በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ በተከታዩ መልኩ ዳሰነዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሳምንቱ አጋማሽ መልካም ውጤት ያስመዘገቡበት የጨዋታ ሳምንትን አሳልፈው ነው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት። ጊዮርጊስ በሸገር ደርቢ የከተማ ተቀናቃኙ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና ደግሞ ከተከታታይ ውጤት ማጣቶች በኃላ በሜዳው ወልዋሎን 5-0 በሆነ ውጤት ከረመሩሙበት የጨዋታ ሳምንት በኋላ የሚደረገው ይህ ጨዋታ እጅግ ተጠባቂ ነው።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | አሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | አቻ |
በተወሰነ መልኩ የተቀራረበ የአጨዋወት መንገድ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በፈጣንና ታታሪ አጥቂዎቻቸው ተጋጣሚን ፋታ በማይሰጥ ጫና ውስጥ በመክተት ስህተት እንዲሰሩ ለማስገደድ ጥረት የሚያደርጉበት መንገድ በእጅጉ ያመሳስላቸዋል።
ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከረቡዑ ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጅኖቭ በድህረ ጨዋታ ቃለምልልሳቸው አጽንኦት ሲሰጡት እንደተደመጠው ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ሲያደርግ እንደነበረው ጫና ፈጥረው እንዲጫወቱ እንደሚሹ ተደምጠዋል። ይህም በዚህኛው ጨዋታ ላይ ዳግም ተግባራዊ ለማድረግ ይሞክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
ሲዳማ ቡናዎች በአንፃሩ ወልዋሎን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከአስፈሪው የይገዙ፣ አዲስና ሀብታሙ ጥምረት ባሻገር ከጀርባቸው የተሰለፉት የአጥቂ አማካዮቹ ዳዊት ተፈራና አበባየሁ ዮሐንስ በተለይ ፈጣኖቹን የመስመር አጥቂዎች ወደ ጨዋታ የሚያስገቡበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነበር። በዚህኛውም ጨዋታ ላይ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ከፈጣኖቹ አጥቂዎች በላይ እነዚህን ፈጣሪ አማካዮች ጊዜና ቦታ መንፈግ ካልቻሉ ጨዋታውን ሊያከብዱባቸው እንደሚችል ይገመታል።
በአንፃሩ ጥያቄዎች የሚነሱበት የሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር ጊዮርጊሶች በረቡዑ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ ሲያደርጉት እንደነበረው ከፍተኛ ጫናን በምን መልኩ ይቋቋሙታል የሚለው ነገር ሌላው ትኩረት የሚስብ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ከሳምንታት በፊት በአዲስአበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ እንደነበረው የተከላካይ መስመራቸውን ወደ መሀል ሜዳ የሚያስጠጉ ከሆነ ከጥልቀት በማጥቃት የተካኑ በሆኑት የጊዮርጊስ አጥቂዎች የመቀጣት እድላቸው የሰፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በጊዮርጊስ በኩል ናትናኤል ዘለቀ፣ለዓለም ብርሀኑ እና ሳላሀዲን ሰዒድ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን የአስቻለው ታመነ መግባትም አጠራጣሪ ነው። በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ መሳይ አያኖ፣ ሙሉቀን ታሪኩ፣ ሚሊዮን ሰለሞን፣ ወንድሜነህ ዓይናለም፣ አዲሱ አቱላ እና ሰንደይ ሙቱኩ በጉዳት ወደ አዲስ አበባ አላመሩም፡፡
እርስ በርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 20 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጊዜ በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ያለው ሲሆን ሲዳማ ቡና አንድ ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
– በግንኙነቶቹ ጊዮርጊስ 30 ሲያስቆጥር ሲዳማ ቡና 8 አስቆጥሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)
ፓትሪክ ማታሲ
ደስታ ደሙ- ምንተስኖት አዳነ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ሄኖክ አዱኛ
የአብስራ ተስፋዬ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ
ጋዲሳ መብራቴ – ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው
ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)
ፍቅሩ ወዴሳ
ዮናታን ፍሰሃ – ግርማ በቀለ – ሰንደይ ሙቱኩ – ተስፉ ኤልያስ
አበባየሁ ዮሐንስ – ዮሴፍ ዮሐንስ
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – አዲስ ግደይ
ይገዙ ቦጋለ
© ሶከር ኢትዮጵያ