ፋሲል ከነማ የትጥቅ ድጋፍ ተበረከተለት

የቢሃ ኮንስትራክሽን ባለቤት ለዐፄዎቹ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የትጥቅ ድጋፍ ሲያደርጉ በቻይና የሚኖሩ ግለሰብ ደግሞ ለ20 ዓመት በታች ቡድኑ ተመሳሳይ ድጋፍ አድርገዋል።

በጀርመን ተሰርተው የመጡት ትጥቆች ከ250-300 ሺህ ብር ወጪ እንደተደረገባቸው የተገለፀ ሲሆን ፋሲል ከነማ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ሙሉ ማልያ፣ ቱታ፣ የጉዞ ቲሸርት እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላት አልባሳትን ያካተተውን ድጋፍ ያበረከቱት የቢሃ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ኤፍሬም እያሱ ናቸው። ትጥቆቹን በድርጅቱ የፕሮዳክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አቤል እያሱ አማካኝነት ያስረከቡ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ አቢዮት ብርሃኑ እና ምክትል አሰልጣኙ ኃይሉ ነጋሽ ትጥቁን ተረክበዋል ።

የቢሃ ኮንስትራክሽን ባለቤት አቶ ኤፍሬም እያሱ በጎንደር እና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በርካታ ስራ በመስራት ላይ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን ለክለቡ ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ የድርጅቱ ባለቤት ከዚህ ቀደም የተማሩበትን (የመሰረት 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) የመማሪያ ክፍሎችን በማደስ እና አዲስ የመማሪያ ብሎኮችን ማሰራታቸውንና በቀጣይ ዓመታትም ለክለቡ ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል ።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና ከዚህ ቀደም ትኩረት እንደተነፈጋቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታ አቅርበው የነበሩት የፋሲል ከ20 ዓመት በታች ቡድን ቻይና በሚኖር ሙሌ ታረቀኝ የተባለ ግለሰብ አማካኝነት የትጥቅ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። አንደኛ እና ሁለተኛ ማሊያ፣ ጫማ፣ የልምምድ ቁሳቁሶች እና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዮት ብርሃኑ ከታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኝ ግርማይ ኪሮስ እና ከደጋፊዎች ማኅበር ስራ አስፈጻሚ ጋር በመሆን ለታዳጊ ተጫዋቾቹ አበርክተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ