ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ መቐለ 70 እንደርታ

ከአስራ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ጅማ አባ ጅፋር የሊጉን መሪ የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከተከታታይ ነጥቦች ማጣት በኋላ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ የገቡት ጅማ አባ ጅፋሮች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ከዚህ ጨዋታ ድል ይዘው መውጣት ይጠበቅባቸዋል።

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ጅማዎች በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከሜዳቸው ውጭ ከሚከተሉት ወደ መከላከል ያዘነበለ አቀራረብ ይልቅ በመጠኑ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያደርጋሉ። ቡድኑ ምንም እንኳ የተጠቀሰው አጨዋወትን መርጦ ቢጫወትም በአማካይ ክፍል ላይ ያለው የፈጣሪ አማካይ ችግር እና አጨዋወቱ በኤልያስ አሕመድ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ በርካታ የግብ ዕድሎች እንዳይፈጥር እክል ሆኖበታል።

በነገው ጨዋታ አጨዋወታቸው  ይቀይራሉ ተብለው የማይጠበቁት ጅማ አባጅፋሮች በተመሳሳይ የአማካይ ክፍል ላይ ክፍተቶች ያለውንን መቐለን መግጠማቸው ክፍተቶቹ እንደሚጠበቀው ላይጎሉ ይችሉ ይሆናል እንጂ ቡድኑ በአማካይ ክፍል ላይ ለውጦች ማድረግ ያስፈልገዋል።

ቡድኑ ዘግይቶ ወደ ቋሚነት በመምጣት ጥሩ በመንቀሳቀስ የሚገኘውን የአብርሀም ታምራት ግልጋሎት ማግኘቱ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በአማካይ ቦታ ላይ ተጫዋቾች ከተፈጥሯዊ ቦታቸው ውጭ ከማጫወት አድኗቸዋል።

ጅማዎች አምረላ ደልታታን በጉዳት ሲያጡ ብሩክ ገብረአብ እና ብዙዓየሁ እንደሻው ከጉዳት ተመልሰውላቸዋል።

የመቐለ 70 እንደርታ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ

ተቸግረውም ጨዋታዎች በማሸነፍ ጥሩ የአሸናፊነት ስነ ልቦናን በመገንባት ላይ የሚገኙት የሊጉ መሪ መቐለዎች በሰንጠረዡ አናት ለመቆየት እና ከተከታዮቻቸው ያላቸው ልዩነት ለማስፋት ከዚህ ወሳኝ የሜዳ ውጭ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት ብቸኛው ምርጫቸው ነው።

በቅጣት እና በጉዳት በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ያጡት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በተለይም አማካዩ ያሬድ ከበደን ማጣታቸው ትልቅ ራስ ምታት እንደሚፈጥርባቸው እሙን ነው። በአጨዋወቱ ላይ ወሳኝ ሚና ያለው ያሬድ ከበደን ጨምሮ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ሥዩም ተስፋዬ እና ኦኪኪ ኦፎላቢን ያጡት መቐለዎች በተለይም የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ለውጦች ለማድረግ ይገደዳሉ። በዚህም ባለፉት በርካታ ሳምንታት አጥቂዎቹን ዒላማ ባደረጉ ረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረገው ቡድኑ በነገው ዕለት ፈጣኖቹ የመስመር ተጫዋቾች ኤፍሬም አሻሞ፣ ያሬድ ብርሀኑ እና ሳሙኤል ሳሊሶን ወደ ተሰላፊነት የሚመልስ ከሆነ በመስመሮች ለማጥቃት አስቦ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ለአጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት አስቦ የሚገቡበት ዕድልም የሰፋ ነው።

መቐለዎች በነገው ዕለት ሚካኤል ደስታ ፣ ያሬድ ከበደ እና እንዳለ ከበደን በጉዳት አጥቂው ኦኪኪ ኦፎላቢን በቅጣት አያሰልፉም።

እርስ በርስ ግንኙነት

የመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ አሸናፊዎች የሆኑት ሁለቱ በድኖች በሊጉ አራት ጊዜ ተገናኝተው መቐለ 2 ሲያሸንፍ ጅማ አንድ አሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። መቐለ 5፤ ጅማ አራት ጎሎች አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

ስዒድ ሀብታሙ

ጀሚል ያቆብ – መላኩ ወልዴ – ከድር ኸይረዲን – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገብረሥላሴ – አብርሀም ታምራት

ሱራፌል ዐወል – ኤልያስ አሕመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ

ብዙዓየሁ እንደሻው

መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፊሊፕ ኦቮኖ 

አሸናፊ ሀፍቱ – ላውረንስ ኤድዋርድ – አሌክስ ተሰማ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ዳንኤል ደምሴ

ያሬድ ብርሀኑ – ዮናስ ገረመው – ኤፍሬም አሻሞ

አማኑኤል ገብረሚካኤል

© ሶከር ኢትዮጵያ