ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ወልዋሎ

በነገው ዕለት በብቸኝነት የሚደረገው የሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፈው በአንዱ ብቻ ያሸነፉት ሲዳማ ቡናዎች ከአስከፊው ጉዟቸው ለመውጣት ሦስት ነጥብን አልመው የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ።

የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

በፈጣን የፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው መሰረት ያደረገ አጨዋወት የሚከተሉት ሲዳማዎች ባለፉት ጨዋታዎች የከፋ እንቅስቃሴ ባያሳዩም የቡድኑ ግብ ማስቆጠር አቅም ማነስ እና የተከላካዮች ስህተት ለውጤት መዋዠቁ እንደዋነኛ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ባለፈው የውድድር ዓመት ውጤታማ የነበረው የቡድኑ የመስመር አጨዋወት የሚፈጥራቸው ንፁህ የግብ ዕድሎች መመናመንም ቡድኑ እንደሚፈለገው ግብ እንዳያስቆጥር አድርጎታል።

ባለፉት ጨዋታዎች እንደ አማካይ ተጫዋቾቻቸው ምርጫ የሚቀያየር አጨዋወት መርጠው የገቡት አሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ በነገው የሜዳቸው ጨዋታ ኳስን ተቆጣጥሮ በመስመሮች ለማጥቃት አልመው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ ተብሎ ሲጠበቅ ቡድኑ በመከላከል ላይ ያለው ደካማ ጎንም ፈቶ ወደ ጨዋታው መቅረብ ይጠበቅበታል።

ሲዳማ ቡናዎች በነገው ጨዋታ መሳይ አያኖ በልምምድ ላይ በደረሰበት ጉዳት እና ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ወንድሜነህ ዓይናለም እና ሚልዮን ሰለሞንን አገልግሎት አያገኙም።
የአጥቂው ሙሉቀን ታሪኩ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ

ባለፉት ጨዋታች የወጥነት ችግር የታየባቸው ወልዋሎዎች ከደረጃው ሰንጠረኙ አናት ላለመራቅ ከዚህ ወሳኝ ጨዋታ ነጥብ ይዘው መውጣት ይጠበቅባቸዋል።

በተጫዋቾች ጉዳት ስብስባቸው የተመናመነው ቢጫ ለባሾቹ ከቋሚ አሰላለፋቸው አራት ተጫዋቾች በጉዳት ማጣታቸው ለአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መጥፎ ዜና ነው። ጠባብ የተጫዋቾች ምርጫ ያላቸው ሲሆን ምንም እንም እንኳ በመሰረታዊ የቡድኑ አጨዋወት ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ባይጠበቅም በወሳኝ ተጫዋቾቹ ጉዳት ምክንያት በቋሚ አሰላለፋቸው ለውጦች ለማድረግ ይገደዳሉ።

ከጥቂት ጊዜያት በኃላ ባልተለመደ መልኩ ከሜዳቸው ውጭ በሚያደጓቸው ጨዋታዎች ከጠጣሩ አቀራረብ ወጥተው በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ማጥቃት ያዘነበለ ቡድን ይዘው በመቅረብ የሚገኘት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በነገው ጨዋታም በአጨዋወቱ ብዙም ለውጥ ሳያደርጉ በተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድሎች ይፈጥራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ፈጣኖቹን የሲዳማ አጥቂዎች እንቅስቃሴ ለመግታት ከባለፉት ጨዋታዎች በተሻለ ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን ይሰጣሉ ተብሎ ይገመታል።

ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ ዓብዱልዓዚዝ ኬታ ፣ አይናለም ኃይሉ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ፍቃዱ ደነቀን በጉዳት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት 

– በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል። ሲዳማ አምስት ሲያስቆጥር ወልዋሎ አንድ ማስቆጠር ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ዮናታን ፍሰሃ – ሰንደይ ሙቱኩ – ግርማ በቀለ – ተስፉ ኤልያስ

ዳዊት ተፈራ – ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየሁ ዮሐንስ –

አዲስ ግደይ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ወልዋሎ (4-2-3-1)

ጃፋር ደሊል

ምስጋናው ወልደዮሐንስ – ዳዊት ወርቁ – አቼምፖንግ አሞስ – ሄኖክ መርሹ

ገናናው ረጋሳ – ሳሙኤል ዮሐንስ

ኢታሙና ኬይሙኔ – ራምኬል ሎል – ሰመረ ሀፍታይ

ጁንያስ ናንጂቡ


© ሶከር ኢትዮጵያ