ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በፍቃዱ ወርቁ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል አዳማ ከተማን አሸነፈ

በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ በሜዳው አዳማ ከተማን አስተናግዶ በፍቃዱ ወርቁ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል 2-1 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ባህርዳር ከተማዎች በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ወደ አዲስ አበባ አቅንተው በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረቱበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ሳሙኤል ተስፋዬን በአዳማ ሲሶኮ በመተካት ወደ ሜዳ ሲገቡ ተጋባዦቹ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ሀዲያ ሆሳዕናን ካሸነፉበት ስብስብ ምኞት ደበበ እና ከነዓን ማርክነህን በመናፍ ዐወል እና ፉአድ ፈረጃ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ለመቆጣጠር ሲያደርጉት የነበረው ትግል ብዙ የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች እንዳይስተናገዱ አድርጓል። በአንፃራዊነት ተጋባዦቹ አዳማ ከተማዎች የሚያገኙትን ኳስ በቶሎ ወደ መስመር በማውጣት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረዋል። ቡድኑ በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ በ11ኛው ደቂቃ በቡልቻ ሹራ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ከመስመር ሰንዝሮ መክኖበታል። ነገር ግን ይህ የጨዋታ እንቅስቃሴ እንደሚያዋጣቸው ቀድመው የተረዱት አዳማዎች ከ3 ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ያገኙትን ኳስ ወደ መስመር አውጥተው ፍሬያማ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ፉአድ ፈረጃ ከበረከት ደስታ የተላከለትን ኳስ በመጠቀም ከተከላካይ ጀርባ ፈጥኖ በመውጣት ግብ አስቆጥሯል።

አጀማመራቸው ብዙም ጥሩ ያልነበረው ባህርዳሮች ከአዳማዎች በኩል የሚሰነዘሩ የመስመር ላይ ጥቃቶችን መመከት ላይ ተጠምደው ታይተዋል። ነገር ግን አዳማዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ አጨዋወታቸውን በመገደባቸው ቡድኑ በተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል። በ20ኛው ደቂቃም ማማዱ ሲዲቤ ራሱ ላይ የተሰራበትን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ግርማ ዲሳሳ ከመስመር ላይ አሻምቶት በግንባሩ ግብ አስቆጥሯል። 

ቡድኑን አቻ ያደረገው ማማዱ ሲዲቤ ሌላ ተጨማሪ ሙከራ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሰንዝሮ ወጥቶበታል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የሲዲቤ ጎል ያነቃቸው ባህርዳሮች ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በ25ኛው ደቂቃም ግርማ ከመስመር ላይ ያገኘውን ኳስ በሚገርም ብቃት ለፍፁም ሲያሻማው መናፍ ዐወል እንደምንም አውጥቶበታል። ከዚህ ለግብነት የቀረበ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ በፍፁም ዓለሙ ሁለት ተከታታይ ሙከራዎች መሪ ለመሆን ጥሮ ሳይሳካለት ቀርቷል።

ከ35ኛው ደቂቃ በኋላ ዳግም የተነቃቁት ተጋባዦቹ ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። በዚህም በረከት በ35ኛው ደቂቃ ጥሩ አክርሮ በመምታት የሞከረውን ፅዮን መርዕድ በጥሩ ብቃት አድኖበታል። ከደቂቃዎች በኋላም ቡልቻ ሹራ የባህር ዳር ተጨዋቾች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ጥሩ ሙከራ ሰንዝሮ ወጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ዜናው ፈረደ ከመስመር ላይ ያገኘውን ኳስ ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ መትቶ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ተጨዋቾቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ተሻሽለው ለመቅረብ የሞከሩት ባህርዳሮች ጥቃቶችን ከየአቅጣጫው መሰንዘር ጀምረዋል። አጋማሹ በተጀመረ በ8ኛው ደቂቃም ሳምሶን ጥላሁን ከመዓዘን ያሻገረውን ኳስ አዳማ ሲሶኮ ሲሞክረው ተከላካዮች ባወጡት አጋጣሚ ወደ ግብ ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ በ61ኛው ደቂቃ ዜናው ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ዳንኤል ኃይሉ ወደ ግብ መትቶት በመከነ አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ቀርበው ነበር።

በተቃራኒው በዚህ አጋማሽ ግብ እንዳይቆጠርባቸው ተጠንቅቀው ሲጫወቱ የነበሩት አዳማዎች ረጃጅም ኳሶችን እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ላይ ብቻ በመተማመን ግቦችን ለማስቆጠር ሲታትሩ ታይቷል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም በ68ኛው ደቂቃ የተገኘን ረጅም ኳስ ዳዋ ለቡልቻ አቀብሎት ቡልቻ በመገልበጥ (በመቀስ ምት) የሞከረበት አኳኋን ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርግ ተቃርቦ ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ አጨዋወት ረጅም ኳስ ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል ያሳለፉት አዳማዎች በባህርዳር ተከላካዮች ስህተት ታግዘው ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ምንም ጨዋታ በሜዳቸው ተሸንፈው የማያውቁት ባህርዳሮች የተጨዋች ለውጦችን በማድረግ ይበልጥ ጫና መፍጠር ጀምረዋል። በ72ኛው ደቂቃም ዜናው ከማማዱ የተቀበለውን ኳስ በሚገርም ጥበብ አታሎ ወደ ጎል ሞክሮ ቴዎድሮስ በቀለ እራሱን ለአደጋ አጋልጦ አውጥቶበታል። ከ3 ደቂቃዎች በኋላም ሲዲቤ ከዜናው የደረሰውን ኳስ እየገፋ ሄዶ ሲሞክረው ተከላካዮች ሲያወጡበት ያገኘው ዳንኤል ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ኢላማውን በሳተበት አጋጣሚ ቡድኑ ተጨማሪ ሙከራ አድርጓል።

በተለይ በግራ መስመር አጋድለው ጥቃቶችን ሲያነጣጥሩ የነበሩት የጣናው ሞገዶች በ83ኛው ደቂቃ ብቻ ሁለት ያለቀለት ዕድል አምልጣቸዋል። በደቂቃ ውስጥ ሁለቱንም ያለቀለት እድል ያገኘው ግርማ ዲሳሳ ኳሱን አቀብላለሁ ብሎ የመታውን ግብ ጠባቂው ጃኮ ፔንዜ አምክኖበታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግባቸውን መጠበቅ ላይ ተጠምደው የታዩት አዳማዎች በ88ኛው ደቂቃ እጅግ የማይታመን ኳስ አምክነዋል። ዳንኤል ኃይሉ የተሳሳተውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት አዳማዎች ቶሎ አስጀምረው የተገኘን ያለቀለት አጋጣሚ ተቀይሮ የገባው ኢስማኤል ሳንጋሪ በማይታመን ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በተጨመሩት 7 ደቂቃዎችም ባለሜዳዎቹ ያላቸውን መሳሪያ ሁሉ በመጠቀም ግቦችን ለማስቆጠር ጥረዋል። በ91ኛው ደቂቃም ቡድኑ በግራ መስመር የተገኘን የቅጣት ምት በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። ከዚህ በተጨማሪ በ93ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ ለማማዱ ሲዲቤ ጥሩ ኳስ ከመስመር አሻምቶለት ሲዲቤ አምክኖታል። የተጨመሩት 7 ደቂቃዎች ሊጠናቀቁ 60 ሰከንዶች በቀሩት ጊዜ የተገኘውን የጨዋታው የመጨረሻ የመዓዘን ምት ግን ግርማ ዲሳሳ አሻምቶት ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ወርቁ በግምባሩ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ጣፋጭ 3 ነጥብ አስጨብጧል። ጨዋታውም በባለሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


©ሶከር ኢትዮጵያ