ሀዲያ ሆሳዕና በወልቂጤ ከተማ 2-1 ከተሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በተፈጠረው ግርግር ለተጎዱ የወልቂጤ ቡድን አባላት እና ደጋፊዎች የመጀመርያ እርዳታ በመስጠት ሙያዊ ግዴታውን ከተወጣው የሀዲያ ሆሳዕናው የህክምና ባለሙያ ቢኒያም ተፈራ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።
በኢትዮጵያ መድን በግብ ጠባቂነት የእግር ኳስ ህይወቱን ጀምሮ በሰበታ ከተማ፣ መብራት ኃይል፣ ወልዲያ፣ ንግድ ባንክ፣ ኒያላ፣ ፊንጫ፣ ለገጣፎ እና መቐለ እንዲሁም በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጭምር አገልግሏል፤ የዛሬው የሀዲያ ሆሳዕና የህክምና ባለሙያ ቢኒያም ተፈራ። ከተጨዋችነት ዘመኑ ጎን ለጎን ከእናቱ በተማረው ሙያ የቡድን ጓደኞቹን ጉዳት ሲገጥማቸው በማሸት እርዳታ እየሰጣቸው ሙያውን ይበልጥ በማዳበር ከቆየ በኋላ በ2009 ለመቐለ እየተጫወተ በነበረበት ወቅት በወቅቱ የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ገብረፃዲቅ አጋዥነት በጥልቀት ወደ ሙያው ሊገባ ችሏል። በዚህም ዘንድሮ ሊጉን የተቀላቀለው ሀዲያ ሆሳዕናን በህክምና ባለሙያነት በማገልገል ላይ ይገኛል።
በ11ኛው ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና ወልቂጤ ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ መገባደጃ ላይ በነበረው ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ በሆነ ክስተት የእንግዳው ቡድን አባላት እና ደጋፊዎች ላይ በደረሰው ጉዳት ቢኒያም የህክምና እርዳታ በመስጠት ያከናወነው ተግባር ለብዙዎች ተምሳሌት የሚሆን ነበር። ” ሁሌም ሙያችንን ማክበር አለብን፤ ከዛ በላይ ደግሞ ሰብዓዊነት ሊሰማን ይገባል። በሰዓቱ ብዙ የተጉዱ ሰዎች ስለነበሩ እነሱን ልረዳ ነው የገባውት። አብዛኛው ጉዳቶች የነበሩት በአስለቃሽ ጭሱ ሳቢያ ነበር፤ ሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለእነሱንም ህክምና አድርግያለሁ። ” የሚለው ቢኒያም በወቅቱ ይህን ምስጉን ተግባር ስላከናወነበት ሁኔታ ሲያስረዳ “ሙያ እና ውጤት በጭራሽ አይገናኙም። በእኔ ዕምነት ከኳስም ሆነ ከሁሉም ነገር በፊት የሚቀድመው የሰው ልጅ መሆን ነው። እንደኔ ሀዲያ፣ ወልቂጤ፣ መቐለ… እያልኩ የመለየት ባህሪ የለኝም፤ ሙያውም አይፈቅድልኝም። እኔ ጋር ብዙ ተጫዋቾች ታክመው ይሄዳሉ። የኛ ሙያ ቀለም፣ ዘር እና ኃይማኖትን አይለይም። ሁሉንም ማኅበረሰብ በትክክለኛው መንገድ ማገልገል ግዴታ ነው። የተጎዳ ተጨዋቾችን ማከም ግዴታችን ነው። በቃ ውጤቱ ማሸነፍ፣ አቻ ወይም መሸነፍ ነው። ስለሆነም የተጎዳን የማንኛውንም ቡድን ተጫዎች በማከም ግዴታዬን እወጣለው። ” ይላል።
ከወልቂጤ ደጋፊዎችና የቡድን አባላት ስለነበረው ምላሽ በሰጠው አስተያየትም ” በወልቂጤ ቡድንም ሆነ ደጋፊ ምንም ስድብም ሆነ ነቀፋ አልደረሰብኝም። ከወልቂጤ ደጋፊ የፈለገውን ምላሽ ቢኖርም እኔን ግድ አይሰጠኝም፤ ማድረግ እየቻልኩኝ ማድረግ ባለመቻሌ የሚፀፅጥኝ የህሊና ቁስል ከምንም ጊዜ ይበልጣል።” ብሏል። በስተመጨረሻም ለሙያ አጋሮቹ ይህንን መልዕክት አስተላልፏል። ” ሁላችንም ሙያችንን እናክብረው። ስፖርተኛው የሚስፈልገውን አቅም አውጥቶ ሊጫወት የሚችለው የኛ ክትትል ሲኖረው ነው። ሁሌም ቅድሚያ መስጠት ያለብን ዕለታዊ ለሆነው ውጤት ሳይሆን ለተጨዋቾች እና ለስፖርት ቤተሰቡ ደህንነት ነው” ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ