በአስራ አንደኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ወላይታ ድቻን በመጨረሻ ደቂቃ ግብ 2ለ1 የረታበት ጨዋታ ላይ አጥቂው መስፍን ታፈሰ ዳግመኛ ጉዳት የገጠመው ሲሆን እስራኤል እሸቱንም በቀጣይ ጨዋታዎች ማጣቱ እርግጥ ሆኗል፡፡
በሰባተኛው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ላይ ጉዳት የገጠመውና ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ያልነበረው አጥቂው እስራኤል እሸቱ ከጡንቻ መሳሳብ ህመሙ ለማገገም በቂ እረፍት ያስፈልገዋል በመባሉ ቢያንስ እስከ አንደኛው ዙር ፍፃሜ ክለቡን እንደማያገለግል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ሌላኛው አጥቂ መስፍን ታፈሰ ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው አቻ በተለያየበት ጨዋታ ጉዳት ካስተናገደ በኋላ ሁለት ጨዋታዎች አምልጠውት በድጋሚ 10ኛው ሳምንት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሰበታ ሲሸነፉ ግብ ካስቆጠረ በኃላ በገጠመው ጉዳት በወቅቱ በአምቡላንስ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል በማምራት ህክምናውን አድርጎ በፍጥነት በማገገም በዚህ ሳምንት ሀዋሳ በሜዳው ወላይታ ድቻን ሲረታ መጫወት ቢችልም በ68ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ ተቀይሮ ለመውጣት መገደዱን ይታወቃል፡፡ የተጫዋቹ ህመም በቂ የእረፍት ጊዜ የሚያስፈልገው በመሆኑም በቀጣዮቹ ሦስት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ክለቡን እንደማያገለግል ተሰምቷል፡፡
ሀዋሳ ከተማ በዚህ ሳምንት ወደ መቐለ አምርቶ ከስሑል ሽረ ጋር የአስራ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያከናውን ሲሆን የፊት መስመሩን ጥሩ ጥምረት እየፈጠሩ ባሉት ብሩክ በየነ እና ሄኖክ አየለ ላይ እንደሚመሰርት ይጠበቃል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ