ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት | የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሠረት በማድረግ በተካሄዱት ስምንት ጨዋታዎች ላይ አንፃራዊ ጥሩ አቋም ያሳዩ 11 ተጫዋቾችን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት የተናጠል ነጥብ መነሻነት ነው። 

አሰላለፍ፡ 3-5-2


ግብ ጠባቂ

ወንድወሰን አሸናፊ (ስሑል ሽረ) 

በምንተስኖት አሎ አለመኖር ምክንያት ያገኛቸው የመሰለፍ ዕድሎችን በአግባቡ እየተጠቀመ የሚገኘው ወንድወሰን አሸናፊ በዚህ ሳምንት ጥሩ ብቃት ካሳዩ በርካታ ግብ ጠባቂዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ከጉዳቱ ብዙም ሳያገግም ወደ ሜዳ የተመለሰው ይህ ግብጠባቂ ከመሪው መቐለ በነበረው ጨዋታ ምንም እንኳ ቡድኑ ቢሸነፍም በጨዋታው ፍፁም ቅጣት ምት ከመመለሱም በተጨማሪ ሁለት ውጤት ቀያሪ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎች አምክኗል።

ተከላካዮች

ደስታ ደሙ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ፈረሰኞቹን በክረምቱ ከተቀላቀለ ወዲህ በቂ የመሰለፍ እድል ባያገኘም በቅርብ ጨዋታዎች በተሰጡት እድሎች ግን ብቃቱን እያስመሰከረ ይገኛል። ከተፈጥሯዊ የመሀል ተከላካይነት ሚና ወደ መስመር ተከላካይነት ተገፍቶ እየተጫወተ የሚገኘው ደስታ ደሙ ቡድኑ ቡናን ሲረታ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ ችሏል። በማጥቃቱ ላይ ከመሳተፍም በዘለለ በእሱ መስመር ሲሰነዘሩ የነበሩ ጥቃቶችን የሚመክትበት እንዲሁም ኳስን መልሶ ቡድኑ እንዲያገኝ ያደርግ የነበረው ጥረት ከሳምንቱ ምርጥ ሦስት ተከላካዮች አንደኛው እንዲሆን አስችሎታል። 


መላኩ ወልዴ (ጅማ አባ ጅፋር)

ለወትሮም ቢሆን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ባለው የቡድን ግንባታቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ስብስብ ውስጥ ከጨዋታ ጨዋታ ጥሩ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ተከላካዩ ቡድኑ በሜዳው በፋሲል ከተማ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን በመመከት በኩል ጥሩ ቀን አሳልፏል። የተከላካይ መስመሩን የሚመራበት እና ከሌሎች የመከላከል አጋሮቹ ጋር የነበረው መልካም መናበብም ለመጀመርያ ጊዜ በምርጥ 11 ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል።


ሚኪያስ ግርማ (ባህር ዳር ከተማ)

በመጀመርያዎቹ ሳምንታት የቀድሞ አቋሙን ለማግኘት ሲቸገር የነበረው ሚኪያስ ግርማ ቡድኑ በሜዳው አዳማ ከተማን ሲያሸንፍ የነበረው አቋም ድንቅ ነበር። ተጫዋቹ የቡድኑን (በተለይ የግራ) የመስመር ላይ ሚዛን ከመጠበቁ በተጨማሪ ይታይበት የነበረው የማሸነፍ ወኔ እና የመጫወት ፍላጎት የሚያስደንቅ ነበር። ጨዋታው ሲጀምር በግራ መስመር በኩል የተሰለፈው ሚኪያስ በተለያዩ 3 አጋጣሚዎች በተቃራኒ መስመር በመጫወት ጥሩ ግልጋሎቱን ለቡድኑ አበርክቷል። ይህንን ተከትሎ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተካቷል።

አማካዮች

አዳነ ግርማ (ወልቂጤ ከተማ)

አንጋፋው የቡድኑ ተጫዋች እና ምክትል አሰልጣኝ ቡድኑ ተከታታይ ጨዋታ እንዲያሸንፍ ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል። በተሰለፈበት የአማካይ ስፍራ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ቡድኑ ሚዛናዊ እንዲሆን አስተዋፅኦ ከማበርከቱ በተጨማሪ የቡድኑን ማጥቃት በማስጀመር በኩል መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል። ከአንደኛው ሳምንት በኋላም ዳግም ወደ ምርጥ 11 ተመልሷል።


አበባየሁ ዮሐንስ (ሲዳማ ቡና)

ዛሬ ሲዳማ ቡና ወልዋሎን በሰፊ ግብ ባሸነፈበት ጨዋታ ቡድኑ ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር ላይ ወሳኝ ሚና ሲወጣ ውሏል። ከአማካይ ክፍል አጣማሪው ዳዊት ተፈራ ጋር በጥሩ ተግባቦት የመሐል ክፍሉን የመራው አበባየሁ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በተደጋጋሚ ከማድረስ በተጨማሪ አንድ ጎል በጨዋታው ማስቆጠር ችሏል። 


ግርማ ዲሳሳ (ባህር ዳር ከተማ)

ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን እያስመለከተ የሚገኘው ግርማ የባህር ዳር ከተማ ሁነኛ የማጥቂያ መሳሪያ እየሆነ መጥቷል። ፍጥነቱን እና ክህሎቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ጥሩ የሆኑት ተጨዋቹ በትላንቱ የባህር ዳር ከተማ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ነበር። በጨዋታውም ቡድኑን አሸናፊ ያደረጉ 2 ኳሶች በማመቻቸት ጥሩ ጊዜን አሳልፏል። ይህንን ተከትሎ ተጨዋቹ ለሦስተኛ ጊዜ የሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።


ዳዊት ተፈራ (ሲዳማ ቡና)

ከዕለት ወደ ዕለት እየበሰሉ ከመጡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀሰው ዳዊት ተፈራ ሲዳማ ቡና ዛሴ በሜዳው ወልዋሎን ሲያሸንፍ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በአግባቡ ሲዘውር ውሏል። ከእግሩ የሚነሱ ኳሶች እና የሚፈጥራቸው የጎል እድሎች ለወልዋሎ አደጋ ሲሆኑ የተስተዋለ ሲሆን ከተቆጠሩ ጎሎችም በሁለቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።


አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)

ሲዳማ ቡና ወደ አሸናፊነት በተመለሰበት ጨዋታ በፊት መስመር አስፈሪ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ውሏል። ፈጣኑ የመስመር አጥቂ የወልዋሎን የተከላካይ ክፍል ከመረበሽ አንስቶ ሁለት ግሩም ግቦችን በጨዋታው አስቆጥሯል፡፡ ተጫዋቹ ግብ ከማስቆጠሩ ባለፈ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በሜዳ ላይ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት ከህመሙ ጋር እየታገለ ለቡድኑ ወሳኝ ድል መገኘት ተጠቃሽ ተጫዋች ሊሆን ችሏል፡፡ 

አጥቂዎች

ሙህዲን ሙሳ (ድሬዳዋ ከተማ)

ወጣቱ አጥቂ ዘንድሮ በተለይም በዚህ ወር ያገኘውን የመሰለፍ ዕድል በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል። ቡድኑ ድደዳዋ ከተማ ሰበታ ከተማን 1-0 የረታበትን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው ሙህዲን ከጎሉ በተጨማሪ በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሷል። የሚደርሰውን ኳሶች የግል ጥረቱን በመጠቀም ወደ ግብ ክልል ይዞ በመግባት የሚፈጥራቸው የጎል እድሎች እና ከቀሪው የቡድኑ ተጫዋቾች ጋር የነበረው መግባባትም መልካም የሚባል ነበር። 


ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ባለፉት ጨዋታዎች እንዳስመለከተን ጌታነህ ከበደ በበቂ መልኮ ግቦችን እያመረተ ባይሆንም ፊት መስመር ላይ የእሱ መኖር በራሱ ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት እያስመሰከረ ይገኛል። በጨዋታው ቋሚ የመለሰበትን ኳስ ጨምሮ በርካታ ሙከራዎችን ማድረግ የቻለው ጌታነህ የትጋት ደረጃው እና የቡድን መሪነት አቅሙ እጅግ ድንቅ ነበር።

ተጠባባቂዎች

ሰዒድ ሀብታሙ (ጅማ አባ ጅፋር)

መናፍ ዐወል (አዳማ ከተማ)

ዓወት ገብረሚካኤል (ስሑል ሽረ)

ተስፋዬ አለባቸው (ሰበታ ከተማ)

ታደለ መንገሻ (ሰበታ ከተማ)

ሄኖክ አየለ (ሀዋሳ ከተማ)

ሳዲቅ ሴቾ (ወልቂጤ ከተማ)

©ሶከር ኢትዮጵያ