በ11ኛ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች በደጋፊዎች ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የሸገር ደርቢን ተከታዩ ዳሰሳችን ይመለከተዋል።
በሁለት የተለያዩ የጨዋታ አስተሳሰብ ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች በነገው ዕለት 10 ሰአት ሲል በጉጉት በሚጠበቀው የሸገር ደርቢ ይገናኛሉ። የጨዋታው ውጤት በሁለቱ ክለቦች ቀጣይ ጉዞ ላይ ከሚኖረው አስተዋጽኦ አንፃር ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ከ10 ጨዋታዎች 13 ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ ወገብ ላይ ሲገኝ በአንፃሩ ተጋጣሚያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከመሪው መቀለ በ2 ነጥብ አንሶ በ17 ነጥብን በመያዝ በ3ኛ ደረጃ ላይ ሆነው ነው የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉት።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፉት ሦስት ተከታታይ የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታዎች ማሸነፋቸው የነገውንም ጨዋታ በተሻለ የማሸነፍ ተነሳሽነት ውስጥ ሆኖ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይታመናል። በአንፃሩ ቅድስ ጊዮርጊሶችም በተመሳሳይ የመጨረሻ ሶስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ቢችሉም ጨዋታዎችን እያሸነፉበት የሚገኘው መንገድ ለደጋፊዎቻቸው የሚዋጥ አልሆነም። ይህም በተወሰነ መልኩ በነገው ጨዋታ ላይ ጫና ውስጥ ሊከታቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል።
ጨዋታው በተለይ ከደጋፊዎችና ከተወሰኑ የቡድኑ ተጫዋቾች ተቃውሞ እየገጠማቸው የሚገኙት የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ሰርጂዮ ልጆች የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው የሚያደርጉት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተቃራኒው ከጨዋታ ጨዋታ እያሳዩ በሚገኙት መሻሻል በደጋፊዎች ዘንድ ቅቡልነቱ እየጨመረ የመጣው ኢትዮጵያ ቡናዎችም ከጨዋታው ድልን አጥብቀው መፈለጋቸው እንደሁልጊዜው ሁሉ በሁለቱም በኩል ውጥረት የነገሰበት የሜዳ ላይ ፍልሚያ ተታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች ምንም እንኳን በቅርቡ ከተገናኙበት የ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ መጠነኛ የተጫዋቾች እንዲሁም የአጨዋወት ለውጥ ቢያደርጉም ጨዋታው ለነገው ጨዋታ ይዘውት ስለሚገቡት የጨዋታ ዕቅድ ግን ጠቋሚ ምልክቶችን የሚሰጥ ጨዋታ ነበር።
የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | አሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደ ግዴታ በሚመለከቱት ኳስን ከራስ የግብ ክልል ለመመስረት በሚያደርጉት ጥረት በሲቲ ካፑ ጨዋታ እንደተመለከትነው ምንም እንኳን አጨዋወቱ ከሚፈልገው የአካል ብቃት ደረጃ አንፃር በሙሉ ጨዋታው ወቅት መዝለቅ ባይችልም በman oriented high press የቡና ተጫዋቾች ጫና ውስጥ በመክተት የምስረታ ሂደታቸውን ፈታኝ ያደረጉባቸውና በጨዋታው ለተቆጠሩት ሁለቱ የማሸነፊያ ግቦች መገኛ የነበረው ሂደቶች ነገም ይደገማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በተወሰኑ መልኩ የኳስ ምስረታቸው ላይ መሻሻሎች እያሳዩ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሶችን የማቀበያ አማራጮችን ፈልገው በፍጥነት የማይወጡ ከሆነና እንደከዚህ ቀደሙ የመሀል ተከላካዮቹ በጥልቀት ወደ ኋላ በተሳበ አቋቋም አደገኛ ቅብብሎችን የሚያደርጉ ከሆነና በተለይ ያልጎለበተው የዓለምአንተ በጫና ውስጥ ሆኖ ፈጣን ውሳኔዎች የመስጠት አቅም በፈጣኖቹ አቤል ያለው እና ጋዲሳ ታታሪነት አደጋ ሊጋብዙ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ነው።
በአንፃሩ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ የሆነውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የመከላከል አደረጃጀት ለማስከፈት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች የሜዳውን ስፋት በመጠቀምና በተለይ ከሁለቱ 8 ቁጥሮቻቸው በመስመሮች መካከል በመገኘት ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች አቅርቦት ላይ ይበልጥ ጠንክረው መቅረብ ይኖርባቸዋል።
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር በአዲስ አስተሳሰብ እየተቃኘ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በእንቅስቃሴ ደረጃ በሒደት መሻሻሎችን እያሳየ ሲገኝ በተደጋጋሚ የኳስ ንኪኪዎች አልፎ አልፎም በረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ ጥረቶች ሲያደርጉና ስኬታማ ሲሆኑም መመልከት ችለናል። በተጨማሪም በቅርብ ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው ጎሎች በአጨዋወቱ ከሚጠበቁ ጎሎች በተቃራኒው መሆናቸው (ከቅጣት ምት፣ ከርቀት የተቆጠረ፣ ከማዕዘን ምት) ሌላ አዎንታዊ ነጥብ ነው።
በአሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ የሚመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በሜዳቸውም ሆነ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ለጥንቃቄ የሚሰጡት የተጋነነ ዋጋ በቡድኑ ደጋፊዎች እምብዛም አልተወደደላቸውም። ቡድኑ በክረምቱ ለዘመናት የነበረበትን የመሐል ሜዳ የፈጠራ ችግር ይቀርፋሉ ተብሎ የታመኑ ተጫዋቾች ቢያስፈርምም አሰልጣኙ እስካሁን በአግባቡ ሲጠቀሙባቸው እየተስተዋለ አይደለም። አሰልጣኙ ለመከላከል ሚና ከሚሰጡት ትኩረት የተነሳ ከአንድ በላይ የማጥቃት ባህሪ ያለው የመሐል አማካይ በጨዋታዎች ለመጠቀም ሲደፍሩ አይስተዋልም። ይልቁንም በእሁዱ የባህር ዳር ጨዋታ እንደተመለከትነው ምንም እንኳን የአጨዋወት ልዩነት ቢኖራቸውም በጨዋታው ተመሳሳይ ሚና ሲወጡ የተመለከትናቸው ምንተስኖት አዳነ እና ሙሉዓለም መስፍንን ሲጠቀሙ መስተዋሉ እንዲውም በመስመሮች ብቻ የተገደበውን ተገማች የማጥቂያ አማራጭ ላይ አሁንም ቡድን የተንጠለጠለ እንዲሆን እየተገደደ ነው።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | አቻ | አሸነፈ |
ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ መልኩ በጨዋታዎች ላይ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ የመቅረብ ነገር ከሰሞኑ እያስተዋልንባቸው እንገኛለን። በዚህም የተነሳ የነገው ጨዋታን ውጤት በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ የተሻለው ቡድን የበላይ ሆኖ ያጠናቅቃል የሚል ግምት ማስቀመጥ አስፈላጊ የሚሆነው።
ከቡድን ዜና ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ቡና አቤል ከበደን በቅጣት አቡበከር ናስርን በጉዳት የማያሰልፍ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ሳለሀዲን ሰዒድ እና ለዓለም ብርሀኑ አሁንም ጉዳት ላይ በመሆናቸው አይሰለፉም። ናትናኤል ዘለቀ እና አቤል እንዳለ ወደ ልምምድ ቢመለሱም መሰለፋቸው ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ ያብስራ ተስፋዬ ደግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 40 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጨዋታ ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጵያ ቡና 6 ድል አሳክቷል። በ16 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የሸገር ደርቢ ምንም እንኳ አሁን አሁን ያለ ግብ የሚጠናቀቅባቸው ጨዋታዎች በርከት ቢሉም ባለፉት 40 ግንኙነቶች 73 ጎሎች ተቆጥረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 49፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 24 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
ተ/ማርያም ሻንቆ
አህመድ ረሺድ – ወንድሜነህ ደረጀ- ፈቱዲን ጀማል- እያሱ ታምሩ
ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – ዓለምአንተ ካሳ – አማኑኤል ዮሐንስ
ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – ሀብታሙ ታደሰ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ፓትሪክ ማታሲ
ደስታ ደሙ – አስቻለው ታመነ- ፍሬምፓንግ ሜንሱ- ሄኖክ አዱኛ
ሀይደር ሸረፋ – ሙሉዓለም መስፍን – ምንተስኖት አዳነ
ጋዲሳ መብራቴ – ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው
© ሶከር ኢትዮጵያ