ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ሀዋሳ ከተማ በመነሳሳት ላይ ያለው ወላይታ ድቻን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ወጣ ገባ አቋም እያሳየ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ከሳምንት በፊት በሜዳው ወልቂጤ ላይ ያሳካው ድልን በመድገም ደረጃውን ለማሻሻል አልሞ ወደ ሜዳ ይገባል።

የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ አቻ

 ወጥ የሆነ የተጫዋች ምርጫን ከማይከተሉ ቡድኖች አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ የውድድር ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ ጀምሮ ኋላ ላይ ከድል ከራቀ በኋላ በዘጠነኛው ሳምንት አሸንፎ ማገገም ቢችልም በአስረኛ ሳምንት መሸነፉን ተከትሎ በድጋሚ ወደ ውጤት መረጋጋት ውስጥ ለመግባት በንፅፅር ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ ለመከላከል ቅድሚያ ከማይሰጡ ቡድኖች አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻን የማሸነፍ መላ መዘየድ ይኖርበታል። በድኑ አዘውትሮ የሚጠቀምበት ቀጥተኛ አጨዋወት ነገም ተመራጭ አቀራረቡ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሀዋሳ ከተማ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎችም ጭምር ኳስን የመቆጣጠር ፍላጎት የማይታይበት እንደመሆኑ በነገው ጨዋታም ኳሱን ለድቻ በመልቀቅ በፈጣን ሽግግር አደጋ በመፍጠር ጎሎች ለማግኘት እንደሚጥሩ ይጠበቃል። የአማካዩ አለልኝ አዘነ የኳስ ስርጭትም ወደ ማጥቃት ለሚያደርጉት ሽግግር ወሳኝ ነው። ሆኖም በነገው ጨዋታ የዳንኤል ደርቤ መሰለፍ አጠራጣሪ መሆን እና እንደሚሰለፍ የሚጠበቀው መስፍን ታፈሰ በተሟላ ጤንነት መጫወት አለመጫወቱ በቡድኑ ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።

በሀዋሳ ከተማ በኩል እስራኤል እሸቱ በጉዳት አሁንም ረዘም ያለ ጊዜ ከሜዳ የሚርቅ ሲሆን ልምምድ የጀመረው ቸርነት አውሽም አይኖርም። ዳንኤል ደርቤ በጉዳት የመግባቱ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን መስፍን ታፈሰ በአንፃሩ በሰበታው ጨዋታ ከገጠመው ጉዳቱ አገግሞ ነገ ወደ ሜዳ ይመለሳል፡፡

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ

በጊዜያዊ አሰልጣኙ እየተመራ ጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን በማስመዝገብ ሽቅብ መውጣቱን ለመቀጠል አልሞ ወደ የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃል።
በለውጦች ማግስት የሚታዩ መነሳሳቶች እና የውጤት መሻሻሎች እየታዩበት የሚገኘው ወላይታ ድቻ ነገም በከፍተኛ የማሸነፍ ስሜት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ደለለኝ በቡድኑ አጨዋወት እና ቀዳሚ ተመራጭ ተጫዋቾች ምርጫ ላይ እምብዛም ለውጥ አለማድረጋቸውን ተከትሎ የቡድኑ ዋንኛ መሳርያ አዕምሯዊ ዝግጅት መሆኑን አሰልጣኙ በድሕረ ጨዋታ ቃለ ምልልሳቸው ገልፀዋል። ይህም የሊጉ መሪ መቐለን አሸንፎ መጣው ወላይታ ድቻ ተጨማሪ ኃይል የሚፈጥርለት ነው።

በነገው ጨዋታ ከሀዋሳ በተሻለ ኳስ ተቆጣጥረው እንደሚጫወቱ የሚጠበቁት ድቻዎች የመልሶ ማጥቃት ተጋላጭነትን መቀነስ ተቀዳሚ ሥራቸው መሆኑ አይቀሬ ነው። በተጨማሪም ከጨዋታው ድለ ለማሳካት የሀዋሳ ጠንካራ ጎን የሆነው የመስመር እንቅስቃሴ ላይ በሚኖሩ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ፈተና ይጠብቃቸዋል።

ወላይታ ድቻ በነገው ፍልሚያ በመቐለው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ደጉ ደበበን እንደማያሰልፍ ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

በሊጉ 12 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 6 በማሸነፍ ቀዳሚነቱን ሲይዝ ሀዋሳ 2 ጨዋታ አሸንፏል። በአራት አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ድቻ 13፣ ሀዋሳ 8 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ቤሌንጋ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – መሳይ ጳውሎስ – ያኦ ኦሊቨር

አለልኝ አዘነ – ተስፋዬ መላኩ

መስፍን ታፈሰ – ዘላለም ኢሳይያስ ሄኖክ ድልቢ

ብሩክ በየነ

ወላይታ ድቻ (4-3-2 / 4-2-3-1)

መክብብ ደገፉ

ያሬድ ዳዊት – ውብሸት ዓለማየሁ – አንተነህ ጉግሳ – ፀጋዬ አበራ

እድሪስ ሰዒድ – ተስፋዬ አለባቸው – በረከት ወልዴ

እዮብ ዓለማየሁ – ባዬ ገዛኸኝ – ቸርነት ጉግሳ

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ