የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-1 አዳማ ከተማ

ባህር ዳር ከተማ በሜዳው አዳማ ከተማን 2-1 ካሸነፈ በኋላ የባለሜዳዎቹ ቡድን አሰልጣኝ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ አስተያየታቸውን ለሚዲያ ለመግለፅ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።

👉 “ጨዋታውን ከማሸነፋችን በላይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጫዋቾቼ ላይ ያየሁት የማሸነፍ ስሜት አስደስቶኛል” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለታችንም ቀዝቃዛ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ስንከተል ነበር። ነገር ግን በእኛ በኩል የታየው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ በምንፈልገው መንገድ የሆነ አልነበረም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥሩ ነበርን። ጨዋታውን ከማሸነፋችን በላይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተጨዋቾቼ ላይ ያየሁት የማሸነፍ ስሜት አስደስቶኛል። ብዙ ጊዜ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ለተሸናፊ ቡድን አሳዛኝ ነው። ነገር ግን ለአሸናፊ ቡድን አስደሳች ነው እና እኔ በጣም ደስ ብሎኛል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ ስለተዳከመበት ምክንያት?

በዋናነት በመጀመሪያው አጋማሽ አንዳንድ ተጨዋቾቼ ላይ የትኩረት ማነስ ችግር ይታይ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ከተጨዋቾች ጉዳት ጋር በተያያዘ አዳዲስ ሚና የሰጠኋቸው ተጨዋቾች የተሰጣቸውን አዲስ ሚና እስኪለምዱ ጊዜ ወስዶብናል። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ የጨዋታ ዘዴ ለመጠቀም ሞክረናል። በዚህም በስተመጨረሻ የዘየድነው ዘዴ አዋቶን አሸንፈናል።

ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የሜዳው ላይ ጨዋታዎች ብዙ የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ስላላደረገበት ምክንያት?

እኛ ያመከናቸው ኳሶች እንዳሉ ሆነው ተጋጣሚያችን የተከተለው አጨዋወት ትንሽ ፈትኖናል። እነሱ እኛ የምናጠቃበትን መንገድ ዘግተው በረጃጅም ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ለዚህ ነው በሁለተኛው አጋማሽ በመሃል ለመሃል እና በመስመር እያፈራረቅን ጥቃቶችን በመሰንዘር ግቦችን ለማስቆጠር የታተርነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ