ሰበታ ከተማዎች ከአንድ ተጫዋቻቸው ጋር ሊለያዩ ነው

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሰበታ ከተማን ተቀላቅሎ የነበረው የተከላካይ መስመር ተጫዋች በስምምነት ክለቡን ሊለቅ ተቃርቧል።

ቡድኑን ሊለቅ የተቃረበው ተጨዋች ሳቪዮ ካቩጎ ነው። በኮንጎ ኤስ ሲ ቪታ ሲጫወት ቆይቶ የነበረው ተጨዋቹ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሰበታ ከተማን መቀላቀሉ ይታወሳል። ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ውድድር ላይ በመሰለፍ ጥሩ ግልጋሎት አበርክቷል። ነገር ግን ተጨዋቹ አቋሙ ቀስ በቀስ እየወረደ በመምጣቱ እና ተደጋጋሚ ጉዳቶችን በማስተናገዱ ቡድኑን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መጥቀም ሳይችል ቀርቷል። የቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ወሳኙ የተከላካይ መስመር ተጨዋቻቸው አንተነህ ተስፋዬ ከጉዳቱ እያገገመላቸው በመምጣቱ ሳቪዮ ካቩጎን ለመልቀቅ ወስነዋል ተብሏል።

የ26 ዓመቱ ተጨዋች ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት የሚገኙ ክለቦች ከመጫወቱ ባሻገር ለሃገሩ ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጥሩ ግልጋሎትን ሰጥቷል። በተለይም ቡድኑ ለ2014 የአፍራካ ዋንጫ ሲያልፍ ወሳኝ ከነበሩ ተጫዋቾች አንዱ ነበር።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ