የዓምና የሁለት ወር ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ሊከፈለን አልቻለም በሚል የአዳማ ከተማ ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾች የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተዋል።
ተከላካዩ ምኞት ደበበ፣ አማካዩ ከነዓን ማርከነህ እና አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ናቸው የመልቀቂያ ደብዳቤውን ለክለቡ ያስገቡት። ትናንት ማምሻውን እንዳስገቡ በታወቀው የመልቀቂያ ደብዳቤ “እዚህ ክለብ ውስጥ ብዙ ነገር ተጎድተን በዝምታ ያለፍነው ክለቡ ለእኛ ብዙ ነገር ስለሆነልን ነው። ሆኖም እግርኳስ መተዳደሪያችን በመሆኑ የዓምና የሁለት ወር ደሞዛችን እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ባለመፈፀሙ ምክንያት ለችግር ተዳርገናል። ስለሆነም ክለቡ የመልቀቂያ ደብዳቤያችንን ተመልክቶ በስምምነት ይሸኘን” ሲሉ ጠይቀዋል።
የክለቡ ፕሬዝደት አቶ ገመቹ በበኩላቸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ለተጫዋቾቹ ገልፀው ክለቡ ክፍያውን መፈፀም ካልቻለ እንደሚሸኛቸው እና ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ከአዳማ ከተማ ም/ከንቲባ ጋር በመነጋገር በቀጣይ ጊዜያት መልሱን እንደሚያሳውቋቸው ገልፀዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ