ናይጄሪያዊው ግዙፍ አጥቂ ፒተር ንዋድንኬ ከሰሞኑ ከሰበታ ከተማ ጋር ልምምድ እየሰራ እና የሙከራ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን እንቅስቃሴውም አመርቂ በመሆኑ የመጀመሪያ የሰበታ ፈራሚ እንደሚሆን ታውቋል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአጥቂ ስፍራ ላይ የአማራጭ እጥረት ካለባቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ሰበታ ከተማ በሁለተኛው ዙር የሚታይበትን ቀዳዳ ለመድፈን የቀድሞው የኤሌክትሪክ እና ንግድ ባንክ አጥቂ ላይ ትኩረት አድርጓል። በ2008 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በወቅቱ በዮርዳን ስቶይኮቭ በሚሰለጥነው ኤሌክትሪክ ከተጫወተ በኋላ በ2009 ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሄድ መጫወት ችሏል፡፡ በተለይ በኤሌክትሪክ ጥሩ ጊዜ አሳልፎ የነበረው አጥቂው በ2009 ክረምት ላይ ኢትዮጵያን ለቆ ወደ ሀገሩ ከሄደ በኋላ ዘንድሮ በመመለስ በፕሪምየር ሊጉ ለመጫወት ተቃርቧል፡፡
ከሰሞኑ ከሰበታ ከተማ ጋር ልምምድ እየሰራ የሚገኘው ተጫዋቹ በቡድኑ ውስጥ ለሳምንታት የሙከራ ዕድል ተሰቶት የሙከራ ጊዜውንም በአግባቡ መጠቀሙ የተገለፀ ሲሆን ከቀናት በፊት በተከፈተው የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የመጀመሪያው የሰበታ ከተማ ፈራሚ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በሁለተኛው ዙርም ሰበታን ማገልገል ይጀምራል ተብሏል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ለአንድ ዓመት ያህል ለክለቡ ለመጫወት በጥቅምት ወር አጋማሽ ፊርማውን አኑሮ የነበረው ዩጋንዳዊው የመሀል ተከላካይ ሳቪዮ ካቩጉ በገጠመው ጉዳት ለክለቡ በቂ ግልጋሎት እየሰጠ ስለማይገኝ በጋራ ስምምነት ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ