ሴቶች 2ኛ ዲቪዝዮን | ሻሸመኔ ወደ መሪነቱ ሲመለስ ፋሲል ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲቀጥል ሻሸመኔ ከተማ፣ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ እና ፋሲል ከነማ አሸንፈዋል።

ጎንደር ፋሲለደስ ስታድየም ልደታ ክፍለ ከተማን ያስተናገዱት ፋሲል ከነማዎች 3 – 0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ምንትዋቦቹ ግብ ለማስቆጠርም ብዙ ደቂቃዎች አልጠበቁም። 10ኛው ደቂቃ ረደኤት ዳንኤል ሳጥን ውስጥ ያገኘችውን ኳስ ወደ ግብ አክርራ በመምታት ግብ አስቆጥራ ፋሲል ከነማን መሪ ማድረግ ችላለች።

23ኛው ደቂቃ ላይ የልደታዋ ግብ ጠባቂ ሔለን ሙሉጌታ ከሳጥን ውጭ ኳስ በእጅ በመያዟ ግብ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበት ሲሆን ይህም ልደታዎች ኳስ ከመቆጣጠር ውጪ በጨዋታው ተፅእኖ እንዳይፈጥሩ አግዷቸዋል።

ፋሲሎች በመጀመርያው አጋማሽ መሪነታቸውን ሊያሰፉባቸው የሚችሏቸው እድሎችን የፈጠሩ ሲሆን በተለይም 35ኛ ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ ቤተልሔም ሽመልስ ለቤተልሔም አምሳሉ ያሻገረችውን ኳስ ቤተልሄም ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ያመከነችው ይጠቀሳል። የመጀመርያው አጋማሽ የተጠናቀቀውም ቅድስት ገነነ የግብጠባቂዋን መውጣት ተከትሎ ወደግብ በመምታት ግብ አስቆጥራ ፋሲል 2-0 በመምራት ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ልደታ ክፍለ ከተማዎች ከመጀመርያው ተሻሽለው በመግባት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በ64ኛው ደቂቃ እየሩስ ወንድሙ ወደ ግብ አክርራ የመታችው ኳስ ግብጠባቂዋ ስታድንባት 82ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ ትእግስት ሽኩር ወደ ግብ አክርራ የመታችው ግብ ጠባቂ በቀላሉ ያዳነበት እንዲሁም 86ኛ ደቂቃ ላይ እየሩስ ወንድሙ ከሳጥን ውጭ ወደ ግብ አክርራ የመታችው ኢላማውን ያልጠበቀው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። 

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ለመንቀሳቀስ በሞከሩት ምንትዋቦቹ በኩልም 80ኛው ደቂቃ ላይ ከቤተልሄም አምሳሉ በግራ መስመር ያተሻማ ኳስ ቅድስት ዳኛቸው  በጭንቅላት ገጭታ የግቡ ቋሚ የመለሰባት ኳስ የሚጠቀስ ጥሩ ሙከራ ነበር። ጃኖ ለባሾቹ 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው እሸት የሻምበል ያሻማችውን ኳስ ቤተልሄም አምሳሉ ወደ ግብ ቀይራው መሪነታቸውን ወደ ሶስት አድርሰው ጨዋታውንም 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል ።
ሻሸመኔ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲን ያስተናገደው ሻሸመኔ ከተማ 3-2 በማሸነፍ መሪነቱን በድጋሚ ከቦሌ ተረክቧል። የሻሸመኔን የድል ጎሎች ያስቆጠሩት ዘቢባ ሀሺም፣ ወለላ ባልቻ እና ዓለሚቱ ድሪባ ናቸው።

አሰላ ላይ ባህር ዳር ከተማን ያስተናገዱት ጥሩነሽ ዲባባዎች በጤናዬ ለታሞ እና ሪታ ግደይ ጎሎች 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ