ከፍተኛ ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ አቻ ተለያይተዋል

በመጀመርያው ሳምንት መካሄድ የነበረበት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ ተስተካካይ ጨዋታ በሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ሜዳ አዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያን አገናኝቶ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጫወት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በተሰባሰቡባቸው ሁለቱም ቡድኖች ውስጥ ጨዋታው ጎል አይቆጠርበት እንጂ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ አስመልክቶናል።

በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች መከላከያ በእንቅስቃሴ ብልጫ በመውሰድ ከፍሬው ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ወጣቱ አጥቂ አቤል ነጋሽ ወደ ጎል የሞከረው እና በኃይሉ ግርማ ከሳጥን ውጭ መቶት ግብጠባቂው ምናለ በቀለ ያዳነበት መከላከያዎች የፈጠሩት የጎል እድል ነበር።

አጀማመራቸው ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት አዲስ አበባዎች በብሩክ ተሾመ የመከላከል ብቃት፣ በተክሉ ተስፋዬ የማጥቃት እንቅስቃሴ ታግዘው መከላከያ ላይ ጫና ለማሳደር ይሞክሩ እንጂ ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አልፈጠሩም

በሁለቱ በኩል በመሐል ሜዳን ለመቆጣጠር ይደረግ የነበረው ፍትግያ የጨዋታውን እንቅስቃሴ አግሎት መከላከያዎች በረዣዥም ኳሶች ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በአዲስ አበባዎች በመከላከል ላይ የነበራቸው ትኩረት ጥሩ የነበረ በመሆኑ ወደ እረፍት መዳረሻ ላይ ሽመልስ ተገኝ ከመስመር ያሻገረውን አቤል ነጋሽ ሳይጠቀምበት የቀረውን የጎል እድል ብቻ እንድንመለከት ያደረገን።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጅማሬ ላይ አዲስ አበባዎች ከቀኝ መስመር በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ በመግባት ምንያህል ይመር በተረከዝ አገባለው ብሎ ያልተጠቀመበት ኳስ አዲስ አበባዎችን ቀዳሚ ማድረግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች።
ለተመልካች ሳቢ የነበረው እና የእያንዳንዱ ተጫዋቾች በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አስገራሚ ነበር። በተለይ በተከታታይ ሁለት የመከላከያ ጨዋታዎች ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ በመሆን ድንቅ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው ከተስፋ ቡድን ያደገው ወጣቱ አማካይ ዊልያም ሰለሞን በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ መልካም ነበር።

ፍሬው ሰለሞን ከመስመር እየተነሳ የሚፈጥራቸው እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባሉ ቢሆንም አጨራረስ ላይ የነበሩ ክፍተቶች የጎል እድሎችን እንዳንመለከት አድርጎናል። በመጨረሻም የጨዋታው መጠናቀቅ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት አዲስ አበባዎች በጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ወደ ጎል ደርሰው ተክሉ ተስፋዬ የግብጠባቂውን አቤል ማሞ አቋቋም አይቶ ወደ ጎል የመታው እና የግቡ አግዳሚ የመለሰው እጅግ ለጎል የቀረበ አዲስ አበባዎች የሚያስቆጭ ዕድል ነበር። በአፀፋው መከላከያ ከመዐዘን ምት የተሻገረውን ግብጠባቂው ምናለ የተፋውን ምንተስኖት ከበደ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው በእንቅስቃሴ አስደሳች ሆኖ ያለፈ ቢሆንም ምንም አይነት ጎል ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ