መቐለ 70 እንደርታ ትግራይ ስታዲየም ስሑል ሽረን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ከተከታታይ ድሎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ሽንፈት የገጠማቸው የሊጉ መሪ መቐለዎች ከሽንፈት ማግስት ስሑል ሽረን በሚገጥሙበት ጨዋታ በመሪነት ለመቆየት ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።
የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
በሜዳቸው ባደረጓቸው ጨዋታዎች በቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወት ውጤታማ የማጥቃት ጥምረት የሰሩት መቐለዎች በነገው ጨዋታም የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ስሑል ሽረ እንደባለፉት ጨዋታዎች የተከላካይ መስመሩ ወደ መሐል ሜዳ አስጠግቶ መጫወት ምርጫው አድርጎ ከገባ መቐለዎች ወደ ቀደምት ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች የሚመለሱበት ዕድል የሰፋ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች የመስመር ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ ላይ ይበልጥ እንዲሳተፉ ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በዚህ ጨዋታ በተጋጣሚያቸው ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ ላለመጋለጥ የመስመር ተከላካዮቹ እንቅስቃሴ መገደባቸው አይቀሬ ነው።
ምዓም አናብስት በነገው ጨዋታ ሚካኤል ደስታ እና ሥዩም ተስፋዬን በገዳት አያሰልፉም። ግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። በአንፃሩ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከጉዳት ተመልሶላቸዋል። በዚህም ባለፉት ጨዋታዎች በመስመር አጥቂነት ተቀይሮ እየገባ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ተስፈኛው አሸናፊ ሀፍቱ ወደ መስመር ተከላካይነት ተመልሶ ጨዋታውን በቋሚነት ይጀምራል ተብሎ ይገመታል።
የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ | አቻ |
እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ከተከታታይ ድሎች በኋላ በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር ነጥብ የጣሉት ስሑል ሽረዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል ከቅርብ ተፎካካርያቸው ነጥብ መውሰድ የግድ ይላቸዋል።
በተከታታይ ጨዋታዎች መልሶ ማጥቃትን መርጠው አስፈሪ ጥምረት የፈጠሩት ሽረዎች በተከላካይ ክፍላቸው ላይ የቅርፅ ለውጥ ከማድረግ የዘለለ ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም። በዚህም አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ የመቐለን ቀጥተኛ ኳሶች ለመከላከል በሜዳቸው ውጭ እንደተከተሉት አጨዋወት አብዛኛው ጊዜውን ከራሱ ግብ ክልል የማይነቅል እና ክፍተት የማይሰጥ አቀራረብ ይዘው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተጠቀሰው አጨዋወት ወሳኝ የሜዳ ውጭ ነጥቦች ይዘው የተመለሱት ሽረዎች በነገው ጨዋታ በሁለቱ ፈጣን የመስመር ተጫዋቾችን መሰረት ባደረገ የመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎች ለመፍጠር አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ አክሊሉ ዋለልኝን በጉዳት ምንተስኖት አሎን ለሙከራ ወደ ቱርክ በማቅናቱ ምክንያት የሁለቱን ተጫዋቾች ግልጋሎት አያገኙም። ረመዳን የሱፍ በዚህ ጨዋታ የመሰለፉ ነገርም አጠራጣሪ ነው።
እርስ በርስ ግንኙነት
ቡድኖቹ በፕሪምየር ሊጉ ሁለት ጊዜ (ዐምና) ተገናኝተው የመጀመርያው በሽረ የተካሄደው ጨዋታ ያለ ጎል ባዶ ለባዶ ሲለያዩ ሁለተኛውን መቐለ 3-1 አሸንፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)
ፊሊፕ ኦቮኖ
አሸናፊ ሀፍቱ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አሌክስ ተሰማ – አንተነህ ገብረክርስቶስ
ዮናስ ገረመው – ዳንኤል ደምሴ – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ያሬድ ከበደ
ኦኪኪ ኦፎላቢ – አማኑኤል ገብረሚካኤል
ስሑል ሽረ (4-2-3-1)
ወንድወሰን አሸናፊ
ዓወት ገብረሚካኤል – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ሸዊት ዮሐንስ
ነፃነት ገብረመድኅን – ሀብታሙ ሽዋለም
ዲዲዬ ለብሪ – ያስር ሙገርዋ – አብዱለጢፍ መሐመድ
ሳሊፍ ፎፋና
© ሶከር ኢትዮጵያ