በሸገር ደርቢ ዋዜማ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የተገባው ቃል ተፈፃሚ ሆኗል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ለኢትዮጵያ ቡና እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰጥቷል።

ሁለቱ የመዲናው ክለቦች በከተማው የመጫወቻ ሜዳ ለመገንባት የከተማ አስተዳደሩን ካርታ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ይታወሳል። ይህንን የክለቦቹን ጥያቄ ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በሸራተን በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ለክለቦቹ ጥያቄያቸውን በአፋጣኝ እንደሚመልሱ ቃል ገብተው ነበር። ምክትል ከንቲባው ዛሬ የክለቦቹን አመራሮች እና የተወሰኑ የሁለቱን ክለብ ደጋፊዎችን በፅህፈት ቤታቸው ጋብዘው የገቡትን ቃል ፈፅመዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን ወክለው የክለቡ የቦርድ ፀኃፊ አቶ ንዋይ በየነ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡናን ወክለው የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ተገኝተው የቅድመ ካርታ ማረጋገጫ ወረቀታቸውን ተረክበዋል።

ለቡ አካባቢ የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጫወቻ ሜዳ እንዲሁም ጀሞ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና የመጫወቻ ሜዳ ለረጅም ጊዜያት ምንም የግምባታ ስራ ሳይሰራባቸው ታጥረው መቆየታቸው ይታወሳል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ