የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀመረ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ተጀምሯል። በሁለቱ ምድቦች የነበረውን የዛሬ ውሎ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል።

ምድብ ሀ

ሀዋሳ ከተማ 2-1 ኢ/ወ/ስ አካዳሚ

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ረፋድ 4:00 ላይ በተካሄደውና ሳቢ እና ያልተደራጁ የቅብብል ሒደቶችን ባየንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ወደ ግብ በመድረስ የተሻለ ቢሆንም የጎላ የአጨራረስ ክፍተት በቡድኑ ላይ ተንፀባርቋል፡፡ በብስለት ተደራጅተው መልሶ ማጥቃትን ተግባራዊ ለማድረግ ሲታትሩ የነበሩት አካዳሚዎች ኳስን ተቀባብለው ወደ ሀዋሳ ሳጥን ጥግ መድረስ ቢችሉም አብዛኛዎቹ የኳሶች ማረፊያ ግን ፍሬያማ አልነበረም። 11ኛው ደቂቃ ላይ በግራ አቅጣጫ ከተገኘ ቅጣት ምት ከድር አሊ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ የሀዋሳው ግብ ጠባቂ የያዛት ኳስ እንግዳው ቡድን ቀዳሚ ሙከራን ያደረገ ቡድን ሆኗል፡፡ ከአንድ ደቂቃ በኃላ የአካዳሚው የመሀል ተከላካይ ለሚ ሙላቱ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ በዛብህ ካቲሶ ቢመታትም ግብ ጠባቂው አቤኔዘር ፈይሳ አድኖበታል፡፡


ሀዋሳዎች ፍፁም ቅጣት ምቷት ከሳቱ በኃላ ወደ አካዳሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመጠጋት ባይገሩም ቢመስልም ፍፁም መረጋጋት የተሳናቸው መሆናቸውና እንደ ቡድን ሳይሆን ተጫዋቾቹ በግል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብቻ መገደቡ ያገኙትን ዕድል እንዳይጠቀሙ አግዷቸዋል፡፡ አካዳሚዎች በሙከራ ረገድ ብልጫ ቢወሰድባቸውም የሀዋሳን ደካማ የቅብብል ስህተት ተጠቅመው 33ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ኤልያስ እንደሻው የሀዋሳን ተከላካዮች ስህተት በሚገባ ከተመለከተ በኃላ በግራ የሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ የመታት ኳስ ከመረብ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ሀዋሳዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ ሁለት ጊዜ በቀላሉ ማስቆጠር የሚችሉበት ክፍት አጋጣሚ ቢያገኙም የአጨራረስ ድክመታቸው አቻ ከመሆን አግዷቸው ውሏል፡፡ 

በሁለተኛው አጋማሽም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ሁለቱም ቡድኖች የተመለከትን ሲሆን በማጥቃቱ ረገድም ደክመው ታይተዋል፡፡ ሆኖም 57ኛው ደቂቃ ላይ ሀይቆቹ ከማዕዘን ምት ከተገኘች ዕድል ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ከቢኒያም ካሳሁን የተሻማውን ኳስ በቀኝ መስመር በኩል ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው ሮቤል ግርማ እጅግ ማራኪ ግብ በማግባት ሀዋሳን 1ለ1 አቻ አድርጓቸዋል፡፡ 


ቡድኖቹ በወጣት የዕድሜ ዕርከን ላይ እንደመገኘታቸው በተመልካቹ ዘንድ ጥሩ የኳስ ፍሰትን ያስመለክተናል ብለን ብናስብም በስህተት ተገኝተው ከተቆጠሩ ግቦች ውጪ ዕይታ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አልተስዋለም፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃ ሲቀረው ለአካዳሚ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ኤልያስ እንደሻው በስተመጨረሻ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ማስቆጠር የሚችልባትን አጋጣሚ ቢያገኝም ካመከናት ሁለት ደቂቃ በኃላ ሀዋሳ ከተማዎች የማሸነፊያ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ ሶስት ደቂቃን ብቻ ማስቆጠር የቻለው ዳዊት ዮሐንስ ከሌላኛው ተቀይሮ የገባው አቤሴሎም ኤልያስ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር በመጨረሻ ደቂቃ ለሀዋሳ ከተማ ሶስት ነጥብ ማግኘት ምክንያት ሆኖ ጨዋታው 2ለ1 በሀዋሳ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


መከላከያ 1-2 ኢትዮጵያ ቡና

(በዳንኤል መስፍን)

ስድስት ኪሎ በሚገኘው መከላከያ ሜዳ በተካሄደው እና ጥሩ እግርኳስ በተመለከትንበት የመከላከያ እና የኢትዮጵያ ቡና  ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ኢትዮጵያ ቡና አሸናፊ ሆኗል። በመጀመርያው አጋማሽ መከላከያዎች ተሽለው በታዮበት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመቅረብ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም በኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ዳዊት ባህሩ ብቃት ከሽፎባቸዋል።

በዋናነት ከመስመር ወደ ሳጥን የገባው ስዮም ደስታ ወደ ጎል መቶት ግብጠባቂው ዳዊት ሲመልሰው ነፃ ኳስ አማኑኤል አባዲ አግኝቶ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ያመከነው፣ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የመከላከያው አጥቂ ድልአዲስ ገብሬ ወደ ጎል መቶት በግብጠባቂው ዳዊት የተመለሰባቸው ኳሶች ለመከላከያ በመጀመርያው አጋማሽ ጎል መሆን የሚችሉ ዕድሎች ነበሩ።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል መሐል ሜዳ ላይ በሚደረጉ ቅብብሎች ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ ውጭ የጎላ የጎል ሙከራ ያደረጉት በየነ ባንጃ አክርሮ የመታው እና በግቡ አናት ለጥቂት የወጣበ ብቸኛው ሙከራ ሆኖ አልፏል። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለኢትዮጵያ ቡና ሲጫወት የተመለከትነው ተስፈኛው ወጣት ያብቃል ፈረጃ እና አማካይ ሙሴ ከበላ በግላቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር ሲያስመለክተን ከመሐል ሜዳ በተጣለለትን ኳስ ሾልኮ የገባው አብዱልከሪም መሐመድ በግብጠባቂው ስጦታው አናት ላይ አሳልፎ ያስቆጠራት ጎል የኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ አድርጋለች። 

ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን በማደግ አቅማቸውን እያሳዩ የሚገኙት መሐመድ አበራ እና ተፈራ አንለይ ተቀይረው ከገቡ በኃላ የመከላከያን የማጥቃት ሚዛንን ከፍ አድገውት ጫና የፈጠሩት መከላከያዎች 70ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታ የተመለሱበት ጎል በዋናው ቡድን ጎል እያስቆጠረ የሚገኘው መሐመድ አበራ ቡድኑን አቻ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። 

ኃይል የተቀላቀለበት እግርኳሳዊ ውጥረት አይሎበት በቀጠለው ጨዋታ ተጭማሪ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የአስኮ ፕሮጀክት ፍሬ የሆነው ተገኝ ዘውዴ የማዕዘን ምት መምቻ ላይ የመከላከያ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት ያገኘውን ኳስ በሚገርም ሁኔታ ብስለት ባሳየ መልኩ ሁለት ተከላካዮችን በማለፍ ተረጋግቶ ኢትዮጵያ ቡናን አሸናፊ ያደረገች ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ይህች ጎል በሜዳ ለነበሩት ተመልካቾችም ሆነ ለኢትዮጵያ ቡና የቡድን አባላት አስደሳች ስትሆን ለመከላከያ ተጫዋቾችን ግን አንገት አስደፍታለች። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።


ወላይታ ድቻ 2-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

(በተስፋሁን ዮሴፍ)

በወላይታ ሶዶ ሌሊቱን ሲዘንብ ያደረውን ዝናብ ይዞ ባደረው የሶዶ ስታድየም ላይ በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል የተመጣጠነ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን እንግዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ኳስን ይዞ ለመጫወት ሲያደርግ የነበረው ጥረት ሜዳው ላይ በተኛው ውሃ ምክንያት ፈታኝ ሆኖበት ተስተውሏል። በዚህም እምብዛም የጎል ሙከራ ሳይታይበት ወደ እረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ ሒደት እስከ ጨዋታው የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች የዘለቀ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ሦስት ተጫዋቾችን በተከታታይ ቀይረው ካስገቡ በኋላ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ጨዋታውን አሸንፈው የሚወጡባቸው ጎሎች አግኝተዋል። በዚህም በ79ኛው ደቂቃ በአማካዩ አበባየሁ አጪሶ አማካኝነት የመጀመርያውን ጎል ሲያስቆጥሩ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ በገባው ተመስገን ብርሃኑ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥረዋል።

በዚህ ምድብ በተደረገ ሌላ ጨዋታ አሰላ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ድሬዳዋ ከተማን በዳንኤል አብርሀም ጎል 1-0 ማሸነፍ ሲችል አሰላ ኅብረት የዚህ ሳምንት አራፊ ቡድን ነው። 

ምድብ ለ


ፋሲል ከነማ 2-2 አዲስ አበባ ከተማ 

(በኤልያስ ኢብራሂም)

ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ነበሩ። 11ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ኢብራሂም ሠንብታ ወደግብ ቀይሮት መምራት የቻሉት እንግዳዎቹ መሪነታቸው የዘለቀው ለጥቂት ደቂቃዎች ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ማሩ ከቀኝ መስመር ወደግብ ያሻማው ኳስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ግብ ተቀይሮ ፋሲል ከነማዎች አቻ መሆን ችለዋል።
በእንግዳዎቹ በኩል በሙከራ ደረጃ 20ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ዘካሪያስ ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ የመለሰበት የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። 35ኛው ደቂቃ ላይ ኢብራሂም ሰንበታ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበትም የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ላይ በማጥቃቱ በኩል አስፈሪ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተስተዋሉት አዲስ አበባ ከተማዎች በመስመር ላይ የሚጫዎቱ ታዳጊዎች ትስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ጨዋታው ላይ ወደፊት በመድረስ አዲስ አበባ ከተማዎች የተሻለ እንቅሰቃሴ ቢያደርጉም ባለሜዳዎቹ ከመመራት ተነስተው ወደ መምራት የተመለሱበትን አጋጣሚ 50ኛው ደቂቃ ፈጥረዋል። በቀኝ መስመር ናትናኤል ማስረሻ ወደ ሳጥን ይዞት የተጠጋውን ኳስ ለዣቬር ሙሉ አሻግሮለት ዣቬር ወደ ግብ ቀይሮ ፋሲል ከነማን መሪ ማድረግ ችሏል። 61ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ማሩ ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ደጀን ገበየሁ ወደ ግብ ለመቀየር ጥረት ቢያደርግም በታከላካዮች ተጨራርፎ የወጣው ኳስም መሪነታቸውን ሊያሰፉበት የሚችል አጋጣሚ ነበር።

በእንግዳዎቹ በኩል 52ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት ዘካሪያስ በመስመር ይዞት የገባውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ተጠግቶ የወጣበት ሲጠቀስ 68ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን የቻሉበትን ጎል አስቆጥረዋል። ሙከሪም ምራብ ያሻማውን ኳስ ዓባይ ኩዊት በጭንቅላት በመግጨት ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።

በምድቡ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ወደ ወልቂጤ ያመራው ሀላባ ከተማ ፀጋው ከድር እና ጀሚል ታምሬ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 ሲያሸንፍ አዳማ ላይ ኢትዮጵያ መድን በመሐመድ ኑረዲን ሁለት ጎሎች 2-1 አሸንፏል። ቢንያም አይተን የባለሜዳዎቹ ብቸኛ ጎል ባለቤት ነው። 

የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሱሉልታ ከተማ ጨዋታ ወደ ነገ ሲሸጋገር አሰላ ኅብረት የዚል ሳምንት አራፊ ቡድን ነው። 

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ