በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 2-1 ማሸነፍ ከቻለ በኃላ የቡድኔቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡
👉 ” ተጫዋቾቼ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እንደሚያገቡ እያመኑ ስለመጡ ይህ የሚቀጥል ይመስለኛል” አዲሴ ካሳ ሀዋሳ ከተማ
ባለፈው ሳምንት ነጥብ ጥላችሁ ነበር የተመለሳችሁት የዛሬውን ጨዋታ ግን እንዴት ተመለከትከው ?
ከባድ ጨዋታ ነበር ፤ በእነሱ በኩልም በኛም። በተለይ ከዕረፍት በኃላ የኛ አጨዋወት ተቀይሯል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ነጥብ ለመያዝ ያደረግነው ጥረት ትንሽ ጫና ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ጎል ካገቡብን በኃላ ደግሞ እንደገና የተሻልን ሆነናል። ይሄ የኳስ ጨዋታው ህግ ነው፡፡ ብዙ ቦታ እንደዚህ እየሆንን ነው፡፡ ውጤት የማስጠበቅ ነገሩ ሁሉም ጋር አንድ እየሆነ ነው፡፡ በጀመርንበት ሂደት እየጨረስን አይደለም። በተለይ አንድ ቡድን ጎል ካገባ በኃላ እሱን ለማስጠበቅ ወደ ኃላ እያለ አደጋ ውስጥ እየገባን ነው። ዛሬ በደንብ መጫወት እንችል ነበር። ምክንያቱም በኃላ ላይ ጎል ከገባብን በኃላ ያደረግነው እንቅስቃሴን ከመጀመሪያው ብንቀጥል ምናልባት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ እዚህ ደረጃም አንደረስም ነበር ለማንኛውም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጎል አግብተን አሸንፈናል፡፡ የሚመጣው ነገር ስለማይታወቅ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ መታገል ነው። ተጫዋቾቼ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እንደሚያገቡ እያመኑ ስለመጡ የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡
ቡድኑ በተለይ በአማካይ ስፍራው ላይ ለውጥ እየታየበት ነው። ምንያህል ቀጣይነት ይኖረዋል ?
አዎ ትክክል ነው ይሄን አጨዋወት የጀመርነው በዚህ ጨዋታ አይደለም። አዲስ አበባ ከሰበታ ጋር ስንጫወት ከዕረፍት በኃላ የመጣ እንቅስቃሴ ነበር። ያደረግነው እሱን ነው። በዛ ጨዋታ ከዕረፍት በኃላ የነበረው ቡድን ነው የገባው ያየነውም እሱን ነገር ነው፡፡ የተሻለ ነገር ነው፡፡ በይበልጥ በራስ መታማመን ስትጀምር እንደዚህ ዓይነህ አጨዋወት ይኖራል፡፡ ግን አሁን የጫናው ነገር በጣም ከባድ ነው። ከውጪ ያለው ነገር ይከብዳል ተጫዋቹንም ከመስመር ያወጣዋል ምን ያህል ተቋቁመን እንጫወታለን የሚለው ነገር ነው እንጂ ተጫዋቾቼ ጥሩ ናቸው።
👉 “ድሉን እኛ ነን አሳልፈን የሰጠናቸው” ደለለኝ ደቻሳ ጊዜያዊ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ
ስለጨዋታው
እንዳያችሁት ጨዋታው በጣም ከባድ ጨዋታ ነው፡፡ ሀዋሳ ሜዳው ላይ በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን እኛ ስንመጣም ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው። እንደሌሎች ከሜዳ ውጪ እንደሚጫወቱ ቡድኖች ሁለት ነጥብ ወይንም ሌላ ነገሮችን ሳይሆን ያለንን አሟጠን ተጫውተን ካለንበት ደረጃ ለመውጣት ሦስት ነጥብ ፈልገን ስለመጣን በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበሩ፡፡ በተለይ እኛም ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ያለ መጠቀም ነገር አለ፡፡ ሁለተኛ አጋማሽን እንዳያችሁት ያሉንን ነገሮች ቀይረን ነው የገባነው፡፡ የተወሰኑ ልጆችንም ቀይረናል፡፡ ብቻ ድሉን እኛ ነን አሳልፈን የሰጠናቸው፡፡ ቡድኑ በአብዛኛው ወጣት ነው ፤ በአዕምሮም ሆነ በፊዚካል ስራዎች ላይ አትኩረን እየሰራን ነው፡፡ ቡድኑ ላይ ግን በሂደት ለውጥ አለ ከሜዳ ውጪ የሚጫወት ቡድን አይመስልም፡፡ ማጥቃት ላይ እየተጫወትን ስለሆነ በቀጣይም መከላከል ላይ ያለንን ቀርፈን ጥሩ ቡድን በተሻለ ይዘን እንቀርባለን፡፡
የመከላከል ችግር በተደጋጋሚ ቡድኑ ላይ ይታያል የዛሬዋም ግብ ከመዘናጋት ጋር ተደምራ የተፈጠረች። ይሄ ከቀጠለ ዋጋ አያስከፍልም ?
ከኃላ መስመራችን ላይ በተወሰነ መልኩ ክፍተቶች አሉ አለመረጋጋትም አለ፡፡ ያው ወደ መጨረሻ አካባቢ ውጤቱንም ፍለጋ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ያው መስራት ያለብን ነገር አለ። በተለይ ከመከላከል ጋር መስራት ባለብን ላይ እንሰራለን የሚል እሳቤ አለኝ። ክፍቶች ለቀጣይ ትምህርት ይሆኑናል ብዬ አስባለሁ፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ