሳይ በዚህ ሳምንት ወደ ሜዳ ተመልሷል። የመስመር ተከላካያቸውን ጌቱ ኃይለማርያምን ወደ ተጠባባቂ ወንበር ያወረዱት ሰበታዎች ዩጋንዳዊው ተከላካያቸው ሳቪዮ ካቩጎን ረዘም ባለ ጊዜ ጉዳት ከማጣታቸው ጋር ተዳምሮ የአንተነህ መመለስ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሀዋሳን በረቱበት ጨዋታ በ79ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ዘውገን በመተካት ወደ ሜዳ የገባው አንተነህ ተስፋዬ በቀጣይ ለአሰልጣኝ ውበቱ ተከላካይ መስመር ላይ አማራጫቸውን ያሰፋል ተብሎ ይጠበቃል።


👉 ሀይደር ሸረፋ 

በክረምቱ መቐለን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው አማካዩ ሀይደር ቡድኑ ባህር ዳር ከተማን ሲረታ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በ57ኛው ደቂቃ ከምንተስኖት አዳነ የተሻገረለትን ኳስ እንደመጣች በግሩም አጨራረስ ለአዲሱ ክለቡ የመጀመሪያ ግቡን በማራኪ መልኩ ማስቆጠር ችሏል።

የተረጋጋው አማካይ ጎል ማስቆጠር ጊዮርጊስ ከሌሎች አማራጮች ጎል ማግኘት መጀመሩጅ ያሳየ ይመስላል።  (ባለፈው ሳምንትም ምንተስኖት አዳነ አስቆጥሯል) ይህም በአጥቂዎቹ ላይ ብቻ የተንጠለጠለው የጎል ማስቆጠር ሸክምን በሒደት ለመቅረፍ እንደመነሳሻ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።


👉 ያለ ጃኮ አራፋት የተሻለው ወልቂጤ 

በዚህኛው ሳምንት ቡድኑን ላለፉት 9 ጨዋታዎች በፊት አጥቂነት ሲመራ የነበረውና 1 ጎል ብቻ ያስቆጠረው ጃኮ አራፋት እና ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህን ከስብስብ ውጭ ያደረጉት ወልቂጤ ከተማዎች ድሬዳዋን ማሸነፍ ችለዋል።

በትንላቱ ጨዋታ ላይ ከተለመደው 4-3-3 ወጣ ባለ አደራደር በ3-5-2 የገቡት ወልቂጤዎች በፊት መስመር ላይ ሳዲቅ ሴቾ፣ አህመድ ሁሴንን አጣምረው የተሻለ ስኬት አግኝተውበታል። በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ ሴቾ ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ በሊጉ ባስቆጠራት የመጀመሪያ ግብም ማሸነፍ ችለዋል።

በ2009 ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት ፕሪምየር ሊጉን የተዋወቀው ጃኮ ባለፉት ዓመታት ከወልቂጤ በፊት በወላይታ ድቻና ባህር ዳር ከተማ ያልተሳኩ ቆይታዎችን ማድረግ ችሏል። የመጫወት ፍላጎት ችግር እንዳለበት የሚስተዋለው አጥቂዎች በጨዋታዎች የተሻለ የግብ እድል ለሚፈጥረው ቡድኑ በሚፈለገው ልክ ግብ ማምረት እየቻለ አይገኝም።


👉 ቸርነት ጉግሳ

በቅርቡ ከረጅም ጊዜ ጉዳት የተመለሰው ቸርነት ጉግሳ ቡድኑ መቐለን በረታበት የቅዳሜው ጨዋታ ወሳኛ የማሸነፍያ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከአሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ስንብት በኋላ በጊዜያዊ አሰልጣኝ ደሳለኝ ደቻሳ የመሰለፍ እድል እያገኘ የሚገኘው ቸርነት ጉግሳ የቀደመ ብቃቱን መልሶ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በቅዳሜው ጨዋታም በጥሩ ትጋት በመንቀሳቀስ የጎል አጋጣሚዎችን ሲፈጥር ውሏል።

©ሶከር ኢትዮጵያ