ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረገውን የአዳማ ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል። 

በፋይናንስ ችግር የቀድሞ ተፎካካሪነቱን ያጣ የሚመስለው አዳማ ከተማ ከአንድ ጨዋታ በፊት በሜዳው ያገኘውን ድል ለመድገም እና ከተደቀነበትን የወራጅ ቀጠና ስጋት በመውጣት ወደ ጥሩ ጎዳና ለመጓዝ ነገ ወደ ሜዳ ይገባል።

የአዳማ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ ተሸነፈ

ከጅማ አባ ጅፋር እኩል በሊጉ 6 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ቡድኑ (ሶስቱ 0-0 በሆነ ውጤት) ቀስ በቀስ የነበረበት የግብ አካባቢ ችግር እየለቀቀው የመጣ ይመስላል። በተለይ በመስመር ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን አዘውትሮ በመጠቀም የተጋጣሚን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ይጥራል።  በነገውም ጨዋታ ቡድኑ በበረከት ደስታ እና በቡልቻ ሹራ አማካኝነት የኢትዮጵያ ቡናን የግብ ክልል በተደጋጋሚ እንደሚጎበኝ ይታሰባል። 

ኢትዮጵያ ቡና ከሚከተለው ኳስን የመቆጣጠር አጨዋወት አንፃር አዳማዎች በነገው ጨዋታ በርከት ያሉ የመሐል ሜዳ ተጨዋቾችን ሊያስገቡ ይችላሉ። እርግጥ ቡድኑ ለዚህ አጨዋወት አዲስ ባይሆንም ነገ ሊፈጠርበት ከሚችለው የመሐል ሜዳ ብልጫ አንፃር አማራጩን ሊጠቀም ይችላል። ከዚህ ውጪ ዳዋን ጨምሮ ያሉት የወገብ በላይ ፈጣን ተጨዋቾች የኢትዮጵያ ቡናን የኳስ አጀማመር ሒደት በማደናቀፍ በጎ ነገሮችን ለቡድናቸው ለማምጣት ሊታትሩ ይችላሉ። በተጨማሪም አዳማዎች ካላቸው የአየር ላይ ጥንካሬ እና ኢትዮጵያ ቡናዎች ካላቸው የአየር ላይ ደካማ እንቅስቃሴ አንፃር የአየር ላይ ኳሶች ለአዳማዎች በጎ ነገሮችን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ።

ባለሜዳዎቹ ብሩክ ቃልቦሬ እና ከነዓን ማርክነህ ከጉዳት ሲመለሱላቸው ሚካኤል ጆርጅ አሁንም አላገገመም ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

13 ነጥቦችን በመያዝ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያ የሜዳቸው ውጪ ድል ለማግኘት አዳማ ገብተዋል። 

ወጣ ገባ አቋም በማሳየት ላይ  የሚገኘው ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ መጠነኛ መሻሻሎች ቢኖሩትም ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ማስመልከት ተስኖት ይገኛል። በተለይ ሊጉ ሲጀምር የነበሩበት አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ የመፍጠር ችግር አሁንም ተመልሶ የተጠናወተው ይመስላል። ከዚህ እና አዳማ ካለው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አንፃር በነገው ጨዋታ ቡድኑ ሊቸገር ይችላል።

ከኳስ ጋር ብዙ በመቆየት የሚታወቀው ኢትዮጵያ ቡና ነገም የጨዋታው የበላይ ሊሆን ይችላል (በኳስ ቁጥጥር)። ከኳስ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ መጠነኛ ለውጦችን በአማካይ መስመሩ ላይ ያደረገው ቡድኑ ነገም በተመሳሳይ አጨዋወት ሊቀርብ ይችላል። በዚህም ቡድኑ አማኑኤል ዮሐንስን ወደ ተከላካይ አማካይነት ቦታ በመውሰድ የኳስ ፍሰቱን ለማፍጠን  ይሞክራል ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ ውጪ በመሐል ለመሐል እንዲሁም በመስመር  ላይ ጥቃቶችን ለመሰንዘር በመጣር ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ይጥራል ተብሎ ይገመታል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ አቡበከር ናስርን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኙም። በቅጣት ላይ የነበረው አቤል ቅጣቱን በመጨረሱ ለጨዋታው ብቁ ነው ተብሏል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች 36 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 20 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ 7 ጊዜ አዳማ አሸንፏል። 9 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

– 95 ጎሎች በተስተናገዱበት የሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 63፤ አዳማ 32 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዳማ ከተማ (4-1-4-1)

ጃኮ ፔንዜ

ሱሌይማን ሰሚድ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ – ሱሌይማን መሐመድ

አዲስ ህንፃ

ፉአድ ፈረጃ – በረከት ደስታ – ከነዓን ማርክነህ – ቡልቻ ሹራ

ዳዋ ሆቴሳ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተ/ማርያም ሻንቆ 

አህመድ ረሺድ – ወንድሜነህ ደረጀ- ፈቱዲን ጀማል- እያሱ ታምሩ 

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሰ ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን- እንዳለ ደባልቄ – ሀብታሙ ታደሰ
©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ