የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ በትናንትናው ዕለት ተደርጎ ፈረሰኞቹ ሙሉዓለም መስፍን ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ከማሸነፋቸው ባሻገር ከመሪው መቐለ በሁለት ነጥቦች አንሰው እየተከተሉ ይገኛሉ። ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጣ ወዲህ በሸገር ደርቢ ላይ ዳግም ጎል ማስቆጠር የቻለው ሙሉዓለም መስፍን ስለ ጨዋታው እና በሸገር ደርቢ ጎል ማስቆጠሩ የፈጠረበትን ስሜት አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
የሸገር ደርቢው ጨዋታው እንዴት ነበር ?
እንዳየኸው የእነርሱ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ነበር። እኛ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እነርሱን ለማገኝት ነበር አቅደን የገባነው። ከእረፍት በፊት የእኛ ተጫዋች የተወሰነ የጎል ዕድል አግኝተው ነበር። ከእረፍት በኃላ እኛ በመልሶ ማጥቃት የተሻሉ እድሎች መፍጠር በመቻላችን ጎልም አስቆጥረን አሸንፈን ወጥተናል። በአጠቃላይ ከመቼው ምጊዜ በተሻለ የኳስ ፍሰቱ ያማረ ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ነበር።
ካቻምና በሸገር ደርቢ ላይ ጎል ማስቆጠርህ ይታወሳል። ትናትም በተመሳሳይ ጎል አስቆጥረሀል እንዴት ነው ሸገር ደርቢ ላይ ጎል የማስቆጠር ገድ አለህ ማለት ነው ?
የትኛውም ጨዋታ ላይ ወደ ሜዳ ስገባ ጎል ለማስቆጠር አስቤ ነው። ሸገር ደርቢ ላይ ጎል ማስቆጠሬ አጋጣሚ ነው ብዬ ነው የምወስደው። ፈጣሪ ይመሰግን ደርቢ ላይ ጎል ስታስቆጥር የተሻለ ስሜት ይኖረዋል። ሸገር ደርቢ ላይ ጎል ማስቆጠር ከየትኛውም ክለብ ከምታስቆጥረው ጎል ይለያል። በዚህም በጣም ደስ ብሎኛል።
የዘንድሮ ጊዮርጊስ ከሊጉ ዋንጫ ከራቀ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። ዘንድሮስ የደጋፊውን የዋንጫ
ጥም ለማርካት እንደ ቡድን ምን ታስባላቹ ?
አሁን ላይ ሆነን እንዲህ ነው ማለት የሚቻልበት ጊዜ አይደለም። ገና ሁለተኛው ዙር አልተጀመረም። ቢሆንም የትናንቱ ድል ለእኛ በጣም ትልቅ ውጤት ነው። በቡድኑ ውስጥ የሚፈጥረው መነቃቃት ከፍተኛ ነው። ከመሪዎቹ ጋር የተቀራረብንበት ውጤት አስመዝግበናል። አሁን ከዋንጫው ፉክክር ውስጥ ነን። በዚህ መንገድ እየቀጠልን እንሄዳለን።
ከሜዳ ውጭ ሦስት ነጥብ እስካሁን ማሳካት አልቻላችሁም። ይህ በቀጣይ ይቀረፋል ?
አዎ በሚቀጥለው ጨዋታዎች ይቀረፋሉ ብዬ አስባለው። ምክንያቱም እስካሁን ባሉ ከሜዳ ውጭ ጨዋታዎች የሜዳ አለመመቸት እና ሌሎች ችግሮች ውጤት ይዘን እንዳንወጣ አሉታዊ ተፅእኖዎች ነበሩ። ሀዋሳ ላይ ብዙ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለን ያለመጠቀም ሁኔታ ነበር። እንደ ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ዓይነት ሜዳ ላይ ጎል ማስቆጠር ከባድ ነው። በዚህ አጋጣሚ ስለ አዲስ አበባ ስታዲየም መናገር እፈልጋለው። ቅሬታ ከምታቀርብባቸው የክልል ሜዳዎች የባሰ እየሆነ መጥቷል። ምንም ዓይነት ክትትል እየተደረገበት አይደለም። ሜዳው ደረቅ ድንጋይ እየሆነ ይገኛል። በዚህ ደረቅ ሜዳ ላይ በሦስት ቀን አንዴ እየተጫወትን እየተቀጠቀጠ ለተለያዮ ጉዳቶች እየተዳረገ ይገኛል። ፌዴሬሽኑ ተመልካች ጥሩ ጨዋታ አይቶ እንዲዝናና ይህን ሜዳ መንከባከብ አለበት ወይም ለአዲስ አበባ ክለቦች ለኢትዮጵያ ቡና እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳውን መስጠት ቢቻል አሪፍ ነው።
በመጨረሻም ለትውልድ ከተማህ ክለብ የትጥቅ ድጋፍ አድርገሀል ይህን በጎ ተግባርህን እንዴት ትገልፀዋለህ?
ጨንቻ ተወልጄ፣ ተምሬ ያደኩበት እና እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት አካባቢዬ ነው። ይህን ማድረግ ደግሞ ግዴታዬ ነው። በዚህ ክለብ እየተጫወቱ እኔ የደረስኩበት ደረጃ ለመድረስ እያሰቡ ያሉ ተጫዋቾች ከጎናቸው ሰው እንዲቆምላቸው ይፈልጋሉ። ዝም ብለህ እየሄድክ በምክር ብቻ ማለፍ በቂ አይደለም። በአንዳንድ ነገሮች መርዳት ያስፈልጋል። ይሄም ግዴታዬ በመሆኑ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጌያለው። በመቀጠልም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ያቀድኳቸው ነገሮች አሉ ከቡድኑ ጎን በመሆን በቀጣይነትም ብዙ ድጋፍ አደርጋለው ብዬ አምናለው።
በጋሞ ጨንቻ ስለሚጫወተው ታናሽ ወንድምህ ትንሽ ነገር በለኝ
አዎ ቡድኑ ውስጥ እስካሁን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። ባቱ ላይ ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ ጥሩ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ አይተኸዋል። ወጣት ተጫዋች እንደመሆኑ መጠን ጠንክሮ በመስራት ወደ ፊት ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለው።
© ሶከር ኢትዮጵያ