ከ11ኛ ሳምንት የዛሬ የሊጉ መርሐ ግብሮች መካከል ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ሰበታ ከተማን አስተናግዶ በሙኸዲን ሙሳ ብቸኛ ግብ አማካኝነት 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ከአስረኛ ሳምንቱ የወልቂጤ ከተማ ሽንፈት አማረ በቀለ ፣ በረከት ሳሙኤል እና ዋለልኝ ገብሬን በማሳረፍ ለሦስቱን ያሬዶች ( ያሬድ ዘውድነህ ፣ ያሬድ ሀሰን እና ያሬድ ታደሰ) የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል ሰጥተዋል። በተቃራኒው ሰበታዎች ሀዋሳን ድል ካደረጉበት ጨዋታ ምንም ለውጥ ያልተደረገበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ይዘው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት።
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ ከተማ የተጫወተው እና አሁን በሰበታ ከተማ ለሚገኘው አንተነህ ተስፋዬ የድሬዳዋ ከተማ ስፖርት ክለብ ደጋፊ ማህበር ስጦታ አበርክቶለታል።
የጨዋታውን የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሰበታ ሜዳ በመግባት እና የጎል ሙከራዎችንም በማድረግ በኩል የተሻሉ የነበሩ ሲሆን በ17ኛው ደቂቃ ላይም የድሬዳዋ ከተማው ያሬድ ዘውድነህ ከርቀት ያሻማውን ኳስ ኦዶንጎ ሪችሞንድ አግኝቶት ሞክሮ አጥቂው ሙህዲን ሙሳ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላም ድሬዎች በኦዶንጎ ሪችሞንድ እና በያሬድ ታደሰ አማካኝነት ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ሰበታ ከተማዎችም በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በ36ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ታደለ መንገሻ የተሻማለትን ኳስ ፍፁም ገብረማርያም አግኝቶ በጭንቅላት ሞክሯት በግቡ አቅራቢያ የወጣችበት አጋጣሚ በዚህ ረገድ የምትነሳ ናት።
የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተጠናቆ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ተጨማሪ ሁለት ደቂቃዎችን ባሳዩበት ቅፅበት ኦዶንጎ ሪችሞንድ ወደ ሰበታ የግብ ክልል ገብቶ ሙህዲን ሙሳን ከግብ ጠባቂው ጋር ማገናኘት ቢችልም ሙኸዲን ለመምታት በሚዘጋጅበት ቅፅበት የሰበታ ተከላካዮች ከኋላው መጥተው አስጥለውታል። የመጀመሪያ አጋማሽም በባለሜዳዎቹ መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተቀይሮ የገባው የሰበታ ከተማው ጌቱ ኃይለማርያም በቀኝ ክንፍ የድሬዳዋ ከተማ የጎል ክልል ውስጥ በመግባት ለኢብራሂም ከድር አቀብሎት ኢብራሂም ወደ ጎል የሞከራት ኳስ በግዙፉ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ተመልሳበታለች። በመልሶ ማጥቃት የድሬዳዋ ከተማው ሙህዲን ሙሳ ከግራ መስመር ወደ ለያሬድ ታደሰ አቀብሎት ወደ ጎል ሞክሯት ለጥቂት የወጣችበትን ኳስ በድጋሚ ሁለቱ ተጫዋቾች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ አደጋ ክልል ይዘውት ገብተው ያሬድ ከርቀት ሲሞክር የወጣችበት ሙከራ ደግሞ የባለሜዳዎቹ ምላሽ ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች የተሻለ የኳስ ቅብብል በማድረግ እና ወደ ጎል በመቅረብ በኩል ሰበታ ከተማዎች የተሻሉ የነበረ ቢሆንም በ65ኛው ደቂቃ የድሬዳዋ ከተማው ኦዶንጎ ሪችሞንድ ለሙኸዲን ሙሳ አቀብሎት ሙህዲን የሞከራትን እና የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጃዬ የመለሰበት አጋጣሚ በድሬዳዋ ከተማ በኩል የምታስቆጭ ነበረች።
ሰበታ ከተማዎች በታደለ መንገሻ እና በፍፁም ገብረማሪያም አማካኝነት በተደጋጋሚ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ጎል በመግባት የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በ76ኛው ደቂቃ ላይም ከኢብራሂም ከድር የተሻማለት ኳስን ናትናኤል ጋንቹላ ሞክሯት ሳምሶን መልሶበታል። በድጋሚ ሰበታዎች በግራ ክንፍ በኩል ኃይለሚካኤል አደፍርስ ያሻማውን ኳስ ታደለ መንገሻ አግኝቶ በጭንቅላት ሞክሯት የወጣችበት ኳስም እንግዶቹን ነጥብ ለማስጨበጥ የቀረበች ነበረች።
በመጨረሻም የሰበታ ከተማው ዳንኤል አጄይ ከተፈቀደለት የጎል ክልል ውጪ ኳስ በመያዙ ምክንያት የዕለቱ አርቢትር የሰጡትን ቅጣት ምት ሪችሞንድ አዶንጎ ሞክሯት ግብ ጠባቂው እንደያዘበት ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ