የፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን እነሆ

👉 ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአስረኛ ሳምንት በአጠቃላይ 13 ጎሎች ተቆጥረዋል። ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ጎሎች በብዛት ሲቆጠሩበት የነበረው ሊግ በዚህ ሳምንት ጥቂት ጎሎች አስተናግዷል። ከአንደኛው ሳምንት ጋር በጋራ ዝቅተኛ ጎል የተስተናገደበት ሆኖም አልፏል።

– በዚህ ሳምንት የጎሎች መጠን መቀነስ ቢያሳይም እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጎሎች ተቆጥረዋል።

– በዚህ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ብዛት አምስት ሆኗል። በዚህ ሳምንት ጎል ያላስቆጠሩት አምስቱም ቡድኖች የተጫወቱት ከሜዳቸው ውጪ ነው።

– በዚህ ሳምንት 13 ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። በዚህም ሁሉም ጎሎች በተለያዩ ተጫዋቾች መቆጠር ችሏል።

– ከተቆጠሩት 13 ጎሎች መካከል 8 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 2 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥሯል። 1 ጎል ደግሞ ከተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች ተገኝቷል።

– ከ13 ጎሎች መካከል 10 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ 1 ጎል ከቀጥታ ቅጣተ ምት፣ ሁለት ጎሎች ከማዕዘን ምት ተሻምተው የተገኙ ናቸው።

– ከዚህ ሳምንት 13 ጎሎች መካከል አንድ ብቻ በግንባር ተገጭቶ ሲቆጠር ቀሪዎቹ በሙሉ በእግር ተመትተው ተቆጥረዋል።

– ከ13 ጎሎች መካከል 10 ጎሎች ሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 3 ጎል ከሳጥን ውጪ ተመትቶ ጎል ሆኗል።

– በዚህ ሳምንት ምንም የፍፁም ቅጣት ምት አልተሰጠም።


👉 ካርዶች

– ባህር ዳር ከተማ ላይ ሁለት ቀይ ካርዶች የተመዘዙ ሲሆን ይህም ሊጉ ከተጀመረ ወዲህ ከአንድ ቡድን ከፍተኛው የቀይ ካርድ መጠን ነው።

– በዚህ ሳምንት ወልዋሎ ምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከተ ብቸኛው ቡድን ሲሆን አዳማ ከተማ ከፍተኛውን የማስጠንቀቂያ ካርድ (4) የተመለከተ ቡድን ሆኗል።

👉ዳዋ ሆቴሳ

– በዚህ ሳምንት በጎሎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ በቀዳሚነት የተቀመጠው ዳዋ ሆቴሳ ነው። ተጫዋቹ አንድ ጎል አስቆጥሮ ለአንዱ በማመቻቸት ከሌሎቹ ልቆ ተገኝቷል።

👉 መቐለ 70 እንደርታ

– በሊጉ ሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጎል እያስቆጠረ ሲወጣ የቆየው መቐለ 70 እንደርታ በዚህ ሳምንት በወላይታ ድቻ መሸነፉን ተከትሎ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ጎል ሳያስቆጥር ወጥቷል። በአጠቃላይ ደግሞ ሰኔ 11 ከኢትዮጵያ ቡና ያለ ጎል አቻ ከወጣ ከ14 ጨዋታዎች በኋላ ነው ጎል ሳያስቆጥር ሊወጣ የቻለው።

👉ፋሲል ከነማ

– ዐፄዎቹ በሜዳቸው አይበገሬ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። ይህን በቁጥር ስናስደግፈውም እውነታውን ያጠናክርልናል። ቡድኑ ያለፉትን 10 ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎች በሙሉ በድል ሲያጠናቅቅ 22 ጨዋታዎች ያለሽንፈት መጓዝ ችሏል።

👉ስሑል ሽረ

– በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ድል አስመዝግበው የነበሩት ስሑል ሽረዎች በዚህ ሳምንት አቻ ተለያይተዋል። ከአራት ጨዋታዎች በኋላም ለመጀመርያ ጊዜ መረባቸውን አስደፍረዋል። በተቃራኒው ለ7ኛ ተከታታይ ጨዋታ ሽንፈት ባለማስተናገድ በጥሩ ጉዞ ቀጥለዋል።

👉 ወልዋሎ

– ቢጫ ለባሾቹ ባለፉት አራት ተከታታይ የሜዳቸው ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ ሳይችሉ ቀርተዋል። ከቡና ጋር አቻ የተለያዩበት የእሁዱን ጨዋታ ጨምሮ በሦስቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ተሸንፈዋል።

👉 ደለለኝ ደቻሳ እና ወላይታ ድቻ

– ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ስንብት በኋላ ቡድኑን በጊዜያዊነት የተረከበው አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ በሁለቱም ጨዋታዎች ድል አስመዝግቧል። አሰልጣኙ ከመጣ ወዲህ በሁለት ጨዋታ ብቻ ያሳካው ነጥብ (6) በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ስር በ8 ጨዋታ ካስመዘገበው ጋር ከወዲሁ እኩል መሆን ችሏል።

– አሰልጣኝ ደለለኝ በወላይታ ድቻ 100% የአሸናፊነት ሪከርድ ይዞ ቀጥሏል። አምና በጊዜያዊነት የመራውን አንድ ጨዋታ ጨምሮ በሦስት ጨዋታ ሦስት ድል ማስመዝገብ ችሏል።

👉ሰበታ ከተማ

– የሜዳዎቹን ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እያደረገ የሚገኘው ሰበታ ከተማ በቅርብ ጨዋታዎች በመደበኛነት ነጥብ እየሰበሰበበት ይገኛል። በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በአጠቃላይ በተከታታይ 5 ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም።

👉ወልቂጤ ከተማ

– ወልቂጤ ከተማ በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ማሸነፉን ተከትሎ ወልቂጤ ላይ በታሪኩ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ድል አሳክቷል። በተጨማሪም የዚህ ሳምንት ድሉ ከአራት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘ ነው።

👉አዳማ ከተማ

– በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ የሚገኘው አዳማ ከተማ በዚህ ሳምንት ከተከታታይ ሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ተገናኝቷል። በተጨማሪም ግንቦት 18 ቀን 2011 ደደቢትን 4-0 ከረታ ከ13 ጨዋታዎች በኋላ በጨዋታ ከአንድ በላይ ጎል አስቆጥሮ ሲያሸንፍ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

👉በዚህ ሳምንት…

– ኢትዮጵያ ቡና ከሜዳው ውጪ ለ7ኛ ተከታታይ ጨዋታ ያለ ድል ሲመለስ ባህር ዳር ከተማ ሦስተኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ሦስተኛ ተከታታይ የሜዳ ድሉን አሳክቷል።

– በዚህ ሳምንት ስድስት ተጫዋቾች ዘንድሮ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ከጎል ጋር ተገናኝተዋል። ሳዲቅ ሴቾ (ወልቂጤ)፣ ፉአድ ፈረጃ (አዳማ ከተማ)፣ አዲስ ተስፋዬ (ሰበታ ከተማ)፣ ኤልያስ አሕመድ (ጅማ አባ ጅፋር)፣ ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ) እና ሐይደር ሸረፋ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ለመጀመርያ ጊዜ ከጎል ጋር የተገናኙ ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በሶከር ኢትዮጵያ የሚወጡትን ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች በቀጥታም ሆነ በግብዓትነት ሲጠቀሙ ምንጭ ይጥቀሱ።