ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፪) | ተጫዋች ትኩረት

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ አጋማሽ መከናወናቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸውን ዐበይት ክስተቶች ከተጫዋቾች አንፃር በሚከተለው መልኩ ቃኝተነዋል።👉 የውጭ ተጫዋቾች ሥነ ምግባር ጉዳይ

በሊጉ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚገኙት የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ለክለቦቹ ከሚሰጡት አበርክቶ በዘለለ ልብ ያልተባለ ነገርግን በአፋጣኝ መታረም የሚሹ የሥነምግባር ጥሰቶች በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ማስተዋል ከጀማመርን ዋል አደር ብለናል።

ለጉዳያ መነሻ ይሆነን ዘንድ በ11ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ወላይታ ድቻን ከገጠመበት ጨዋታ ጅማሮ በፊት የሀዋሳ ከተማው ግብጠባቂ ካሜሩናዊው ቤሊንጋ ኢኖህ በጨዋታው ዳኞች በጣቱ ላይ ያደረገውን የጣት ቀለበት እንዲያወልቅ ቢጠይቅም ፈቃደኛ ባለመሆኑ በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ጨዋታው ከተያዘለት የመጀመሪያ ሰዓት ለ4 ደቂቃዎች ዘግይቶ መጀመር ምክንያት ሆኗል። በተመሳሳይ እንዲሁ በ10ኛ ሳምንት የሀዋሳ ከተማው የቡድን አጋሩ ላውንረስ ላርቴ በአዲስአበባ ስታዲየም ሰበታን ሲገጥሙ ከካልሶተኒው በላይ የደረበውን ነጭ ካልሲ እንዲያወልቅ በእለቱ ዳኛ ቢነገረውም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ጨዋታው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሊስተጓጎል ችሏል። በ10ኛ ሳምንት ሀሪሰን ሄሱ ከባህርዳሩ ጨዋታ በፊት የለበሰውን ትጥቅ እንዲቀይር ቢነገረውም አሻፈረኝ በማለቱ እስከ ቀጥታ ቀይ ድረስ የደረሰው ንትርክ እንዲሁም በ11ኛ ሳምንት የስሁል ሽረው ዩጋንዳዊው አማካይ ያስር ሙገርዋ በመቐለው ጨዋታ ከደጋፊዎች ጋር በፈጠረው አለመግባባት ደጋፊዎችን ለፀብ ያነሳሳበት መንገድን ለተመለከተ በተጫዋቾቹ ዘንድ እየዳበረ የመጣው መታበይ ለሌሎች አላስፈላጊ ድርጊቶች በር ሳይከፍት መታረም ይኖርበታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የአንድ የሊጉ ተካፋይ ክለብ የውጭ ዜጋ ተጫዋች በግልፅ “ይህ ለሀገራችሁ እግርኳስ ሲበዛባችሁ ነው።” ብሎ የምፀት የሰጠው አስተያየት የሁሉንም ሀሳብ ባይወክልም በአብዛኞቹ ተጫዋች ውስጥ እየተፈጠረ የሚገኘውን የሀገራችንን የእግርኳስ ደረጃ አንኳሶ የመመልከት ነገርን በአጭሩ የሚገልፅ ነው።

ከተወሰኑ ተጫዋቾች ይልቅ በክለቦቻቸው ጉዳት ሳያጋጥማቸው በሰበብ አስባቡ ክለባቸውን የማያገለግሉ እንዲሁም በተክለ ቁመና እንጂ በሌሎች እግርኳሳዊ መመዘኛዎች ከሀገራችን ተጫዋቾች ደረጃ የማይሻሉ በደረጃቸው ዝቅ ያሉ የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ወደ ሀገራችን እየመጡ ባለበት በዚሁ ወቅት መሰል አሉታዊ ዕይታዎችና ድርጊቶች መታረም ይኖርባቸዋል።👉 ጌታነህ ከበደና ታታሪው የፈረሰኞቹ የፊት መስመር

ፈረሰኞቹ ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት የሸገር ደርቢ ጨዋታ የጌታነህ ከበደ ተፅዕኖ እጅግ የጎላ ነበር። ተጫዋቹ ምንም እንኳን የአምበልነቱን ጨርቅ በክንዱ ባያስርም ቡድኑን ይመራበት የነበረው መንገድ ትኩረት የሚስብ ነበር። በተለይም ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች አቤል ያለው እና ጋዲሳ መብራቴ ጨዋታውን በጀመሩት የትጋት መጠን ለመቀጠል በተቸገሩባቸው የጨዋታ ቅፅበቶች የሚገስፅበት እንዲሁም የቡድን አጋሮቹን የሚያበረታታበት መንገድ ፍፁም የተለየ ነበር።

በተጨማሪም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ባስመለከቱን ተስፋ ሰጪ የፕሬሲንግ አጨዋወት ውስጥ ታታሪዎቹ ሦስቱ የፈረሰኞቹ የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች አቤል፣ ጌታነህና ጋዲሳ ያሳዩት የነበረው ፍላጎት የማቀበያ አንግሎችን ይዘጉ የነበረበት መንገድና ብርታት በቀጣይ ጨዋታ የሚደገም ከሆነ ቡድኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ያራምዳል ተብሎ የሚጠበቅ ጥምረት ሊሆን ይችላል።👉 አማኑኤል ዮሐንስ ወደ ተከላካይ አማካይነት ሚና መመለስ

በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ስር ከቀደመው የ6 ቁጥርነት ሚናው በተለየ በ8 ቁጥር ሚና ሲጫወት የሰነበተው የኢትዮጵያ ቡናው አምበል አማኑኤል ዮሐንስ በረቡዕ የሸገር ደርቢ ዓለምአንተ ካሣን በመተካት በቀደመው የተከላካይ አማካይ ሚናው መልካም የሚባል የጨዋታ ጊዜን አሳልፏል።

ኳስን ከኋላ ለመመስረት በሚያስቡ ቡድኖች ላይ ኳሱን ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል የሚያደርገውን ጉዞ ላይ እንቅቃሴውን በማሳለጥ ወሳኝ ሚናን እንዲወጡ በሚጠበቅበት በዚህ አጨዋወት ለመጫወት በሚፈልገው ኢትዮጵያ ቡና ውስጥ ከአለምአንተ ካሳ በተሻለ አማኑኤል በጫና ውስጥ ሆኖም ምስረታውን የማስቀጠልና የተጋጣሚን ጥቃት በማቋረጥ ረገድ የተሻለ ስለመሆኑ የሸገር ደርቢ በቂ ምስክርነትን ሰጥቶ አልፏል።👉 የተለያየ መልክ የነበረው የጨዋታ ቀን ያሳለፈው ኦኪኪ አፎላቢ

ናይጄሪያዊው የመቐለ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ በ11ኛ ሳምንት ቡድኑ ስሑል ሽረን ሲረታ የተለያየ መልክ የነበረው የጨዋታ ቀን አሳልፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ መቐለዎችን ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኃላፊነት ወስዶ የመታት ኳስ ከመረብ ሳትዋሀድ ቀርታበታለች። በዚህም ቁጭት ውስጥ የገባው ኦኪኪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል።

ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት መቐለዎች አንድ ተጫዋቾች ገና በማለዳው ካጡት ሽረዎች ጋር ጨዋታቸውን ሊፈፅሙ ከ10 ያነሱ ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅት ኦኪኪ አፎላቢ ቡድኑ የሊጉን መሪነት ያስቀጠለበትን ወሳኝ 3 ነጥብ ያስመዘገበች ግብ ማስቆጠር ችሏል። በግቧ መቆጠር በኃላ ደስታውን ለመግለዕ መለያውን በማውለቁ ሳቢያ በተመለከተው ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።👉 የሳዲቅ ሴቾ መነሳሳት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አጥቂዎች ጥሩ ከኳስ ውጭ እንቅስቃሴ ካላቸው ጥቂት አጥቂዎች አንዱ የሆነው ሳዲቅ ሴቾ ምንም እንኳን የመጨረሻ ውሳኔዎቹ ላይ ችግሮች ቢኖሩበትም በአሁኑ ሰዓት የወልቂጤ ከተማ ወሳኝ ተጫዋች እየሆነ መጥቷል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያገኘውን በቋሚነት የመሰለፍ እድል በመጠቀምም በሁለቱም ጨዋታዎች ወሳኝ የሆኑ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። መሰል በጨዋታዎች ልዩነት መፍጠር የሚችሉ ተጫዋቾችን አጥቶ ሲንገራገጭ ለነበረው የወልቂጤ ከተማ ደካማ የማጥቃት ሀይል ሳዲቅ በመጠኑም ቢሆን እፎይታን የሰጠ ሆኗል።👉 ብዙም ሙገሳዎች የማይቸሩት ደቃቃው የሲዳማ የማጥቃት አቀጣጣይ

በሲዳማ ቡና እንቅስቃሴ ላይ ሦስቱ የፊት መስመር አጥቂዎች ከሚያስቆጥሯቸው ግቦች የተነሳ በቀዳሚነት ጎልተው ይነሱ እንጂ ከእነሱ ጀርባ ይህን ሂደት ስለሚመራው ዳዊት ተፈራ ግን ብዙም ሲወራ አይደመጥም። የፈጣን አዕምሮና የአስደናቂ ዕይታ ባለቤቱ ዳዊት በብዛት ተነጥለው የሚስተዋሉትን እነዚሁን ሦስት አጥቂዎች ከተቀረው የቡድን ክፍል ጋር በማገናኘት ረገድ ወደር የሌለው ሚና በመወጣት ላይ ይገኛል። ወልዋሎ ላይ አምስት ግቦችን ሲያዘንቡ በተለይ በተለጠጠ አቋቋም ላይ የሚገኙትን ሁለቱን የመስመር አጥቂዎች ወደ ጨዋታ የሚያስገባበት መንገድ እንዲሁም ወደፊት የሚሻልካቸው አስደናቂ ኳሶች እጅግ የተለዩ ነበሩ።👉 ሙህዲን ሙሳ እና የድሬዳዋ ወጣቶች ተስፋዎች

ዘንድሮም እንዳለፉት ጊዜያት በውጤት መንገራገጭ ውስጥ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካሉት ቡድኖች አንፃር ለወጣቶች ጥሩ እድል እየሰጠ ተጫዋቾቹም አቅማቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። ከሁለት ዓመት በፊት ከተስፋ ቡድኑ አድጎ እምብዛም በዋናው ቡድን የመጫወት እድል ያላገኘው ሙህዲን ሙሳ ዘንድሮ በተለይም ባለፉት አራት ሳምንታት የተሰጠውን የጨዋታ ጊዜ በአግባቡ በመጠቀም ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር የብርቱካናማዎቹ ተስፋ ሆኗል። ከትናንት በስቲያ ቡድኑ ሰበታን ያሸነፈበት ጎል ባለቤትም ወጣቱ አጥቂ ነው።

ሌላው በቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች እየተሰለፈ የሚገኘው የመስመር ተከላካዩ ያሲን ጀማል በጥሩ ሁኔታ ከቡድኑ ጋር በመዋሀድ ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። የመስመር ተጫዋቾቹ ያሬድ ታደሰ እና ሳሙኤል ዘሪሁን (ሳሙኤል በዚህ ሳምንት አልተጫወተም) እንዲሁም በርካታ በተጠባባቂ ወንበር ላይ የሚቀመጡ ወጣቶች በእግርኳስ የቀደመ ገናናነቷን ለመመለስ ምጥ ላይ ላለችው ድሬዳዋ መልካም ዜና ሆኗል። ከዚህም ባሻገር በከተማው ትልቅ ክለብ እድል ማግኘታቸው ለሌሎች የከተማው ወጣቶች በጎ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።


©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ