ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር እና ፋሲል ከነማ ያለ ግብ ተጠናቋል

በአስራ አንደኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ላይ ፋሲል ከነማን የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር ያለ ጎል አቻ ተለያይቷል።

ጅማ ባለፈው ሳምንት ከስሑል ሽረ ነጥብ ከተጋራው ስብስብ መካከል ኤፍሬም ጌታቸውን አሳርፎ ሀብታሙ ንጉሴን ወደ ሜዳ ሲያስገባ ፋሲሎች በበኩላቸው በኦሲ ማውሊ ምትክ አማካዩ ኪሩቤል ኃይሉ ተተክቶ ገብቷል።

በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ቀጥተኛ ኳሶችን መሰረት አድርገው የሚጫወቱት ጅማዎች ተደጋጋሚ እድሎችን በአምረላ ደልታታ ሄኖክ ገምቴሳ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች እንዲሁም በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ መፍጠር ቢችሉም ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም።

በፋሲሎች በኩል ኳስን በመቆጣጠር ተጭነው ለመጫወት ጥረት ያደረጉ ሲሆን ሱራፌል ዳኛቸው ላይ ተመስርተው እድሎችን መፍጠር ቢችሉም በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጅማው ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ በኢዙ እና ሱራፌል የተሰነዘሩበትን ሙከራዎች አምክኗል። በተጨማሪም ከፋሲሎች የሜዳ ክፍል ከቅጣት ምት በረጅሙ ወደ ጎል የተሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም ሳይታሰብ ከተከላካዮች መሐል አግኝቶ መትቶ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጣበት እንጂ ጥሩ የጎል አጋጣሚ ነበር።

ዐፄዎቹ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ በቻሉበት በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም ሳይቆዩ ከመሐል ሜዳ ኢዙ ኡዙካ እና ሱራፌል ዳኛቸው በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ካለፉ በኋላ አዙካ በመጨረሻም ወደ ግብ ክልሉ ገብቶ በግራ እግሩ ወደ ጎል የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ፋሲሎች ኳሱን ይዞ ለመጫወት ጥረት በሚደርጉበት ወቅት ጥሩ በነበረው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው በጀሚል ያዕቆብ አማካኝነት ጥሩ የጎል አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ፋሲሎች ሱራፌል ዳኛቸውን በጉዳት በማስተናገዱ ሊቀይሩት ሲገደዱ ከቅያሬው በኋላ የጨዋታውንም እንቅስቃሴ ቀጥተኛ በማድረግ ሙጂብ ቃሲም የግብ እድሎችን እንዲያገኝ ያደረጉት ጥረት ባይቀናቸውም በርካታ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ፋሲሎች በዚህ መንገድ ጫና ፈጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ጅማ አባጅፋሮች ከግብ ክልላቸው ለማራቅ ተከላካዮች የመቱትን ኳስ መሐመድ ያኩቡ አግኝቶ ጥሩ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በመልሶ ማጥቃት የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት እየፈተናቸው ባሉበት ሁኔታ ፋሲሎችን መሪ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ በ87ኛው ደቂቃ አግኝተው ነበር። ኢዙ አዙካ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ጎል የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ በመውጣት ለዐፄዎቹ የምታስቆጭ የጎል አጋጣሚ ሆና አልፋለች። ጨዋታው በሁለቱም ቡድን በኩል ጎል ሳይስተናግድ ያለ ግብ ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ