ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

በድሬዳዋ ስታዲየም የሚደረገውን የድሬዳዋ ከተማ እና የሰበታ ከተማን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ካሉበት የስጋት ወረዳ ፈቀቅ ለማለት እና ከሁለት ሳምንት በፊት በሜዳቸው አዳማ ከተማ ላይ የተቀዳጁትን ድል ለመድገም ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በአሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ የሚሰለጥነው ቡድኑ በየሳምንቱ የማይገመት ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። እርግጥ ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ብዙም የተሻሻሉ ነገሮች ባይኖሩትም በሊጉ ጅማሮ የደረሰበትን ሁለት ተከታታይ ሽንፈት በማረም ጨዋታዎችን እያደረገ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ከሜዳ ላይ ጨዋታዎቹ ነጥቦችን ይዞ ለመውጣት የሚጥረው ቡድኑ ነገም ለሰበታ ከተማ ፈታኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ተጋጣሚው ሰበታ ከተማ ከሚከተለው ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት ፍላጎት አንፃር እና የመሐል ሜዳው የበላይነት እንዳይወሰድበት ከመስጋት የተነሳ ቡድኑ በነገው ጨዋታ የአማካይ መስመር ተጨዋቾችን በቁጥር አብዝቶ እንደሚጠቀም ይገመታል። የአማካይ መስመር ተጨዋቾቹ ለመሃል ሜዳው ብልጫ ብቻ ሳይሆን አስተማማኝ ላልሆነው የተከላካይ ክፍል ሽፋን ለመስጠት ስለሚጠቅሙ አሰልጣኙ አማራጩን እንደሚጠቀሙ ይታሰባል።

በሊጉ ከፍተኛ ግብ ካስተናገዱ ክለቦች መካከል ግምባር ቀደሙ የሆኑት ድሬዳዋዎች(19) ያላቸው የላላ የተከላካይ መስመር ራስ ምታት ሆኖባቸው ጨዋታዎችን ማድረግ ቀጥለዋል። በተለይ ቡድኑ ፈጣን እና የሜዳውን መስመር ይዘው የሚጫወቱ የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች ሲያገኙት ችግሮች ውስጥ ሲገባ ይስተዋላል። በነገውም ጨዋታ የሰበታ የመስመር ተጨዋቾች ይህንን ያልተደራጀውን የቡድኑን የኋላ መስመር በመፈተን ግቦችን ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ይገመታል።

ቡድኑ ያሬድ ታደሰን ከጉዳት መልስ ለነገው ጨዋታ ሲያገኝ ለረጅም ጊዜ ጉዳት ያስተናገዱት ምንያህል ተሾመ እና ረመዳን ናስር አሁንም ባለማገገማቸው ከስብስቡ ውጪ ሆነዋል።

የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

በተከታታይ ሦስት የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎችን ድል ያስመዘገቡት ሰበታ ከተማዎች ያላቸውን የሜዳቸው ላይ ጥንካሬ ከሜዳ ውጪ ለመድገም ወደ ምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል አምርተዋል።

በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ደረጃ እየተሻሻለ የመጣው ሰበታ ከተማ ከሜዳው ውጪ የሚገጥመውን ፈተና ለማለፍ እየተቸገረ ይገኛል። እርግጥ ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት ዋነኛ የጨዋታ አላማው ኳስን መቆጣጠር እንደሆነ ቢታይም አልፎ አልፎ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ግቦችን ለማስቆጠር ይጥራል። በነገውም ጨዋታ ቡድኑ ይህንን ዋነኛ አላማውን በሜዳ ላይ ለመተግበር እንደሚታትር ይገመታል። ነገር ግን ቡድኑ ኳስን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ፈተናዎች ከገጠሙት የመስመር ላይ ጥቃቶችን እና በዘንድሮ የውድድር ዓመት በጥሩ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ፍፁም ገ/ማርያምን ኢላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች በመጠቀም በጎ ነገሮችን ለራሱ ሊያመጣ እንደሚችል ይታሰባል።

በነገው ጨዋታ የሰበታ የመስመር ተጨዋቾች ሜዳውን በመለጠጥ ተጋጣሚን ለማስጨነቅ የሚያደርጉት ጥረት ይጠበቃል። በተለይ ወደ መስመር እየወጡ ወደ ሳጥን የሚያሻግሩት ኳስ ለድሬዳዋዎች ስጋት እንዳይጭር ያስፈራል። ከዚህ በተጨማሪ የመሐል ሜዳ ተጨዋቾቹ የሚልኩትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ድሬዳዋዎች በአግባቡ ካልመከቱት አደጋ ውስጥ ሊገቡ ይችላል።

ምንም እንኳን ቡድኑ በየጨዋታው ተሻሽሎ ለመቅረብ ቢሞክርም ከሜዳ ውጪ ያለው ድክመት በነገው ጨዋታ ዋጋ እንዳያስከፍለው ያሰጋል። ከዚህ በተጨማሪ ወደ መሐል ሜዳ ተጠግቶ የሚከላከለው የተከላካይ ክፍሉ ለድሬዳዋ ከተማ የመልሶ ማጥቃት እጅ እንዳይሰጥ እና ግቦችን አስተናግዶ ችግር ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ጨዋታ የዳዊት እስጢፋኖስ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ አስቻለው ግርማ እና ሳቪዮ ካቩጎን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ6 አጋጣሚዎች ተገናኝተው ድሬዳዋ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሰበታ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎ በድል ተወጥቷል፡፡

– በስድስቱ ግንኙነታቸው ድሬዳዋ 4 ጎሎች ሲያስቆጥር ሰበታ 5 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ፍሬዘር ካሣ – ዘሪሁን አንሼቦ – በረከት ሳሙኤል – አማረ በቀለ

ፍሬድ ሙሸንዲ – ዋለልኝ ገብሬ

ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሙህዲን ሙሳ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል አጃይ

ኢብራሂም ከድር – አዲስ ተስፋዬ – ወ/ይፍራው ጌታሁን – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ

ታደለ መንገሻ – መስዑድ መሐመድ – እንዳለ ዘውገ

ናትናኤል ጋንቹላ – ፍፁም ገ/ማርያም – ባኑ ዲያዋራ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ