ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፪) | ተጫዋች ትኩረት

12ኛ ሳምንቱ ላይ በደረሰው ሊጉ በዚህኛው ሳምንት የተመለከትናቸውን ተጫዋች ነክ ጉዳዮች በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል።

👉 የጌታነህ – አቤል ጥምረት እና የፓትሪክ ማታሲ አበርክቶ 

ሁለቱ የቀድሞ የደደቢት አጥቂዎች በሰማያዊዎቹ መለያ የነበራቸውን አስደናቂ ጥምረት ያስታወሰ እንቅስቃሴ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ ላይ ዳግም አስመልክተውናል። ሁለቱ አጥቂዎች ሁለት ሁለት ግቦችን ከማስቆጠራቸው በዘለለ ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል አስደናቂ ቀንን አሳልፈዋል። 

ከሳምንት ሳምንት በቋሚነት ግብ የሚያስቆጥር አጥቂን በተለያዩ ምክንያቶች ማግኘት ያልቻሉት ፈረሰኞቹ ከጋዲሳ፣ ጌታነህ እና አቤል የፊት መስመር ጥምረት በቋሚነት ግቦችን ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ለዋንጫው ኮስታራ ተፎካካሪ የመሆናቸው ነገር አያጠያይቅም።

ሌላኛው በቅርቡ ከጉዳት መልስ የመጀመርያ ተመራጭነቱን ከባህሩ ነጋሽ ያስመለሰው ኬንያዊው የግብ ዘብ ፓትሪክ ማታሲ ግቡን ከመጠበቅ በዘለለ በማጥቃቱ ሂደት ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎዎችን ሲያደርግ ተስተውሏል። ቡናን በሸገር ደርቢ ሲረቱ በቀጥታ ከእሱ እግር በተከላካዮች ጀርባ በተጣሉ ረጃጅም ኳሶች ሶስት ጥሩ የግብ እድሎችን መፍጠር ችሎ የነበረው ማታሲ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም አቤል ላስቆጠረው አምስተኛ ግብ ኳስን በተመሳሳይ ሂደት ማሐቻቸት ችሏል። በዚህም ከግብ ጠባቂነት ክህሎቱ በዘለለ ጥሩ መሪም እንደሆነ በተደጋጋሚ እያስመሰከረ የሚገኘው ማታሲ አሁን ደግሞ ለፈረሰኞቹ ሌላ የማጥቂያ አማራጭ ይዞ የመጣ ይመስላል።

👉 ከጉዳት የተመለሱት የድቻ ተስፈኛ ተጫዋቾችና አዝናኙ ግብ ጠባቂ 

ወላይታ ድቻ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ለመጀመሪያ ጊዜ ባሸነፈበት ታሪካዊው ጨዋታ ላይ በቅርብ ዓመታት ወዲህ ከተስፋ ቡድን ያደጉትና በሂደት የዋናው ቡድን ሁነኛ ተጫዋች ለመሆን የበቁት ተስፈኞቹ እዮብ ዓለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳ እንቅስቃሴ የጎላ ነበር።

በቡድኑ ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወደ ዋናው ቡድን ያደጉት የመስመር ተጫዋቾቹ እዮብ ዓለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳ ቡድኑ ድሬዳዋን አሸንፎ እንዲወጣ የነበራቸው ሚና እጅግ ልዩ ነበር። በቅርቡ ከጉዳት የተመለሰው እዮብ የሊጉን ፈጣንዋን ግብ በመጀመሪያ አጋማሽ ጅማሮ 40ኛ ሰከንድ ላይ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ 3-0 በተጠናቀቀው ጨዋታ የቡድኑን ማሳረጊያ ግብ በ40ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል። በተጨማሪም ሌላኛው በቅርቡ ከጉዳት የተመለሰውና በመጨረሻው የሜዳቸው ጨዋታ መቀለን ሲረቱ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ አስቆጥሮ የነበረው ሌላኛው የመስመር ተጫዋች ቸርነት ጉግሳ ከእድሪስ ሰዒድ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ደምቆ በዋለበት ጨዋታ ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ጥሩ ቀንን አሳልፏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሀዋሳና አዳማ ከተማ በመቀጠል በርከት ያሉ ታዳጊ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ በጥቅም ላይ እያዋሉ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች በወጣት ተጫዋቾቻቸው ላይ እያሳደሩ ያሉት እምነት በስተመጨረሻም መልሶ እየከፈላቸው ይመስላል።

ሌላው የወላይታ ድቻው ግብጠባቂ መክብብ ደገፉ የቡድኑ እንቅስቃሴ ደከም ባለባቸው ወቅቶች የቡድኑ ደጋፊዎች ተጫዋቾችን በድጋፋቸው እንዲያበረቱና እንዲያነቃቁ በተደጋጋሚ ለቡድኑ ደጋፊዎች መልእክት ያስተላልፍበት የነበረው መንገድና የቡድኑን መሪነት ተከትሎ ያሳያቸው የነበሩ አክሮባቲክ መንገዶች በስታዲየም ለታደሙ የቡድኑ ደጋፊዎች አይረሴ ገጠመኞች ነበሩ።

👉 ኳስን አቅልሎ የሚጫወተው ፉዓድ ፈረጃ 

በ2010 የውድድር ዘመን ከተስፋ ቡድን ያደገው ፉዓድ ፈረጃ ዘንድሮ አልፎ አልፎ እያገኛቸው የሚገኙትን የጨዋታ ደቂቃዎች በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል። ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ሲረታ ምርጥ ብቃቱን ያሳየው ወጣቱ አማካይ በተለይ አብዛኛው የሀገራችን አማካዮች የሚጎድላቸውን ኳስን አቅልሎ የመጫወት ሒደት የተካነበት መስሏል።

የአዳማን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሲመራ የነበረው ፉዓድ በተለይ እጅግ አስፈላጊ በሆነው ኳስን በተቻለ ፍጥነት ከእግር የመልቀቅ ሒደት በአላስፈላጊ የጀብደኝነት ኳስ ንኪኪዎች ይባክን የነበረውን የቡድኑን የማጥቃት ሽግግር ስለማሻሻሉ የቡናው ጨዋታ ምስክር ነው። 

በብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ እስከመጠራት ያደረሰ መሻሻሎች እያሳየ የሚገኘው ተጫዋቹ በቀጣይ በቋሚነት ይህን ሂደት በማስቀጠል በክለቡ የመጀመርያ ተመራጭነት ዝርዝር ውስጥ ለመግባት ተግቶ መስራት ይኖርበታል።

👉 ጥንቁቁ ወንድሜነህ ደረጀ

ኢትዮጵያ ቡና በአዳማ በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ምንም እንኳን ሦስት ግቦችን ቢያስተናግዱም የመሀል ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጀ እንቅስቃሴ ግን ትኩረት የሚስብ ነበር። ከፊቱ የሚገኙ ክፍት የሜዳ ክፍሎችን ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት እንዲሆም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ያለው ንቃትና ቆራጥነት እጅግ አስገራሚ ነበሩ።

ከሽንፈቱ በዘለለ የኢትዮጵያ ቡናን እንቅስቃሴ ለተመለከተ በጨዋታው በብቸኝነት በኢትዮጵያ ቡና በኩል በበጎነት ሊጠቀስ የሚችለው የወንድሜነህ ደረጀ ጥረት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በዚህ ዓመት እያሳየው ከሚገኘው ወጥ አቋም አንፃር አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በቀጣይ የብሔራዊ ቡድን ጥሪያቸው ላይ መካተት ከሚገቧቸው ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።

👉 የያስር ሙገርዋ ይቅርታ

በሳምንቱ አጋማሽ መቀለ 70 እንደርታ ስሁል ሽረን በኦኪኪ ብቸኛ ግብ ባሸነፈበት የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ በ65ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ ተቀይሮ ሲወጣ ባሳየው ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጭ የሆነ ድርጊት ተቃውሞ ሲያስተናግድ ቆይቷል። ተጫዋቹ በቅርቡ ወደ ሀገሩ ዩጋንዳ ሊግ ለመመለስ ሂደት ላይ መሆኑ በስፋት ሲነገር የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በስሑል ሽረ የሚያቆየውን ውል ለመፈረም በድርድር ላይ ስለመሆኑ ታውቋል።

ይቅርታ መጠየቅ በሀገራችን እግርኳስ በስፋት ያልተለመደ ቢሆንም ተጫዋቹ በድርጊቱ ተፀፅቶ ይቅርታ መጠየቁ ሊያስመሰግነው የሚገባ ነው። በሌላ ጎኑ ደግሞ ሒደቱ ከውል እደሳው ጋር በተቀራራቢ ጊዜ መሆኑ ከይቅርታው በስተጀርባ በሽረ የሚኖረው ቆይታን ከማርዘሙ ጋር ሊገናኝ እንደሚችልም ይጠረጠራል።

👉 አህመድ ሁሴን በስተመጨረሻም በሊጉ ግብ አስቆጥሯል

ዐምና በከፍተኛ ሊግ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ የሰነበተው አህመድ ሁሴን በፕሪምየር ሊጉ በቂ የመሰለፍ እድል ባያገኝም ወልቂጤ ባህር ዳር ከተማን በረታበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል። ቁመተ መለሎው አጥቂ በአየር ላይ ኳሶቹ አጠቃቀም ረገድ ጥያቄ የማይነሳበት ቢሆንም ራሱን በሊጉ ለማስተዋወቅ በእሁዱ ጨዋታ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ጥሩ መነሳሻ ይሆኑታል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ያልተወራለት የሰበታ የመስመር አጥቂና ፍፁም ገ/ማርያም 

ሰበታ ከተማ በዚህኛው ሳምንት ተቸግሮም ቢሆን ሰበታ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ የፍፁም ገ/ማርያምና ባኑ ዲያዋራ ጉዳይ ትኩረት የሚስብ ነው። ብዙም የማይነገርለት የመስመር አጥቂው ባኑ ዲያዋራ በዝምታ ውስጥም ቢሆን ለቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን በተደጋጋሚ እያስመሰከረ ይገኛል። ጥሩ ቀን ባሳለፈበት የትላንቱ ጨዋታም ከመስመር እየተነሳ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ፍፁም ላስቆጠራት ወሳኝ የማሸነፊያ ግብም ከመስመር ተጫዋቾችን ቀንሶ አመቻችቷል። 

በተያያዘ አጥቂው ፍፁምም ቡድኑም ሆነ በግሉ በእንቅስቃሴ በሚቸገሩበት ወቅትም እንኳን በአስፈላጊ ሰዓት ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር ለሰበታ ከተማ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን በድጋሚ አሳይቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ