የፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አንደኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።

👉 ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአስረኛ ሳምንት በአጠቃላይ 17 ጎሎች ተቆጥረዋል። ባለፈው ሳምንት ከተቆጠረው የጎል ብዛትም በሦስት ከፍ ማለት ችሏል። 

– በዚህ ሳምንት የጎሎቹ መጠን ካለፈው ሳምንት አንፃር መሻሻል ቢያሳይም በርካታ ጎሎች ተቆጥሮበታል ለማለት አያስደፍርም። ሲዳማ ቡና ያስቆጠራቸው አምስት ኳሶችም የጎሎች መጠን እንዳይቀንስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

– በዚህ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ብዛት ስድስት ሆኗል። ይህም ከባለፈው ሳምንት በአንድ የበለጠ ሲሆን ጎል ያላስቆጠሩት አምስቱ ቡድኖች የተጫወቱት ከሜዳቸው ውጪ ነው። አንድ ቡድን (ጅማ) ብቻ በሜዳው ተጫውቶ ያለ ጎል ጨዋታውን አገባዷል።

– በዚህ ሳምንት 16 ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። አንድ ተጫዋች ብቻ (አዲስ ግደይ) ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ቀሪዎቹ ጎሎች በ15 የተለያዩ ተጫዋቾች መቆጠር ችሏል።

– ከተቆጠሩት 17 ጎሎች መካከል 12 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 4 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥሯል። 1 ጎል ደግሞ ከተከላካይ ሥፍራ ተጫዋች ተገኝቷል።

– ከ17 ጎሎች መካከል 10 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ 6 ጎል ከቅጣት ምት እና ማዕዘን ምቶች ተሻምተው የተቆጠሩ ናቸው። አንድ ጎል ደግሞ ከፍፁም ቅጣት ምት ተገኝቷል።

– ከዚህ ሳምንት 17 ጎሎች መካከል ሰባት ጎሎች በግንባር ተገጭተው ተቆጥረዋል። ይህም በዘንድሮው ሊግ ከፍተኛ የግንባር ጎሎች የተቆጠሩበት ሳምንት ሆኖ ተመዝግቧል። ቀሪዎቹ አስር ጎሎች ደግሞ በእግር ተመትተው ተቆጥረዋል።

– ከ17 ጎሎች መካከል 16 ጎሎች ሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 1 ብቻ ከሳጥን ውጪ ተመትቶ ጎል ሆኗል።

– በዚህ ሳምንት ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች ተሰጥተው አንደኛውን የሀዲያ ሆሳዕናው ሄኖክ አርፊጮ ሲያስቆጥር አንደኛውን ደግሞ የመቐለው ኦኪኪ አፎላቢ አምክኖታል።


👉 ካርዶች

– በዚህ ሳምንት እንዳለፈው የጨዋታ ሳምንት ሁሉ ሁለት ቀይ ካርዶች ተመዘዋል። በመቐለ 70 እንደርታ እና ስሑል ሽረ መካከል በተደረገው ጨዋታ ለኦኪኪ አፎላቢ (ሁለት ቢጫ) እና ዲዲዬ ለብሪ (ቀጥታ ቀይ) ነው ሁለቱ ካርዶች የተመዘገቡት።

– በዚህ ሳምንት አምስት ቡድኖች (ወልዋሎ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ፋሲል ከነማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ሲዳማ ቡና) ምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ ያልተመለከቱ ቡድኖች ናቸው። የሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ ጨዋታም ምንም ካርድ ሳያስመለክት ተገባዷል። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማ ከፍተኛውን የማስጠንቀቂያ ካርድ (5) የተመለከተ ቡድን ሆኗል።

👉 የሲዳማ ቡና የማጥቃት ጥምረት

– በጎሎች ተንበሽብሾ የወጣው ሲዳማ ቡና የፊት መስመሩ ወደ አስፈሪነት የተመለሰ ይመስላል። በዚህ ሳምንት 5-0 ሲያሸንፉ የተቆጠሩት ሁሉም ጎሎች ላይ አጥቂው ይገዙ ቦጋለ እና ከጀርባው የተሰለፉት ሦስት ተጫዋቾች የተሳተፉባቸው ነበሩ። አዲስ ግደይ ሁለት አስቆጥሮ ሁለት ሲያመቻች ሀብታሙ ገዛኸኝ አንድ አስቆጥሮ አንድ አመቻችቷል፤ ዳዊት ተፈራ ሁለት ሲያመቻች ይገዙ ደግሞ አንድ አስቆጥሯል። 

👉 ሙሉዓለም መስፍን እና የሸገር ደርቢ

– ፈረሰኞቹ በሸገር ደርቢ ቡናን 1-0 ሲረቱ ጎል ያስቆጠረው ሙሉዓለም መስፍን በደርቢው ላይ በድጋሚ ጎል አስቆጥሯል። በ2010 በተመሳሳይ በጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ ጎል ያስቆጠረው ሙሉዓለም ባለፉት አምስት የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነቶች ላይ የተቆጠሩት ሁለቱም ጎሎች ባለቤትም ነው። 

👉 የብሩክ በየነ የጎል ተሳትፎ

– ወጣቱ አጥቂ ዘንድሮ ክስተት መሆኑን ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት ቡድኑ 2-1 ሲያሸንፍ አንድ ኳስ ያመቻቸው ብሩክ ለተከታታይ ሦስተኛ ጨዋታ በጎል ላይ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል። (2 ጎል እና 3 አሲስት)

👉 የወልቂጤ ከተማ ተከታታይ ድል

– ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 የረታው ወልቂጤ ከተማ ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል። ይህም በፕሪምየር ሊግ ታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ያሳካው ሲሆን በአንድ ጨዋታ ሁለት ጎል ሲያስቆጥርም በተመሳሳይ ለመጀመርያ ጊዜ ሆኗል።

👉 የስሑል ሽረ ሽንፈት

– ባለፉት ሰባት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ ዘልቆ የነበረው ስሑል ሽረ በዚል ሳምንት ጨዋታ በመቐለ 70 እንደርታ ሽንፈት ደርሶበታል።

👉 በዚህ ሳምንት…

– ከሜዳቸው ውጪ በተከታታይ ድል ማስመዝገብ ያልቻሉት አዳማ ከተማ (ለ16ኛ ጊዜ) እና ፋሲል ከነማ (ለ10ኛ ጊዜ) በዚህም ሳምንት ድል ሳያስመዘግቡ ተመልሰዋል። 

– በዚህ ሳምንት ሦስት ተጫዋቾች ዘንድሮ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ከጎል ጋር ተገናኝተዋል። ሙሉዓለም መስፍን (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ፍቃዱ ወርቁ (ባህር ዳር ከተማ)፣ አሳሪ አልመሐዲ (ወልቂጤ ከተማ) ለመጀመርያ ጊዜ ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በሶከር ኢትዮጵያ የሚወጡትን ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች በቀጥታም ሆነ በግብዓትነት ሲጠቀሙ ምንጭ ይጥቀሱ። 

ያጋሩ