የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-0 ፋሲል ከነማ

ከዛሬ ጨዋታዎች መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ላይ ተካሂዶ ያለግብ ከተጠናቀቀው የጅማ አባ ጅፋር እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።


👉 ” በሁለቱም በኩል ዕልህ አስጨራሽ እና አጓጊ ጨዋታ የታየበት ነበር ” ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባ ጅፋር)

ስለጨዋታው

ለዋንጫ ከሚጫወት ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው። የኛ ተጫዋቾች ወጣቶች ናቸው። ነገር ግን በሁለቱም በኩል ዕልህ አስጨራሽ እና አጓጊ ጨዋታ የታየበት ነበር። ወጣቶቹ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ እንደሆኑም የታየበት ነው። እነዚህን ተጫዋቾች ተንከባክቦ መያዝ ያስፈልጋል። እኔም ደጋፊውን ለማስደስት የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ከጎኑ ነኝ።

ከደጋፊው ስለተሰማው ተቃውሞ

እኔ ‘ደክሞኛል’ ብላችሁ ደስ ይለኛል። ቡድኑን እያዘጋጀው ነው። የአስተዳደሩን ጉዳይ እናንተ ገብታችሁ ጠይቁ። ሜዳ ላይ የሚታየው ግን ተስፋ ሰጪ ነገር ነው። ይህ ቡድን በደንብ ተይዞ በሚቀጥለው አራት አምስት ተጫዋቾች ተጨምረውበት የጅማ ልጆችንም አካተን ለቀጣይ መዘጋጀት ይገባናል። ፍራቻዬ ግን በቀጣይ ብዙ ልጆችን የምንቀማ ይመስለኛል ፤ ምክንያቱም የተዘጋጀነው ነገር የለም። ስለዚህ የተለፋው ልፋት በከንቱ እንዳይቀር መሰራት አለበት። እንደ ባህር ዳር ሁሉ 13 ልጅ ነው ከጅማ የያዝኩት። ህዝቡ ደግሞ የራሱን ልጆች ሲያይ ደስተኛ ይሆናል።

👉 ” ዛሬ ትልቁ ድክመታችን አጨራረስ ላይ ነበር ” ስዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ስለጨዋታው

የምንፈልገውን ነገር ለማድረግ ሞክረናል ፤ ምክንያቱም እስካሁን ከሜዳ ውጪ አላሸነፍንም። ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ ሙሉ ዝግጅታችን ነበር። ዛሬ ትልቁ ድክመታችን አጨራረስ ላይ ነበር። አራት እና አምስት የሚሆኑ መቶ ፐርሰንት ሊገቡ የሚችሉ ኳሶች አጋጥመውን ነበር ፤ አልተሳካም። በአጠቃላይ ግን ቡድኔ ጥሩ ውሎ ነው ያደረገው።

ከሜዳ ውጪ ስላለው ያለማሸነፍ ችግር

የስነልቡና ችግር ባንለውም ተጫዋቾቼ ከሜዳ ውጪ ጨዋታችንን እናሳምራለን ወይንም እናሸንፋለን ሲሉ የራሱ ጫና ይፈጥራል። ማድረግ የሚገባንን አድርገናል። በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ የኳስ ቁጥጥር ነበረን። አጨራረስ ላይ ግን ብዙ ኳሶችን ስተናል። ይህን እንደ ዕድል ከመመልከት ውጪ ሌላ አማርጭ የለም።

ስለ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም

ስታድየሙ በጣም ደስ ይላል ፤ ሜዳውም በጣም ጥሩ ነው። ሳሩ ራሱ ከዚህ የበለጠ ጥሩ መሆን የሚችል ይመስለኛል። በአጠቃላይ ለጨዋታ ምቹ እና ለተመልካችም ደስ የሚል ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ