የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-0 ሰበታ ከተማ

ድሬዳዋ ከተማ ሰበታ ከተማን አስተናግዶ 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

👉 ” ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ካሉ ጥሩ ነገር መስራት ይቻላል” ስምዖን ዓባይ (ድሬዳዋ ከተማ)

ስለጨዋታው

የጠበኩትን ነው ያገኘውት፤ ኳስ ይይዛሉ ብዙ ግን ፍሰቱ ፍጥነት አልነበረውም፤ አዝጋሚ ነበር። ያንንም ከዕረፍት በፊት መግታት ችለን ነበር፤ ከዕረፍት በኋላ ግን ፈቀድንላቸው። አንድ ጎል ብቻ አስተማማኝ አይደለም። ሙኸዲን ከዕረፍት በፊት ያገኛትን አጋጣሚ ብናገባ ሦስትም አራትም ልናገባ እንችል ነበር። ሆኖም አንድ ጎል ብቻውን ስለማያስተማምን ያንን ለማስጠበቅ ባደረግነው ጥረት ኳሱን የተሻለ መያዝ ችለው ነበር። ያንንም ጠብቄዋለው። ግን ከባድ አልነበረም። ሊጉም ባለፈው እንደታናገርኩት ከባድ አይደለም። ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾች ካሉ ጥሩ ነገር መስራት ይቻላል።

👉 “ቢያንስ ነጥብ ተጋርተን መውጣት ነበረብን” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ስለጨዋታው

ወደ ጨዋታው ለመግባት መዝግየት ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ መቀዛቀዝ ነበረብን፤ ከመከላከል ጋር ተያይዞ ክፍተቶች ነበሩብን። እሱን ካስተካከልን በኋላ ግን ወደ ጨዋታው መመለስ ችለናል። ማሸነፍ ባንችልም መልካም ነበር።

ስለውጤቱ

እንደኔ አቻ መውጣት ነበረብን። እነሱም ጥሩ ተጫውተዋል። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ እንደነበረን ጫና ቢያንስ ግብ አስቆጥረን ነጥብ መጋራት ነበረብን። በተለይ ሰዓቱ እያለቀ ሲሄድ በጣም አፈግፍገው ነበር የተጫወቱት። እና ያን ተጠቅመን ብዙ ዕድሎችን ፈጥረናል። ቢያንስ ነጥብ ተጋርተን መውጣት ነበረብን።

ቡድኑ ከጨዋታው ማግኘት ስለፈለገው ውጤት

ክፍት የነበረ ጨዋታ ነው። እኛም አጥቅተን ለመጫወት እንጂ ተከላክለን ወይ ተኝተን አንድ ነጥብ ይዞ ለመሄድ አልነበረም። ምክንያቱም በአቻ እና በማሸነፍ መሀከል ሰፊ ልዩነት ነው ያለው። በተደጋጋሚ አቻ ለመውጣት መጫወት ብዙ ነጥብ ያስጥላል። በተለይ ከሰንጠረዡ አጋማሽ በታች ያሉ ቡድኖችን አለማሸነፍ ለአደጋ ያጋልጣል። ለማሸነፍ ነበር የገባነው ፤ አቀራረባችንም ያ ነው የነበረው። አጋጣሚ እግርኳስ ያመጣውን መቀበል ነው። ተሸንፋናል።


©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ