በሲዳማ ቡና የህክምና ባለሙያ የሆነው አበባው በለጠ ባለፉት ሳምንታት በገጠመው ስብራት ምክንባት እጁ ታስሮ ሥራውን ሲያከናውን መታየቱ ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ሆኗል።
በአንድ ክለብ ለረጅም ጊዜ በህክምና ሙያ ውስጥ ከቆዩ ባለሙያዎች መካከል ይጠቀሳል፤ የሲዳማ ቡናው የህክምና ባለሙያ አበባው በለጠ። ከ1999 ጀምሮ ያለፉትን አስራ ሦስት ዓመታት በክለቡ ውስጥ የቆየ ሲሆን ከሦስት ሳምንታት ወዲህ በገጠመው ስብራት ምክንያት ራሱን ከማስታመም ይልቅ እጁን ታስሮ ከህመሙ ጋር እየታገለ ሥራውን በሚገባ እየከወነ ይገኛል፡፡ ማንኛውም ሰው የስብራት ህመም ሲገጥመው ረዘም ያለ የማገገሚያ ጊዜ የሚያስፈልገው የነበረ ቢሆንም አበባው ከባድ በሚባለው የእግር ኳስ ስፖርት ላይ እየተሯሯጠ ሲሰራ መታየቱ አስገራሚ ሆኗል።
በደረሰሰት አደጋ በአንገት ሥር የምትገኝ አጥንት ስብራት (Clavicle Fracture) የገጠመው አበባው ጉዳቱ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገውም የማያስፈልገውም ጊዜ ቢኖርም እርሱ ግን ህመሙን ችሎ ክለቡን ማገልገል መምረጡን ይናገራል። ተኝቶ ራሱን ከማስታመም ይልቅ ስራው ላይ ስላተኮረበት ምክንያትም ሲያስረዳም ” እንደ አባት ያሳደገኝ ክለብ ስለሆነ ተጎድቼም ቢሆን ባገለግል ጉዳቴን አላስታውስም። ቡድኑን ብቻ ነው የማስታውሰው። ክለቡን እያገለገግኩኝ ጉዳቴን እረሳለሁ። የሚያስተኛ ስብራት የገጠመኝ ቢሆንም ተሰብሬ ብሰራም ለለፋሁበት ክለብ ምንም አይደለም። የቡድኑን ውጤት እየሰራሁ በአይኔ አይቼ ነው የምረካው። ብተኛ የሚሰማኝ ስሜት አለ። ግን የክለቤን ውጤት ተኝቼ ከምሰማ በአይኔ ባየው ነው ደስ የሚለኝ። ሜዳም መጥቼ ስሰራ ጉዳቴን እረሳዋለሁ። ” ይላል።
አበባው እንደሚለው ጉዳቱ በአግባቡ ክትትል ከተደረገበት እስከ ስድስት ሳምንት ሊድን ይችላል፡፡ ቀዶ ጥገና ቢሰራ ኖሮ ደግሞ በአራት ሳምንት ውስጥ ሊስተካክል ይችል ነበር። ባለሙያው በስራ ላይ በሚሆንበት ወቅት ከሌሎች አጋሮቹ እገዛን እንደሚያገኝም ያናገራል። ” ለምሳሌ አሁን ከኢትዮጵያ ቡና ስንጫወት ይስሀቅ ሽፈራው እያገዘኝ ነበር፤ ሆሳዕና ላይም በተመሳሳይ። ወደ እኛ ቡድን ስመጣ ደግሞ የኛ ትጥቅ ያዥ አብሮኝ እያገዘኝ ነው ያለው፡፡ በዛውም እሱን ለማብቃት እየጣርኩ ነው ያለሁት፡፡”
የስብራት አደጋ ከሚፈጥረው ከባድ የህመም ስሜት እና በቶሎ ለማገገም ከሚያስፈልገው ዕረፍት አንፃር የአበባው በሥራው መቀጠል ትልቅ የአዕምሮ ጥንካሬን የሚጠይቅ ተግባር ነው። የባለሙያው የመጨረሻ አስተያየትም ይህንን ይጠቁማል። “ዕረፍት ላይ ብንሆን እና ጨዋታ ባይኖርብን ያስተኛኛል፤ እተኛለሁ። ግን አሁን አዕምሮዬ አያርፍም። ሥራ ላይ ሆኜ ህመሜንም እየረሳሁ ለቡድኔም ካለኝ ፍቅር ከቡድኑ ጋር የትም እየሄድኩኝ ነው። በተጎዳው ማግስት ከሆሳዕና ጋር ስንጫወት ሄጄ ሰርቻለሁ። ከዛ ጊዜ ጀምሮም አላረፍኩም ” ብሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ