በአዲስ አበባ የሚዘጋጀውን የፊፋ ኮንግረስ ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ውይይት ተደረገ

ዓለም አቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል ፊፋ 70ኛውን ዓመታዊ ኮንግረስ በአዲስ አበባ ያከናውናል። ይህንን ስብሰባ በስኬት ለማጠናቀቅም የተለያዩ አካላት እና የፊፋ ልዑኮችን ያካተተ ውይይት ተደርጓል።

በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አዳራሽ የተደረገው ይህ ውይይት የመሩት ወ/ሮ ካሪን አስተርበርገር (የፊፋ ኮርፖሬት ኤቨንት ማናጀር) ሲሆኑ መነሻ ሀሳቦችን በተዘጋጀ ሰነድ አማካኝነት ለታዳሚዎቹ ያካፈሉት ግለሰቧ ሰነዱን ካቀረቡ በኋላ የትኞቹ ሥራዎች ትኩረት ተሰጥተው መከናወን እንዳለባቸው ገልፀዋል። ከነዚህም መካከል፡-

– የቪዛ ዓይነት ቀድመው መለየት (በውይይቱ የሚሳተፉ አካላት የተለየ የኮንፍረስ ቪዛ መጠቀም አለባቸው።)

– ከስብሰባው በፊት ቀድመው የሚመጡት 300 ያህል የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ማስተናገድ

– በስብሰባው ተሳታፊ ለሚሆኑ አካላት የህክምና አገልግሎት።

– ለስብሰባው የሚረዱ ቁሳቁሶችን ከሀገሪቱ ህግ ጋር በማቀናጀት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት

– የትራንስፖርት አገልግሎትን እና የትራፊክ ፍሰት ማሳለጥ

– የስልክ እና ፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት ማዘጋጀት

– ጥበቃ እና ደህንነትን ማረጋጥ

ከውይይቱ በኋላ ኮንግረሱ በስኬት እንዲከናወን የሚያስችል በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂነት እና በስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብሳቢነት የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ተዋቅሯል። በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና የስፖርት ተቋማትም በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን እነሱም ስፖርት ኮሚሽን፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ የሴቶች ህፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ የባህር እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ የኤሜግሪሽን ጉዳዮች ጸህፈት ቤት፣ የአ.አ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የብሮድካስት ባለስልጣን እና የብሔራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ናቸው። ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ በኮሚቴው የሚካተቱ ተቋማት ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ታውቋል።

የፊፋ ልዑክ ዛሬ በውይይቱ ያነሳቸው ሀሳቦችን ተግባራዊነት እና የቅድመ ዝግጅቱ ደረጃ ምን እንደደረሰ የሚገመግም ልዑክ በመጋቢት ወር መጨረሻ እንደሚልክ የታወቀ ሲሆን ከዛ ቀደም ብሎ ዛሬ የተቋቋመው የዝግጅት ኮሚቴ የሥራ እቅዶች እና ተያያዥ ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ በየካቲት ወር አጋማሽ ወደ ፊፋ እንደሚላክ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

በግንቦት ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደው 70ኛው የፊፋ ኮንግረስን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከ1400 በላይ ተሳታፊዎች፣ 600 የሁነት አስተባባሪዎች እና ከ300 በላይ የማድያ አካላትን ተቀብላ የምታስተናግድ ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ