ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ወልዋሎን ረመረመ

በአስራ አንደኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በሜዳው ወልዋሎን ጋብዞ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 5ለ0 በማሸነፍ ከተከታታይ ድል አልባ ጉዞ በኋላ ወሳኝ ሦስተ ነጥቦች ሰብስቧል፡፡

ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ከሜዳቸው ውጪ በፋሲል ከነማ ሽንፈትን ካስተናገዱበት ስብስብ ውስጥ ሰንደይ ሙቱኩን በአበባየው ዮሐንስ ሲለውጡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በሜዳቸው ነጥብ የተጋሩት ወልዋሎዎች በበኩላቸው እንደ ሲዳማ ቡና የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰመረ ሀፍታይን ወደ ተጠባባቂ አውርደው በምትኩ ብሩክ ሰሙን ተቀዳሚ ተመራጭ በማድረግ ተጠቅመዋል፡፡

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በባህር ዳር ሽንፈት ሲያስተናግዱ የዲሲፕሊን ጥሰት አሳይተዋል በሚል በተላለፈባቸው የአምስት ጨዋታ ቅጣት ምክንያት የዛሬውን ጨዋታ የመምራት አጋጣሚ ሳያገኙ የቀሩ ሲሆን በምትኩ በረዳት አሰልጣኙ ኪዳኔ ሀፍተ እየተመሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ የሲዳማ ቡና የማጥቃትም ሆነ የመከላከል አደረጃጀት ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር ፍፁም ተስተካክሎ በቀረበበት በዛሬው ጨዋታ በተጋጣሚው ላይ ብልጫን ያሳየ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ ተጋጣሚው ወልዋሎ የመረጠው ተሻጋሪ ኳሶችን መጠቀም ላይ ለሲዳማ ቡና አስጊ ከመሆን ይልቅ ቀለው መቅረባቸው ላሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ ተጠቃሹ አጨዋወታቸው ነው፡፡ 

8ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ተከላካይነቱ ወደ መሐል ገብቶ ሲጫወት የነበረው የወልዋሎው አምበል ሳሙኤል ዮሐንስ ከመሐል ወደ ግብ ያሻገራትን ኳስ ኢታሙና ኪሙኒ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በወጣችበት አጋጣሚ ወደ ሲዳማ ግብ ክልል ለመጠጋት ቢሞክሩም መሀላቸውን ለሲዳማ ቡና ገላልጠው ማቅረባቸው እንደ ጉድ ሲፈነጩ ለነበሩት የሲዳማ ቡና የአማካይ ክፍል የተመቹ ነበሩ፡፡

ቀስ በቀስ የጨዋታው መንፈስ እየጋለ ሲመጣ የሲዳማ ቡና የመሐል አማካዮች ዳዊት ተፈራ እና አበባየው ዮሐንስ ጥምረት ድንቅ የነበረ ሲሆን ከፊት ለተደረደሩት የሲዳማ አጥቂዎች ሀብታሙ ገዛኸኝ፣ አዲስ ግደይ እና ይገዙ ቦጋለ መሀል ለመሀል አሾልከው ሲልኳቸው የነበሩት ድንቅ ኳሶች በወልዋሎ ግብ ክልል በተደጋጋሚ እንዲገኙ አስችሏቸዋል፡፡ 10ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ዳዊት ተፈራ በተደጋጋሚ ሲዳማዎች ሲያጠቁበት በነበረው ቀኝ መስመር ላይ ለሀብታሙ ገዛኸኝ ሰቶት ፈጣኑ አጥቂም ክፍት አጋጣሚን ተረጋግቶ ማስቆጠር እየቻለ ኳሷን ተዋክቦ ሲመታት አቅጣጫዋን ስታ ወጥታለች፡፡ 

የዳዊት ተፈራን ብቃት ለመጠቀም በይበልጥ ወደ አጥቂ መስመሩ እንዲጠጋ አበባየውን ደግሞ ከጀርባው አድርገው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ጥረቶች አሁንም ያልተለያቸው ቡናማዎቹ በርካታ ኳሶችን ከአማካዮቻቸው መነሾ አድርገው ወደ መስመር በመለጠጥም ሆነ ከፊት ለተሰለፈው ይገዙ ቦጋለ ቢጥሉም የአጨራረስ ክፍተት ያገኞቸውን መልካም አጋጣሚዎች በጊዜ ወደ ግብነት እንዳይለውጡ ያደረጋቸው ዕክል ነበር፡፡

በሲዳማ ቡና ለመበለጥ የተገደዱት ወልዋሎዎች ኳስ እግራቸው ስር ስትገባ በቶሎ ከፊት ለነበሩት ሁለቱ የውጪ ዜጋ አጥቂዎች ለመጣል ቢያልሙም ከወትሮ ለጠጠረው የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ከባዶች አልነበሩም፡፡ በግል አምበሉ ሳሙኤል ዮሐንስ ከሚያደርገው አመርቂ እንቅስቃሴ ውጪ እንደ ቡድን ይዘው የገቡት አቀራረብ አዋጭ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ 

21ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከል አቋቋም ስህተት የታየበት እና የሲዳማ ቡና አስደናቂ የአጨራረስ አቅም የታየበት ግብ ተቆጥሯል፡፡ ከተከላካዩ ምስጋናው ወልደዮሐንስ እግር ስር ይገዙ ቦጋለ በፍጥነት ነጥቆ ለአዲስ ግደይ ሲሰጠው አምበሉም ወደ ሳጥን እየገፋ በመግባት በግራ አቅጣጫ ለነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ሰቶት ሀብታሙም በግራ በኩል ከሳጥን ውጪ እጅግ ግሩም ግብ በጃፋር ደሊል መረብ ላይ አሳርፎ ባለሜዳውን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

ከግቧ በኃላ ለተጨማሪ ግብ በወልዋሎ የግብ ክልል ሲያነፈንፉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በተለይ ከዳዊት ተፈራ በሚነሱ ኳሶች ጥቃት ከመሰንዘር ወደኃላ አላሉም። ራሱ ዳዊት ከርቀት መቶ ግብ ጠባቂው ጃፈር ደሊል የያዘበት፤ አዲስ ግደይ ያቀበለውን እና ሀብታሙ ገዛኸኝ መቶ ሳይጠቀምበት የቀረበት ክስተትም ሌላው ግብ ሊያገኙ የሚችሉባቸው መልካም ዕድሎች ነበሩ፡፡ በተለይ ሀብታሙ ገዛኸኝ ሁለተኛ ግቡን ሊያስቆጥር ተቃርቦ መረጋጋት ባለ መቻሉ ወደ ውጪ ኳሷ ወጥታለች፡፡ የእረፍት መውጫ ሰዓት ሲቃረብ ወልዋሎዎች በገናናው ረጋሳ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን ዕድልን ያገኙ ቢሆንም የግቡ ብረት መልሶታል፡፡

ከመልበሻ ቤት መልስ ሲዳማ ቡና ከመጀመሪያው አጋማሽ በበለጠ ጠንክሮ የገባ ሲሆን የጎል ናዳ ማውረድም ችሏል፡፡ ቢጫ ለባሾቹ 48ኛው ደቂቃ ላይ ጁኒያስ ናንጂቡ በዛሬው ጨዋታ ለወልዋሎ ብቻውን ሲታትር ለነበረው ሳሙኤል ዮሐንስ ሰጥቶት ሳሙኤልም ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ጋር ተገናኝቶ ተከላካዩ ጊት ጋት ኮች ከኃላ መቶ በብልጠት አስጥሎታል፡፡ ከዚህች ሙከራ ውጪ ረጃጅም ኳሶች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን አጨዋወታቸው ብኩን በመሆኑ ወደ ሲዳማ ግብ መጠጋት ተስኗቸዋል፡፡

59ኛው ደቂቃ ላይ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የነበሩት ሲዳማዎች ሁለተኛ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ አበባየው ዮሐንስ ከመሀል ሜዳው ጨረር ላይ ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ለነበረው ሀብታሙ ገዛኸኝ ሰቶት ሀብታሙም ወደ ሳጥን እየነዳ ገብቶ የሰጠውን አዲስ ግደይ ሁለቴ ገፋ ካደረገ በኃላ በመምታት ወደ ግብነት ለውጧት የሲዳማን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

ለወልዋሎ ተጫዋች ፋታ አልሰጥ ያሉት ቡናማዎቹ ተጨማሪ ግባቸውን 65ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም አግኝተዋል፡፡ ዮናታን ፍሰሀ በቀኝ በኩል ከወልዋሎ ተጫዋች እግር ነጥቆ ለአዲስ ግደይ ሰቶት አዲስም ወደ ሳጥን ውስጥ እየገፋ ከነጎደ በኃላ ከግቡ ትይዩ መስመር ላይ ወደ ግብ ሲልክ ይገዙ ቦጋለ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ግባቸውን ከፍ አድርገዋል፡፡ ይገዙ ግቧን ሲያስቆጥር ኳሷን የገጨበት ሁኔታ አደገኛ በመሆኑ ደስታውን ከመግለፅ ይልቅ ሜዳ ላይ ለተወሰነ ሰዓት ተኝቶ ተነስቷል፡፡ ግቦች እየበረከተባቸው የመጡት እንግዳዎቹ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ለማንሰራራት ቢያልሙም ይባሱኑ ለውጥ ሳያመጣላቸው ቀርቷል፡፡

69ኛው ደቂቃ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ዳዊት ተፈራ የወልዋሎን ተከላካይ አቋቋም ደካማነት ተመልክቶ በአቼምፓንግ አሞስ አናት ላይ ያሳለፈለትን ኳስ ሌላኛው በዛሬው ጨዋታ ድንቅ የነበረው አበባየው ዮሐንስ ወደ ግብነት ለውጧት የሲዳማን መሪነት አስፍቷል፡፡ 70ኛው ደቂቃ ላይ የማሳረጊያዋን ግብ ባለ ሜዳው አግኝቷል፡፡ ዳዊት ተፈራ መሀል ለመሀል የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ለውጧታል፡፡

አዲስ ከጎሎቹም በኋላ ተደጋጋሚ እና ሐት-ትሪክ ሊሰራ የሚችልበትን አጋጣሚዎች ቢያገኝም ማከል ሳይችል ቀርቷል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ተቀይሮ የገባው ገዛኸኝ በልጉዳ ስድስተኛ ግብ ሊያስቆጥሩ ሚችሉበትን ዕድል ካመከነ በኃላ ጨዋታ አንድም ቢጫ ካርድ ሳይታይበት 5ለ0 በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

*ጨዋታው እየተደረገ 56ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡና አጥቂዎች ሀብታሙ ገዛኸኝ እና አዲስ ግደይ ሜዳው ላይ ኳስን ለማግኘት ሲሯሯጡ እርስበርስ በመጋጨታቸው ሜዳ ላይ በወደቁበት ሰአት የሲዳማ ቡናው የህክምና ባለሙያ አበባው በለጠ (አሁንም በቀኝ እጁ ላይ ከደረሰበት ጉዳት አላገገመም) ተጫዋቾቹን ለማከም ወደ ሜዳ ከገባ በኃላ በአንድ እጁ ህክምና ሲሰጥ የተመለከቱት የወልዋሎው የህክምና ባለሙያ አታክልቲ አለነ በፍጥነት ወደ ሜዳ ገብተው ህክምና የሰጡበት መንገድ እጅግ ሊበረታታ የሚገባው መልካም ተግባር መሆኑን ተመልክተናል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ