ፕሪሚየር ሊጉ ከአንድ ሳምንት እረፍት በኋላ ከነገ እስከ እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከ1 ሳምንት እረፍት በኋላ ከረቡዕ እስከ እሁድ ድረስ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል፡፡ አመዛኞቹ ክለቦች በሳምንቱ አጋማሽ የኢትዮጵያ ሊግ ዋንጫ ጨዋታ በማድረግ ሲያሳልፉ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ውድድራቸውን አካሂደዋል፡፡

የ10ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም በሚደረጉ 2 ጨዋታዎች ይጀመራሉ፡፡ በአዳማ ከተማ በመለያ ምቶች ተሸንፎ ከ1ኛው ዙር የሊግ ዋንጫ የተሰናበተው ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ በንግድ ባንክ 3-0 ተሸንፎ ከውድድር ውጭ የሆነው ድሬዳዋ ከተማን 9፡00 ላይ ይገጥማል፡፡ ኤሌክትሪክ ዋና አሰልጣኙ ብርሃኑ ባዬ እና አምበሉ አዲስ ነጋሽን በቅጣት በማጣቱ በረዳት አሰልጣኙ እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያለፉትን ተከታታይ ጨዋታዎች ያልተሰለፈው ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ሊመለስ ይችላል፡፡

በ11፡30 ደደቢት ሀዋሳ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ ደደቢት ሳምንቱን ካለ ጨዋታ ያሳለፈ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ በሳምንቱ አጋማሽ ባደረገው የሊግ ዋንጫ በአርባምንጭ ከተማ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ ደደቢት በቅርቡ ያስፈረማቸው ሁለቱ ጋናዊያን ተጫዋቾች የስራ ፈቃዳቸው ባለመጠናቀቁ እንደማይሰለፉ ታውቋል፡፡ በሀዋሳ ከተማ በኩል ያለፉትን ጨዋታዎች በጉዳት ያልተጫወተው አንጋፋው አማካይ ሙሉጌታ ምህረት ወደ ሜዳ ተመልሷል፡፡

ውድድሩ ሀሙስ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል አርባምንጭ ከተማ ሁለተኛ ተከታታይ የሊግ ጨዋታውን በሜዳው ያደርጋል፡፡ አርባምንጭ ዳሽንን በ9፡00 በሚያስተናግድበት ጨዋታ በግል ጉዳይ የመጨረሻውን ጨዋታ ማድረግ ያልቻለው የአምበሉ በረከት ቦጋለን ግልጋሎት ያገኛል፡፡ በተከታታይ 3 ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው የጎንደሩ ክለብ ቁልቁል ጉዞውን እልባት ለማበጀት ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡

Ethpl Fixture

11፡30 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል፡፡ ሁለቱም ክለቦች ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ያደረጉትን የሊግ ዋንጫ ጨዋታ አሸንፈው ወደ ተከታይ ዙር ማለፍ የቻሉ ሲሆን ሲዳማ ወደ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት ኢትዮጵያ ቡናም ከወገብ በታች የተቀመጠበትን ደረጃ ለማሻሻል ፍልሚያቸውን ያደርጋሉ፡፡ ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከሜዳ ርቆ የቆየው ግብ ጠባቂው ሃሪሰን አገግሞ ልምምድ ማድረግ ከጀመረ ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን ትላንት ባደረጉት የእርስ በእርስ ጨዋታ ላይም በመጀመርያ ተሰላፊዎቹ በኩል ተጫውቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት የሊግ መሪነቱን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያስረከበው አዳማ ከተማ ቅዳሜ በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል፡፡ ስራቸውን ሊለቁ ተቃርበው የነበሩት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ዛሬ ወደ ስራቸው መመለሳቸው ለአዳማ ከተማ መልካም ዜና ሲሆን ቀላል ጉዳት አስተናግደው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው የሊግ ዋንጫ ጨዋታ ላይ መሰለፍ ያልቻሉት የሀዲያ ሆሳዕና ቁልፍ ተጫዋቾች አበባየሁ ዮሃንስ እና ዱላ ሙላቱ ለቅዳሜው ጨዋታ እንደሚደርሱ መረጋገጡ ለሆሳዕናው ክለብ እፎይታ ፈጥሯል፡፡

መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ የክለብ ውድድሮች መልስ እሁድ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ መከላከያ በ9፡00 ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በሊግ ዋንጫው 1ኛ ዙር ቢደለደሉም መከላከያ በነበረበት የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት በዚህ ሳምንት ጨዋታ ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡ ሁለቱ የቀድሞ የወላይታ ድቻ ኮከቦች ባዬ ገዛኸኝ እና አዲሱ ተስፋዬ በመከላከያ ማልያ የቀድሞ ክለባቸውን ለመጀመርያ ጊዜ ይገጥማሉ፡፡

በ11፡30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋለማሉ፡፡ ፈረሰኞቹ ከእሁዱ የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ በኋላ የ2 ቀን እረፍት ለተጫዋቾቻቸው የሰጡ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የተቆናጠጡትን የሊግ መሪነት ለማስጠበቅ ይጫወታሉ፡፡ ንግድ ባንኮች ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማን 3-0 በማሸነፍ የውድድር ዘመናቸውን ምርጥ አቋም አሳይተዋል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

EthPL standing

የከፍተኛ ግብ አግቢዎች ደረጃ

Top Scorers

ያጋሩ