የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የወሩ ምርጦች (ታኅሣሥ 24 – ጥር 21)

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተጀመረ ሁለት ወር ሞልቶታል። ባለፈው ወር ከኅዳር 21-ታኅሣሥ 20 በነበሩት ስምንት ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ ተንተርሰን ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ በአንድ ወር ውስጥ የተከናወኑ 6 ሳምንታት ጨዋታዎችን ተንተርሰን በዚህ መልኩ የወሩን ምርጦች አዘጋጅተናል። 

አጠቃላይ የወሩ መረጃ 

የጨዋታ ብዛት – 48

የተቆጠሩ ጎሎች ብዛት – 108

በአማካይ በጨዋታ – 2.25

የማስጠንቀቂያ (ቢጫ) ካርድ ብዛት – 185

የቀይ ካርድ ብዛት – 4

ከፍተኛ ነጥብ የሰበሰቡ ቡድኖች

1. ቅዱስ ጊዮርጊስ – 14

2. መቐለ 70 እንደርታ – 12

3. ስሑል ሽረ – 11

4. ፋሲል ከነማ – 11

ዝቅተኛ ነጥብ የሰበሰቡ ቡድኖች (የጎል ልዩነት ደረጃቸውን ለያይቶታል)

1. ወልዋሎ – 5

2. አዳማ ከተማ – 5

3. ጅማ አባ ጅፋር – 6

4. ሲዳማ ቡና – 6

5. ሀዲያ ሆሳዕና – 7

የጎሎች መረጃ

አጠቃላይ ጎል – 108

በጨዋታ የተቆጠሩ – 98

በፍ/ቅ/ም የተቆጠሩ – 10

በራስ ላይ የተቆጠሩ – 3

የመከኑ ፍ/ቅ/ምቶች – 3

ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ብዛት – 71

በርካታ ጎል ያስቆጠሩ ቡድኖች – ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና (11)

ከፍተኛ ጎል የተቆጠረበት ቡድን – ባህር ዳር ከተማ (12)

ዝቅተኛ ጎል ያስቆጠረ ቡድን – ወልቂጤ እና ጅማ አባ ጅፋር (4)

ዝቅተኛ ጎል የተቆጠረበት ቡድን – ስሑል ሽረ (2)

በጎል ማስቆጠር ረገድ ወጥ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም በዚህም ወር በስድስት ጨዋታዎች አምስት ጎሎች በማስቆጠር ቀዳሚው ስፍራ ላይ ተቀምጧል። 

አሲስት 

ለጎል አመቻችቶ በማቀበል በኩል አዲስ ግደይ እና ግርማ ዲሳሳ የወሩን ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግበዋል። በዚህ ወር በአጠቃላይ 57 ተጫዋቾች ለጎል በማመቻቸቱ ረገድ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ሁለት እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡትን በዚህ መልኩ ተመልክተናቸዋል።

የጎል ተሳትፎ 

ጎሎች በማስቆጠር አልያም በማመቻቸት ብዙ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው ተጫዋች አዲስ ግደይ ነው። የሲዳማ ቡናው አጥቂ በተለይ በዚህ ሳምንት በአራት ጎሎች ላይ መሳተፉ ቁጥሩን ከፍ እንዲል አድርጎታል። በአጠቃላይ በተሳትፎ ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡ የወሩ ምርጦች እነሆ!

ጎል ጠባቂዎች

ይህ ወር ካለፈው ጋር ሲነፃፀር በጎሎች ረገድ የተሻለ መጠን ቢመዘገብም ጎል ባለማስተናገድ የጎል ጠባቂዎች ሪከርድ ግን ካለፈው ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚህሕ የስሑል ሽረው ምንተስኖት አሎ በዚህ ወር በአራት ሳምንታት ጨተታዎች ላይ ተሳትፎ አድርጎ በአራቱም ሳይቆጠርበት ቀዳሚው ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አጠቃላይ ደረጃው ይህንን ይመስላል። 

የወሩ ምርጥ ተጫዋቾች

በዚህ ወር በተጫዋቾች በኩል ተቀራራቢ አቋም የታየ ሲሆን በተለይ ወጥ አቋም በማሳየት ረገድ የነበረው ክፍተት በወሩ የተሻለ አቋም ያሳየውን ለመምረጥ አስቸጋሪ አድርጎታል። ያም ሆኖ ሦስቱን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

ጋዲሳ መብራቴ 

በዚህ ወር በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች በንፅፅር ጥሩ አቋሙን በማሳየት ቅዱስ ጊዮርጊስ በደረጃ ሰንጠረዡ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ ረድቷል። ከመስመር እየተነሳ የሚፈጥራቸው የጎል እድሎች እንዲሁም የፊት መስመሩ የተጋጣሚን የኋላ መስመር ለማፈን በሚያደርገው ጥረት ላይ ተሳትፎ በማድረግ፤ በተጨማሪም በአንድ ጎል እና ሁለት አሲስት በወሩ ከሌሎች ተጫዋቾች የተሻለ ጊዜ አሳልፏል። በቅዱስ ጊዮርጊስ የቋሚ ተሰላፊነትን ለማግኘት በአስገራሚ የትጋት ደረጃ ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ ቦታው በሒደት የግሉ ለማድረግ በዚህ ወር ያሳየው ጥረት በሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ተጫዋች በሚል ለመመረጥ በቅቷል።

ሙጂብ ቃሲም 

ብዙም ሙገሳዎች የማይቸረው ሙጂብ ፋሲል ከነማ በዚህ ወር ሙሉ ለሙሉ የእሱ ጎሎች ጥገኛ ነበር ማለት ይቻላል። ቡድኑ ካስቆጠራቸው 7 ጎሎች አምስቱን ያስቆጠረው አጥቂው በተለይ በሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸው የማሸነፍያ ጎሎች ለቡድኑ አሁንም ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን ያስመሰከሩ ነበሩ። 

አብዱለጢፍ መሐመድ 

ታታሪው የመስመር ተጫዋች ስሑል ሽረ በወሩ ላሳየው ከፍተኛ መሻሻል ተመስጋኙ ተጫዋች ነው። በተለይ ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎችን ባሸነፈባቸው ጨዋታዎች ላይ ውጤታማነቱን ያሳየ ሲሆን አንድ ጎል ማስቆጠርም ችሏል። በግራ መስመር ሙሉ ኮሪደሩን ሸፍኖ የመጫወት አካላዊ ብርታት ባለቤት የሆነው ተጫዋቹ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በወሩ ረገድ ለቡድኑ ከፍተኛ አበርክቶ ነበረው።

የወሩ ውጤታማ አሰልጣኞች

በዚህ ወር አሰልጣኞቹ የሚመሯቸው ቡድኖች ውጤታማነትን፣ ካለፈው ወር አንፃር ያሳዩትን መሻሻል እና ተያያዥ መመዘኛዎችን በማስቀመጥ በዚህ መልኩ መርጠናል። 

ሳምሶን አየለ

የስሑል ሽረው አሰልጣኝ ቡድኑን ባለፈው ወር ከነበረበት የወራጅ ቀጠና ወደ ሰንጠረዡ አናት እንዲጠጋ በማድረግ መልካም ወር አሳልፈዋል። አንድ ጨዋታ ብቻ ሽንፈት ያስተናገዱት ሽረዎች ያላቸውን የስብስብ ጥልቀት እና የፋይናንስ ችግር ተቋቁመው ጥሩ ቡድን አድርገውታል። በአሉታዊ አቀራረቦች አለመሸነፍን ተቀዳሚ አላማው አድርጎ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይተች የነበረው ቡድን በዚህኛው ወር ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቡድን ሆኖ እንዲቀርብ በማስቻሉ ረገድ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

ገብረመድህን ኃይሌ 

መቐለ 70 እንደርታን በሊጉ ከዓምና ጀምሮ አንፃራዊ ወጥ ብቃት ያለው ቡድን እንዲሆን ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ምንም እንኳ ካለፈው ወር አንፃር ባያሻሽሉትም ወደ መሪነት እንዲሸጋገር ሚናቸው ከፍተኛ ነበር። በተጨማሪም በጥራትም ሆነ በጥልቀት ካለፈው ዓመት ዝቅ ያለውን ቡድን በውጤት ጎዳና ማስቀጠላቸው ሌላው የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። ቡድኖች ዋንጫ ባነሱ በአመቱ ክብራቸውን ለማስከበር በተጫዋቾች ዘንድ የተነሳሽነት ችግር የሚታይ ቢሆንም አሰልጣኙ ይህን እሳቤ እስካሁን ፉርሽ ማድረግ ችለዋል።

ሰርዳን ዝቪጅኖቭ 

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ በአቀራረባቸው እምብዛም ባይወደዱም በዚህ ወር ከፍተኛ ነጥብ የሰበሰበው የሚያሰለጥኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው።ለመከላከሉ የበዛ ትኩረት በመስጠቱ የሰሉ ትትቶችን ያስተናግድ የነበረው ቡድን ጨዋታዎችን ቢያሸንፍም አሁን ቢሆን በማጥቃቱ ረገድ የጠሩ የግብ ማግኚያ ዘዴዎች የሉትም በሚል ቡድኑ የሚገባውን ሙገሳ እየተቸረው አይገኝም።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ