ሪፖርት | መቐለዎች በኦኪኪ ኦፎላቢ ጎል ስሑል ሽረን አሸንፈው መሪነታቸውን አስጠብቀዋል

ውዝግብ የተሞላበት የ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ አንተነህ ገብረክርስቶስ፣ አሚን ነስሩ፣ ሥዩም ተስፋዬ እና ኤፍሬም አሻሞን በላውረንስ ኤድዋርድ፣ አስናቀ ሞገስ፣ አሸናፊ ሀፍቱ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ተክተው ሲገቡ ስሑል ሽረዎችም ባለፈው ጨዋታ ከጅማ አባጅፋር ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ረመዳን የሱፍን በሸዊት ዮሐንስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች፣ ኃይል የተቀላቀለባቸው አጨዋወቶች እና በበርካታ ካርዶች የታጀበው ይህ ጨዋታ አሰልቺ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር። ሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ይልቅ የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾች ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት እና የዋና ዳኛው ባህሩ ተካ አወዛጋቢ ውሳኔዎች የጨዋታው አበይት ጉዳዮች ነበሩ። በተለይም ዋና ዳኛው ውጥረት የተሞላበትን ጨዋታ የመሩበት መንገድ ለበርካታ ውዝግቦች እና ጭቅጭቆች መንስኤዎች ነበሩ።

በአስራ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ የስሑል ሽረው የመስመር አማካይ ዲዲዬ ለብሪ ከኳስ ውጭ አስናቀ ሞገስ ላይ ጥፋት ሰርተሀል በሚል በቀጥታ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። በዚህም ሽረዎች ቀሪዎቹን ረጅም ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል።

በጨዋታው የተለመደው ቀጥተኛ አጨዋወት መርጠው የገቡት ባለሜዳዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለት ያለቀላቸው ሙከራዎች አድርገው በወንድወሰን አሸናፊ ጥረት መክነዋል። በተለይም አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሙልጌታ ወልደዮርጊስ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ወንድወሰን አሸናፊ የመለሳት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች። በያሬድ ከበደ ተቀይሮ በገባው ያሬድ ብርሀኑ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ከርቀት ሙከራዎች አድርገው ወደ ግብነት ሳይቀየሩ የቀሩትም የመቐለ መልካም አጋጣሚዎች ነበሩ።

አይቮሪኮስታዊውን ተጫዋች በቀይ ካርድ ካጡ በኋላ አፈግፍገው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ስሑል ሽረዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎች መፍጠራቸው አልቀረም። ከነዚህም በፍሊፕ ኦቮኖ ስህተት ተገኝታ ፎፋና ሞክሯት የኃላ ኃላ ጥፋት የተባለችው ሙከራ እና ሳሊፍ ፎፋና ከሸዊት ዮሐንስ በጥሩ ሁኔታ ተሻግሮለት ሳያገኛው ወደ ውጭ የወጣችው ንፁህ የግብ ዕድሎች ይጠቀሳሉ።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ አሰልቺ የነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በሙከራ ረገድ የመቐለዎች ብልጫ የታየበት ነበር። በአጋማሹ የተጫዋች ለውጥ አድርገው የገቡት መቐለዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በሄኖክ ኢሳይያስ እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል።
በተለይም ኦኪኪ ኦፎላቢ ከሄኖክ የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ መቐለን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

ከደቂቃዎች በኃላ መቐለዎች መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል አምክነዋል። ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ናይጄርያዊው ኦኪኪ ኦፎላቢ መትቶ በወንድወሰን ድንቅ ብቃት ተመልሶበታል።

ጨዋታው ጠንካራ ሙከራዎች ሳይታዩበት ዘልቆ የመጨረሻ አስር ደቂቃ ሲቀረው መቐለ ድል ያስመዘገበበትን ጎል አግኝቷል። በ81ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው ያሻማትን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል በግንባሩ ጨርፎ ለኦኪኪ ኦፎላቢ አመቻችቶለት አጥቂው በግንባሩ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ በኃላም በሀምሳ አራተኛው ደቂቃ ቢጫ ካርድ ያየው ኦኪኪ ኦፎላቢ ማልያውን አውልቆ ደስታውን በመግለፁ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

መሪ የምታደርጋቸው ግብ ካገኙ በኃላ በተጫዋች ቁጥር ከተጋጣሚያቸው ጋር የተስተካከሉት መቐለዎች በያሬድ ብርሀኑ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት ልዩነቱን የሚያሰፉበት ዕድል አግኝተው ነበር። በተለይም አማኑኤል ከመስመር ያሬድ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።
በሁለት ቀይ ካርዶች እና በርካታ ቢጫ ካርዶች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ በመቐለ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ተከትሎ ቡድኑ ከተከታዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ነጥቦች በልጦ ሊጉን በ22 ነጥቦች መምራቱን ቀጥሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ