በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ሙሉዓለም መስፍን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹ በድል በመወጣት መሪውን መቐለ በቅርብ ርቀት መከተላቸውን ቀጥለዋል።
ከሁለቱ ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ ከመካሄዱ በፊት አዲስ በተዋቀረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደጋፊዎች ጥምረት አማካኝነት የኢትዮጵያ ቡናና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በጋራ በመሆን ከ10 የሊጉ ክለቦች ከተወከሉ ደጋፊዎች ጋር የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታን አድርገዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የ5-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ሌላው ከጨዋታው መጀመር በፊት በቅርቡ አጋጥሟት በነበረው የኩላሊት ህመም በመላ የስፖርት ቤተሰቡ ድጋፍ የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አድርጋ ወደ ሙሉ ጤንነቷ የተመለሰችው ወጣት ሀያት ኑርሁሴን በስታዲየሙ በመገኘት ለደገፋት የስፖርት ቤተሰብ ምስጋናዋን አቅርባለች።
በዛሬው ጨዋታ ባለ ሜዳ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወልዋሎ አቻ ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ ዓለምአንተ ካሣን አስወጥተው በታፈሰ ሰለሞን ብቻ ተክተው ወደ ተጠባቂው ጨዋታ ሲገቡ በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባህር ዳርን ከረታው የቡድን ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሬ አድርገዋል። በዚህም በአብዱልከሪም መሐመድና አስቻለው ታመነ ምትክ የአብስራ ተስፋዬና ደስታ ደሙን በመተካት ወደ ጨዋታው መግባት ችለዋል።
በጨዋታው ኳስን ከራሱ ግብ በመመስረት በኳስ ቁጥጥር ለመጫወት የሚጥረው ኢትዮጵያ ቡና በጨዋታው በተወሰኑ መልኩ ወጣ ገባ በሚል የቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጫዋችን መሠረት ባደረገ ከፍተኛ ጫና ሲፈተን ውሏል። የቡና ተጫዋቾች ኳስን እንዳይመሰርቱ ከፍተኛ ጫና ለመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በተለዋዋጭ አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉበት የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ነበር።
ጊዮርጊሶች በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች በከፍተኛ ብርታት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ጫና ውስጥ መክተት ቢችሉም በዛሬው ጨዋታ አማኑኤል ዮሐንስን በቀደመው ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይነት ሚናው ላይ የተጠቀሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን በከፍተኛ ጫና ውስጥ ቢሆንም በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመሸጋገር ያደረጉትን ጥረት ጥሩ የሚባል ነበር።
የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነበሩ። በ13ኛው ደቂቃ ደስታ ደሙ ከግራ መስመር ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለለትን ኳስ በቀኝ አጥብቦ ከገባ በኃላ ከጠበበ አንግል ኳሱን አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ከግቡ አናት በላይ የሰደዳት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።
በአጋማሹ ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄድ ከጊዮርጊሶች ጥረት መዳከም የተነሳ በተሻለ ወደ ጨዋታው መግባት የቻሉት ቡናማዎቹ ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉበት አጋማሽ ነበር። በ16ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ግብ የላካትና ማታሲ ያዳነበት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸው ነበረች።
በጨዋታው ሂደት መጀመሪያ ላይ ከጀመሩበት የትጋት መጠን ቀስ በቀስ እየወረዱ የመጡትን የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾችን በተለይ የመስመር አጥቂዎች በሂደት ጫና ለመፍጠር ያደረጉትን ጥረት መቀነሳቸውን የተመለከተው የቡድኑ የፊት አጥቂ ጌታነህ ከበደ በቀደመው መልኩ ወጥተው ጫና እንዲፈጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተጫዋቾቹን ከገሰፀ በኃላ ጊዮርጊሶች ዳግም የትጋት መጠናቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል። በዚህም በፈጠሩት ጫና መልሰው ያገኙትን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ራሱ ጌታነህ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚ አስቆጭ ነበር።
በሒደት ወደ ጨዋታው የተመለሱት ቡናዎች በ31ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሐንስ ሁለቱን የቅዱስ ጊዮርጊሶች የመከላከል መስመሮች ባስከፈተች እጅግ አስደናቂ ኳስ ተጠቅሞ አህመድ ረሺድ ወደ ግብ ሊሞክራት ሲል ፓትሪክ ማታሲ ፈጥኖ ደርሶ ያዳነበት ኳስ አደገኛ አጋጣሚ ነበረች። ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቡናዎች በ34ኛው ደቂቃ ከማዕዘን በአጭሩ የጀመሩትን ኳስ ሚኪያስና ሀብታሙ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል አልፈው ለእንዳለ አመቻችተው አቀብለውት ወደ ግብ የላካትና የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ በቡናዎች በኩል የተደረገች አስደንጋጭ ሙከራ ነበረች። በተመሳሳይ ሂደት በ36ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት አሻሙ ተብሎ ሲጠበቅ በአጭር ኳስ ታፈሰ ሰለሞንና ሚኪያስ ተቀባብለው በስተመጨረሻ ታፈሰ አክርሮ የመታት ኳስ ማታሲ በአስደናቂ ብቃት ሊያድንበት ችሏል።
ተመጣጣኝ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ሁለቱ ግብ ነበር ወደ መልበሻ ቤት ማምራት የቻሉት። በእረፍት ሰዓትም ሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ የፕሪምየር ሊጉ ክለብ አመራሮች ከከተማ አስተዳደሩ የምስጋና ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ እጅግ የተለየን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመመልከት ችለናል። በመጀመሪያው አጋማሽ መተግበር ያሰቡትን ከፍተኛ ጫና አጠናክረው የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ የቡናን ስህተት ከመጠበቅ በዘለለ በራሳቸው መገለጫ አጨዋወት እድሎችን ለመፍጠር የተጉበት አጋማሽ ነበር። በ49ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ ከመቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ጠርዝ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ የሞከራትና ተክለማርያም በሚገርም ቅልጥፍና ያወጠበት ኳስ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ጊዮርጊሶች በ50ኛው ደቂቃ እንዲሁ ጌታነህ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን ኳስ ተክለማርያም ሊያድንበት ችሏል።
ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ጫና ፈጥሮ ለመጫወት በመሠረታዊነት በሚፈልገው የአዕምሮ ዝግጁነት ደረጃ ላይ የነበሩት ጊዮርጊሶች ለቡናዎች ጨዋታውን አክብደውባቸው ተስተውሏል። በ58ኛው ደቂቃም ፓትሪክ ማታሲ በቀጥታ ከተከላካዮች ጀርባ የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ጌታነህ ከተከላካዮች ሾልኮ ወደ ግብ የላካት ኳስ ተክለማርያም በማዳኑ የተገኘውን የማዕዘን ምት ተጠቅሞ ከኳስ ርቆ በሚገኘው ቋሚ አካባቢ የነበረው ሙሉዓለም መስፍን በእግሩ ደግፍ በማድረግ ቡድኑን መሪ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሙሉዓለም ከአንድ ዓመት በፊት በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ተመሳሳይ ጨዋታ ላይ በተመሳሳይ የሜዳው ወገን ከማዓዘን ምት የቸነሳች ኳስ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ከግቧ መቆጠር በኃላ በመጠኑም ቢሆን የመቀዛዝ ቢያሳዩም አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት ሲሞክሩ ከነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ጀርባ የነበሩት ክፍት ቦታዎች ለማጥቃት በቀጥተኛ አጨዋወት ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ አልሆኑም እንጂ አስፈሪ ነበር። በአንፃሩ አስቀድመው በያዙት የጨዋታ እቅድ የፀኑት ቡናዎች በ77ኛው ደቂቃ ከመስመር ያለፈለትን ኳስ እንዳለ የሞከረውና ማታሲ ካዳነበት ኳስ ውጭ የጠሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ጊዮርጊሶች ውጤቱን ለማስጠበቅ የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ያስገባሉ ተብሎ ቢጠበቅሞ አሰልጣኝ ሰርዳን ግን እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ድረስ ለማጥቃት በማሰብ የማጥቃት ባህሪ የተላበሱ ተጫዋቾችን በማስገባት ለማጥቃት የነበራቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ጨዋታው በጊዮርጊሶች የ1ለ0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ከመሪው ያላቸው የነጥብ ልዩነት በሁለት ነጥብ እንዲቀጥል ማድረግ ችለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ