ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፫) | አሰልጣኞች ትኩረት 

በ10ኛው ሳምንት ከአሰልጣኞች አንፃር እምብዛም የተከሰቱ ጉዳዮች ባይኖሩም በአስተያየቶቻቸው ላይ አተኩረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።


👉 የተረጋጋው ፋሲል ተካልኝ 

የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒው በአሰልጣኝነት የገጠመው ፋሲል ከጨዋታው ጅማሮ በፊት ግብ ጠባቂያቸው ሀሪሰን ሄሱን በቀጥታ ቀይ ካርድ ባጡበት ወቅት በመልበሻ ቤት አካባቢ በገዛ ተጫዋቾቹና የአሰልጣኝ አባላት ላይ ተፈጥሮ የነበረውን የስሜት ግለት ለማብረድ የሄዱበት ርቀት እንዲሁም በተደጋጋሚ በዳኞች ይወሰኑ የነበሩ ውሳኔዎች ይቃወሙ የነበሩ የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በመገሰፅ ያረጋጉበት የነበረው መንገድ አድናቆት የሚቸረው ጉዳይ ነው።
ከውጤት ማጣት መልስ ጥቃቅን ጉዳዮችን በመንተራስ ለሽንፈቶች መደበቂያ ፍለጋ በውጪያዊ አካላት ማላከክ በተለመደበት ሀገር የትላንቱ የፋሲል ተካልኝ ሁኔታ እና በጨዋታው ላይ ያተኮረ ድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ትምህርት ሊሆን የሚገባ ነው።

👉 የስምዖን ዓባይ ምሬት 

ወደ ወልቂጤ የተጓዙት ድሬዳዋ ከተማዎች በወልቂጤ 1-0 ከተሸነፉበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የድሬዳዋው አሰልጣኝ ምቹ ያልሆነው የወልቂጤ ሜዳ ያቀዱትን ስትራቴጂ ለመተግበር እክል እንደሆነባቸው በዚህ መልኩ ተናግረዋል
” በ90 ደቂቃ ጨዋታ ውስጥ ብዙ ነገሮች አሉ። ከዛ ውስጥ የኛን ቡድን እንቅስቃሴ ለመተግበር መቻል አንዱ ነው። ነገር ግን እዚህ ሜዳ ላይ ለመተግበር ከባድ ነው። ሜዳው አመቺ አይደለም። ምክንያት ስትሰጥ መሸነፍህን ለመሸፈን ይመስላል። ቢሆንም ግን እኛ ይዘን የመጣነውን የጨዋታ ፍልስፍና ለመተግበር ተጫዋቾቼ የተቻላቸውን ቢያደርጉም ከብዶናል።”

👉 ጫናዎች እየበረከቱባቸው የሚገኙት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ በደጋፊዎች እየደረሰባቸው ስለሚገኘው ጫና ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል

“ይህ የተለመደ ነው፤ የትኛውም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመጣ አሰልጣኝ ጫናዎች አሉበት። ምክንያቱም ደጋፊዎቹ ቡድኑ ሁሌም ጨዋታዎች እንዲያሸንፍና ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ነገርግን ደጋፊው መረዳት የሚኖርበት ዋንጫ ለማንሳት ሁሌ መንገዶች ቀላል አይሆኑም። እያሸነፍንም ቢሆን በጨዋታዎች ላይ ደጋፊዎች ከቡድኑ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችን እየፈለጉ ደስተኛ ባይሆኑ እኔ ብዙ ግድ አይሰጠኝም። አሁን ላይ ሁሉም በክለቡ ዙርያ ያሉ አካላት ደስተኛ መሆን ያለባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም ከመሪው መቐለ በሁለት ነጥቦች ርቀን 17 ነጥብ መያዝ ችለናል። ዋናው ነገር ጎሎችን እያስቆጠርን ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻላችን ነው።”

👉 የተቋረጠው የአዳማው ድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልስ

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተፈጠረ ፀጥታ ችግር ምክንያት የአዳማው ም/አሰልጣኝ ደጉ ዱባም ድህረ ጨዋታ አስተያየታቸውን መጨረስ ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በነበራቸው አጭር ቆይታ ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል ቡድኑ ሙሉ ትኩረቱ ሜዳ ላይ ቢሆን ጠንካራ ቡድን ይሆናል የሚል ነበር።

“ልጆቹ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆነው ክለቡን በመውደድ እና ህዝቡን በማክበር  ላደረጉት ነገር ሊመሰገኑ ይገባል። ምንም ጥያቄ የለውም ለተጫዋቾቹ ደሞዝ አለመከፈሉ ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ አድርጓል። እስካሁን ወደ አስራ አምስት ቀናት እንደ ቡድን ተሰባስበን ልምምድ መስራት አልቻልንም። ቡድኑ ውስጥ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጀምሮ እስከ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች ጭምር የያዘ ነው። ይህ ቡድን ደሞዝ ቢከፈለው ነገሮች ቢስተካከሉለት ኖሮ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት የሚችል አቅም ነበረው።”

👉 ካሳዬ አራጌ ከሜዳ ውጭ ድል ማስመዝገብ ስለተሳነው ኢትዮጵያ ቡና

“ጉዞ ለሁሉም ነው። ከአዲስ አበባ ወጥቶ ነጥብ ማግኘት ለሁሉም ቡድን አስቸጋሪ እንደነበር ነው የምሰማው። አሁን ቡና ላይ ለምን በተለየ መንገድ እንደሚታይ አልገባኝም። ለምን ቡና ላይ የተለየ ነገር እንደሚጠበቅ አልገባኝም። ሁሉም ቡድን ላይ እንደዛ ነገር ስላለ ማለቴ ነው። ከሜዳ ውጭ ነጥብ ጥለው የሚመለሱት እንደዚ የሚጠየቁ ከሆነም ጥያቄው የጋራ ስለሆነ እኔም መመለስ ይኖርብኛል። አንድ ቡድን የሚጫወተው በሜዳው ነው ብለህ ለባለ ሜዳው አሳልፈህ የምትሰጠው ነገር አለ። ይህንን አስተሳሰብ ከኛ ተጫዋቾች ማስወገድ አለብን። ግን በተለየ መልኩ ቡና ላይ መታየት የለበትም።”

👉 አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ስለሚዋዥቀው የቡድናቸው የሜዳ ላይ ብቃት 

“ይሄ የሁሉም ቡድኖች ችግር ነው። አንደኛው በአስራ ስድስተኛው ይሸነፋል። አንደኛው በሌላኛው ይሸነፋል። ይሄ ለእግር ኳሱ ጥሩ ነው። አንዱ ዝም ብሎ ከወጣ ደጋፊም አይመጣም። ሌላው አብዛኞቻችን በየዓመቱ አዲስ ቡድን ነው ምንገነባው። ስለዚህ ወጥነትን ለመፍጠር ጊዜ የለም። ከአምናው ኬይታን ብቻ ነው ያስቀጠልነው። በዝግጅት ሌሎች ቡድኖችን እኛ ቀድመናቸው ነበር፤ የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎች አሸነፍን። ከዛ ሌላው ደሞ እየተሻሻለ እና እየተነቃቃ መጣ። ይሄን መጥላት አይገባም ምክንያቱም ብያንስ ከአንድ እስከ ዘጠነኛ ያለው በአንድ ቀን ጨዋታ ደረጃው የሚለዋወጥ ነው።”

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ