በ11ኛ ሳምንት ከሚደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብሮች መካከል ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው ፋሲል ከነማን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
በ3 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማግኘት ያልቻሉት ጅማ አባ ጅፋሮች በ7ኛ ሳምንት ያስመዘገቡትን ሦስት ነጥብ (ወልቂጤ ከተማን 1-0) በደጋፊያቸው ፊት ለመድገም እና ከፊታቸው ከተደቀነውን የወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ 3 ነጥብን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።
የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | አቻ |
ባለፉት ሳምንታት በወጣ ገባ አቋም ጨዋታዎቻቸውን እያደረጉ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች በሁለቱ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ማግኘት የቻሉት አንድ ነጥብ ብቻ በመሆኑ በነገው ጨዋታ ነጥብ ማስመዝገብ የግድ ይላቸዋል። እርግጥ ቡድኑ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ሲከተል ባይስተዋልም የመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን በፍጥነት በማስጀመር ተጋጣሚን ሲፈትን ይታያል። ነገም ቡድኑ በተመሳሳይ አጨዋወት ጎሎችን ለማስቆጠር እንደሚጥር ይገመታል።
የተከላካይ መስመሩ ላይ የሚተማመነው ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ግብ በማስቆጠርም ሆነ የጠሩ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ክፍተቶች ቢታይበትም በሒደት ከአማካይ ተጫዋቾቹ ግብ ማግኘት መጀመሩ ጥሩ ዜና ነው። ለዚህ ደግሞ ቡድኑን በዘንድሮ የውድድር ዓመት የተቀላቀለው ኤሊያስ አህመድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ተጨዋቹ የሚያስጀምራቸው ብሎም የሚያፋጥናቸው የመልሶ ማጥቃት ሂደቶች ቡድኑን እጅጉን ሲጠቅም ስለሚታይ ተጨዋቹ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት የስሑል ሽረን ጠንካራ የመስመር አጨዋወት በመግታት ረገድ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ጅማዎች በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ የተጋጣሚያቸውን የመስመር አቀራረብ ለመግታት ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቡድኑ በኩል ብሩክ ገብረአብ እና ሄኖክ ገምቴሳ በጉዳት መሰለፋቸው አጠራጣሪ ሲሆን ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ወደ ሜዳ ተመልሷል ተብሏል። የወረቀት ጉዳዮች ያላለቁለት ጋናዊው ተከላካይ አሌክስ አሙዙ አሁንም ለጨዋታው አይደርስም፡።
የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | አቻ | አሸነፈ |
በዘንድሮ የውድድር ዓመት አንድም የሜዳ ውጪ ጨዋታውን ያላሸነፈው ፋሲል ከነማ የሜዳ ላይ ጥንካሬውን ከሜዳ ውጪ ለማስቀጠል እና ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመዝለቅ ወደ ጅማ አምርቷል።
በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመራው ቡድኑ ተጋጣሚ ላይ ብዙ ግቦችን (18) በማስቆጠር ከሚጠቀሱ ክለቦች ቀዳሚው ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ተጠቃሽ የሆኑት የቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ፋሲልን ሲጠቅሙት ይታያል። በዋናነት ግን በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር 10ኛ ግቡን በ10ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ሙጂብ ቃሲም ለቡድኑ ጥንካሬ ተጠቃሽ ነው። በነገውም ጨዋታ እነኚህ የቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ፍጥነታቸውን እና ቅልጥፍናቸውን ተጠቅመው የባለሜዳዎቹን ጊዜ ከባድ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።
በተለይ ደግሞ የመስመር ላይ ጥቃቶችን አዘውትረው ለመጠቀም የሚሞክሩት ፋሲሎች ጥቅጥቅ ብሎ የሚጫወተውን የጅማን የተከላካይ መስመር ለመበታተን መፍትሄዎችን ይዘው እንደሚቀርቡ ይገመታል። ቡድኑ ከመስመር ላይ አጨዋወቱ በተጨማሪ ከሱራፌል የሚነሱ እና መሃል ለመሃል የሚደረጉ ጥቃቶችንም ተንተርሶ ግቦችን ሊያስቆጥር ይችላል።
የቡድኑ አምበል ያሬድ ባዬ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ጨዋታዎችን ማድረግ መጀመሩ ለተጋባዦቹ ትልቅ ዜና ነው። ተጨዋቹ የተሰለፈበትን የተከላካይ መስመር ከማደራጀት እና ጥንካሬ ከመስጠት በተጨማሪ ቡድኑን የሚያነሳሳበት እና የኳስ ቅብብሎችን የሚያስጀምርበት መንገድ ልዩ ነው። በተለይ በትኩረት ማነስ ችግር ከሜዳ ውጪ ግቦችን እያስተናገደ ለመጣው ቡድኑ የያሬድ ወደ ጨዋታ መመለስ ትልቅ መፍትሄ ነው።
በፋሲል በኩል ጋብሬል አህመድ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ኦሲ ማውሊ ባጋጠማቸው ጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ተጠቁሟል። ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ሌላ የጉዳት ዜና ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ ርቆ የሰነበተው እንየው ካሳሁን ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ወደ ስፍራው መጓዙ ተገልጿል። ከእንየው በተጨማሪ የቡድኑ የመስመር አጥቂ አብዱራማን ሙባረክም ከጉዳቱ አገግሞ ቀላል ልምምዶችን መስራት ጀምሯል።
እርስ በእርስ ግንኙነት
– በሊጉ 4 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ከነማ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ሁለት ጊዜ አቻ ተለያይተው ጅማ አባ ጅፋር ምንም አላሸነፈም። የዐምናውን የ6-1 ድል ጨምሮ ፋሲል 7 ጎሎችን ሲያስቆጥር ጅማ አንድ ግብ ፋሲል ላይ አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)
ሰዒድ ሀብታሙ
ጀሚል ያቆብ – መላኩ ወልዴ – ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ
ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ
አምረላ ደልታታ – ኤልያስ አህመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ
መሐመድ ያኩቡ
ፋሲል ከነማ (4-3-3)
ሚኬል ሳማኬ
ሰይድ ሀሰን – ያሬድ ባዬ – ከድር ኩሊባሊ – አምሳሉ ጥላሁን
በዛብህ መለዮ – መጣባቸው ሙሉ – ሱራፌል ዳኛቸው
ኢዙ አዙካ – ሙጂብ ቃሲም – ሽመክት ጉግሳ
© ሶከር ኢትዮጵያ