ሪፖርት | የአለልኝ አዘነ የሽርፍራፊ ሰከንድ ጎል ሀዋሳን ውድ ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች

በአስራ አንደኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ወላይታ ድቻን 2ለ1 በማሸነፍ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ አግኝቷል፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም በሰበታ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ተከላካዩ አዲስዓለም ተስፋዬን በአጥቂው ሄኖክ አየለ ብቻ ሲለውጡ መሪው መቐለን በሜዳቸው ረተው የመጡት ወላይታ ድቻዎች በተመሳሳይ በአንድ ተጫዋች ላይ ቅያሪን በማድረግ ባለፈው ሳምንት ጉዳት ገጥሞት በነበረው ደጉ ደበበ ምትክ ፀጋዬ አበራን ተክተው ገብተዋል፡፡

ጨዋታው ሊጀመር ሁለቱ ቡድኖች ወደ ሜዳ ሲገቡ የሀዋሳ ከተማው ካሜሩናዊ ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኢኖህ በጣቱ ላይ ያደረገውን ቀለበት በዕለቱ ዳኞች እንዲያወጣ ሲነገረው አሻፈረኝ በማለቱ በዳኛው እና ተጫዋቹ መሀል በተፈጠረ ያለ መግባባት ጨዋታው ከተያዘለት የማስጀመሪያ ሰዓት አራት ደቂቃዎች ዘግይቶ ተጫዋቹም ካወለቀ በኋላ ጨዋታው ሊጀመር ችሏል፡፡

የዕለቱ ዳኛ የጨዋታውን ማስጀመርያ ፊሽካ ባሰሙበት ቅፅበት ኳሷ ወደ ወላይታ ድቻ ግብ ክልል አምርታ ሄኖክ አየለ ብልጠቱን ተጠቅሞ በቀጥታ ሲመታት የመሀል ተከላካዩ ውብሸት ዓለማየሁ በሳጥን ውስጥ በእጅ የነካት ቢሆንም የዕለቱ ዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን በዝምታ ማለፋቸው የክለቡን ተጫዋቾች ጨምሮ ከደጋፊውም ዘንድ ተቃውሞን አስተነስታለች፡

ሀዋሳ ከተማ ከተጋጣሚው ወላይታ ድቻ በአንፃራዊነት ተሽሎ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ከዚህ ቀደም መረጋጋት የተሳነው የሀዋሳ የአማካይ ክፍል ከወትሮው ተጠግኖ መቅረቡ በማጥቃት ሽግግሩ የተሻሉ መሆን እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ የሄኖክ ድልቢ እና የአለልኝ አዘነ ኳሶች በግራ እና ቀኝ ወደተሰለፉት መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ በሚያሰራጯቸው ኳሶች ጥሩ ጅማሮ ቢያደርጉም በወጥነት መዝለቅ ግን አልቻሉም፡፡ የጦና ንቦቹ በበኩላቸው በተደራጀ መከላከልና ወደ መጥቃት ሽግግሩ ሲገቡ ጥሩዎች ነበሩ፡፡ ሀዋሳዎች ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ሊገቡ ሲሉ የተስፋዬ አለባቸው እና በረከት ወልዴ አጥሩን በሚገባ ሸፍኖ መቅረብም በቀላሉ ግባቸውን እንዳያስደፍሩ በተወሰነ መልኩ ረድቷቸዋል፡፡

10ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ተመልክተናል፡፡ ሄኖክ አየለ ያቀበለውን ብሩክ በየነ በቀጥታ መትቶ ለጥቂት በወጣችበት ሙከራ ወደ ሳጥን መጠጋት የቻሉት ባለሜዳዎች ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ በሚገባ አስተውለናል፡፡ በተለይ ከግራ መስመር እየነሳ ሰብሮ ለመግባት ሲሞከር የነበረው ብሩክ በየነ ምንም እንኳን በክፍት ሂደት ነፃ የማስቆጠር ዕድሎችን ቢያገኝም የኳሱ የመጨረሻ ማረፊያ ስኬታማ ባለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲባክኑ ውለዋል፡፡

የሀዋሳን የአጨዋወት መንገድ ሲያጠኑ የቆዩ የሚመስሉት ድቻዎች ልክ ከሀያ አምስተኛው ደቂቃ በኃላ ተረጋግቶ በመጫወት እና በሚያገኙት ቀዳዳ ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል በመሄድ ጥቃት ለመሰንዘር አልተቸገሩም፡፡ 25ኛው ደቂቃ የሀዋሳን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ በግራ ባጋደለ ቦታ ላይ ፀጋዬ አበራ ያገኛኝን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ የግቡን የላይኛው ብረት ነክታ የወጣችበት ሙከራ ምናልባትም ድቻዎችን ቀዳሚ የምታደርግ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ከዚህ ሙከራ ሁለት ደቂቃ በኃላ አሁንም ከቀኝ በኩል ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው እዮብ ዓለማየሁ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ቢሊንጋ ወደ ውጪ በአስደናቂ መልኩ ሊያወጣት ቻለ እንጂ እንግዳው ቡድን ጫና አሳድሮ ግብ ለማስቆጠር መቃረቡን ያመላከቱ ነበሩ፡፡

ከድቻዎች ሙከራ በኃላ ወደ ራሳቸው አጨዋወት በፍጥነት ተመልሰው አፀፋ ለመመለስ በሚመስል መልኩ ማጥቃት ላይ በቶሎ ያንሰራሩት ሀዋሳዎች ሁለት ያለቀላቸውን ንፁህ ዕድሎችን አግኝተው አንዷን ወደ ግብነት ለውጠዋታል፡፡ 33ኛው ደቂቃ በግል ጥረቱ የድቻን ተከላካይ ሲረብሽ የነበረው ብሩክ በየነ ለሄኖክ አየለ ሰጥቶት ሄኖክ አየለም በቀጥታ ሲመታት ኳሷ ኃይል ስላልነበራት በቀላሉ ግብ ጠባቂው መክብብ ተቆጣጥሯታል፡፡ ከሙራዋ በኋላ አስር ደቂቃዎች በኋላ ሀይቆቹ መሪ የሆኑበት ግብ አስቆጥረዋል፡፡ መረጋጋት የተሳነው የድቻ የተከላካይ ክፍልን ስህተት ያየው ብሩክ በየነ በቀኝ በኩል ወደ ግብ የላካትን ኳስ አጥቂው ሄኖክ አየለ ወደ ግብነት ለውጧት ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

ሁለቱ ክለቦች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ ወላይታ ድቻን ለመደገፍ የገቡ ሁለት ደጋፊዎች ዕርስ በዕርስ በትሪቡኑ ግራ በኩል የተጣሉ ሲሆን የፀጥታ አካላት እና በሜዳ ላይ ሲያስተባብሩ የነበሩ የደጋፊ ማኅበር አካላት በቀላሉ የተቆጣጠሩበት መንገድ ሊበረታታ የሚገባው መልካም ተግባር ነበር፡፡

ከእረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥ ካደረጉ በኃላ ቅያሪያቸው ትክክል መሆኑን በሜዳ ላይ በግልፅ መመልከት የቻልንበት፤ ሀዋሳ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ካሳዩት አንፃር ቀዝቀዝ ብለው በመጀመር ረጃጅም ኳስን መጠቀሙ ላይ አተኩረው የገቡበት ነበር፡፡ 64ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል መስፍን ታፈሰ ሁለት ጊዜ አግኝቷት በጉዳት በግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ተቀይሮ የገባው መኳንንት አሸናፊ የተያዙበት ሀዋሳዎች ለማጥቃቱ ቀዳሚ መሆናቸውን ያሳዩ ነበሩ፡፡

ከእነኚህ ሙከራዎች በኃላ መዝለቅ ያልቻለው የሀዋሳ የማጥቃች ሂደት በተቃራኒው በድቻዎች ተተክቷል፡፡ በተለይ 55ኛው ደቂቃ ላይ የቀኝ ተከላካዩ ያሬድ ዳዊትን ተክቶ የገባው ፀጋዬ ብርሀኑ በቀኝ መስመር በኩል ተጠግቶ መጫወት ከጀመረ ወዲህ ወላይታ ድቻዎች በፍጥነት ቶሎ ቶሎ መድረስ ችለዋል፡፡ በቀኝ በኩል ፀጋዬ ነፃ አቋቋም ለነበረው ባዬ ሰጥቶት ባዬ በቀላሉ ካመከናት ኳስ በኃላ አቻ የሚሆኑበት ግብ አግኝተዋል፡፡ የጨዋታው ደቂቃ እየተጋመሰ ሲመጣ በመሐል ክፍል ኳስን በማስጣል ሲዋጣለት የነበረው ተስፋዬ አለባቸው 79ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ ሲመታ የሀዋሳው ተከላካይ ላውረንስ ጨርፏት አቅጣጫዋን ቀይራ ባዬ ገዛኸኝ እግር ስር ስትገባ አጥቂው አንድ ጊዜ ብቻ ገፋ ካደረገ በኃላ አስቆጥሮ ድቻን 1ለ1 አድርጓል፡፡

ከግቧ በኃላ በእንቅስቃሴ ረገድ ወላይታዎች የበላይነት ቢያሳድርጉም በሙከራ ግን ተመሳሳይ ቁጥር ሁለቱም ነበራቸው፡፡ ሀዋሳዎች ዘላለም ኢሳይያስ ከማዕዘን ሲያሻማ ብሩክ በየነ መቷት ተከላካዮች ተደርበው ያወጧት እና ራሱ ብሩክ በየነ ተጫዋቾችን አልፎ ወደ ሳጥን ገብቶ የመታት ኳስ ባለ ሜዳውን ወደ መሪነት ለማሸጋገር የተቃጡ ሙከራች ነበሩ፡፡

የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቸርነት ጉግሳ ወደ ቀኝ ባዘነበለ መልኩ እየነዳ መትቶ ለባዬ ሰጥቶት አምበሉ ባዬም ከግብ ጠባቂው ቢሊንጋ ፊት ለፊት ለነበረው ፀጋዬ ብርሀኑ ቢሰጠውም ፀጋዬ የመታት ኳስ ጠንካራ ባለመሆኗ ግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ያዛት እንጂ እንግዳውን ቡድን ሶስት ነጥብ ልታስጨብጥ የቀረበች ትሆን ነበር፡፡

ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ በተሰጠው አራት ጭማሪ ደቂቃ ላይ ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ግብ አስቆጥሯል፡፡ 90+3 ላይ ጭማሪ ሊጠናቀቅ 58 ሰከንዶች ብቻ ሲቀሩት ሀዋሳ ከተማዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት አማካዩ ዘላለም ኢሳይያስ ወደ ግብ ሲያሻማ የግብ ጠባቂው መኳንንት አሸናፊ የአቋቋም ስህተት ተክሎበት አለልኝ አዘነ ከመሀል ዘሎ በመነሳት በግንባር ገጭቶ ከመረብ ጋር አሳርፏት ሀዋሳን ወደ መሪነትት አሸጋግሯል፡፡ ከግቧ በኋላ ኳሷ መሀል ሜዳ መታ እንደተጀመረች ተጠናቋል፡፡ ሀዋሳም 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሎበታል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ