ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ዋና አሰልጣኙን ካሰናበተ በኋላ መጠነኛ መነቃቃቶች የነበሩት ወላይታ ድቻ በሀዋሳ ከተማ ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ይገጥማል።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ

ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ እና በሜዳው ያሸነፈው ቡድኑ ከቀናት በፊት በሀዋሳ ከተማ ተረቶ ከነበረበት የፌሽታ ጊዜ (አሰልጣኝ ሲቀየር የሚኖር መነቃቃት) የተመለሰ መስሏል። እርግጥ በእንቅስቃሴ ደረጃ የከፋ ብቃት እያስመለከተ የማይገኘው ቡድኑ በተለይ ከአሰልጣኙ መቀየር በኋላ ቅርፁን እየያዘ መጥቷል። በተለይ በማጥቃቱ ረገድ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጋጣሚን ሲረብሽ ይታያል። ነገም በቸርነት ጉግሳ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና እዮብ ዓለማየሁ የሚመራው የቡድኑን የፊት መስመር የተጋባዦቹን የተከላካይ መስመር ሊፈትን ይችላል።

በሜዳው ባደረገው የመቐለ ጨዋታ ጥሩ ብቃት ያስመለከተው ቡድኑ የነበረበት የመልሶ ማጥቃት አከላከል ችግር ሲፈተነው ታይቷል። ምናልባት ነገም ድሬዳዋዎች በዚህ የጨዋታ አቀራረብ የሚቀርቡ ከሆነ ድቻዎች ሊፈተኑ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያሉበት የመዘናጋት ችግር ዋጋ እንዳያስከፍለው ያሰጋል። ነገር ግን ቡድኑ በሜዳው መቐለን ሲገጥም ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበ ወደ ሜዳ በመመለሱ ለኋላ መስመሩ ጥንካሬ ጥሩ የምስራች ነው።

ከአንድ ጨዋታ በፊት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ደጉ ደበበ፣ ረዘም ያለ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ይግረማቸው ተስፋዬ እና በሀዋሳው ጨዋታ መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ባዬ ገዛኸኝ ወደ ሜዳ በመመለሳቸው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

የድሬዳዋ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሜዳቸው እና ከሜዳቸው ውጪ የተለያዩ መልኮችን እያሳዩ የሚገኙት ድሬዳዋዎች ታህሳስ 25 ያገኙትን ጣፋጭ የሜዳቸው ውጪ ድል (ሲዳማ ቡናን 2-1 ያሸነፉበት) ለመድገም ሶዶ ይገኛሉ።

በአሰልጣኝ ስምዖን ዐመባይ የሚመራው ቡድኑ ሊጉ ሲጀምር የነበረበትን አስከፊ ጊዜ ረስቶ ወደ ጥሩ ጎዳና እየተጓዘ ይመስላል። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ረጃጅም ኳሶችን አዘውትሮ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር በመጣር የተጋጣሚን ተከላካይ ሲፈትን ይስተዋላል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በፍጥነት በማስጀመር ነጥቦችን ለመያዝ ይታትራል። ነገም ቡድኑ በተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ወደ ሜዳ በመግባት እንደሚጫወት ይገመታል።

በሊጉ ሁለተኛው ብዙ ግቦችን ያስተናገደ ክለብ (19) የሆነው ድሬዳዋ ከተማ ያለው የመከላከል አደረጃጀት የራስ ምታት ሆኖበት ቀጥሏል። እርግጥ በ11ኛ ሳምንት የሊጉ ቡድኑ መረቡን ሳያስደፍር ቢወጣም በጨዋታው ያለው የመከላከል አደረጃጀት ሙሉ ለሙሉ እንዳልተስተካከለ ታይቷል። ይህንን ተከትሎ ቡድኑ በነገው ጨዋታ የመከላከሉ አደረጃጀት ላይ ችግሮች ሊፈጠሩበት ይችላሉ።

ድሬዳዋዎች ያሬድ ታደሰን ከጉዳት መልስ በነገው ጨዋታ ሲያገኙ የግብ ጠባቂያቸው ሳምሶን አሰፋ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። በረከት ሳሙኤል፣ ረመዳን ናስር፣ ሳሙኤል ዘሪሁን እና ምንያህል ተሾመ አሁንም ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ተደርገዋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ8 ጊዜያት ተገናኝተዋል። በዚህም ድሬዳዋ አራት ጊዜ አሸንፎ በአራቱ አቻ ሲለያዩ እስካሁን ወላይታ ድቻ ድል ማስመዝገብ አልቻለም። ድሬ 8፤ ድቻ 3 ጎሎችንም አስቆጥረዋል። 

ግምታዊ አሰላለፍ 

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ 

ያሬድ ዳዊት – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – ውብሸት ዓለማየሁ

እድሪስ ሰዒድ – ተስፋዬ አለባቸው – በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – ባዬ ገዛኸኝ – እዮብ ዓለማየሁ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ሳምሶን አሰፋ

ፍሬዘር ካሣ – ያሬድ ዘውድነህ – ዘሪሁን አንሼቦ – ያሲን ጀማል

ፍሬድ ሙሸንዲ –  ዋለልኝ ገብሬ

ያሬድ ታደሰ – ኤልያስ ማሞ – ሙህዲን ሙሳ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ

©ሶከር ኢትዮጵያ