በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው አዳማ ከተማ አስደናቂ ፍጥነት በታከለባቸው ሽግግሮቹ ኢትዮጵያ ቡናን 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
በባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በኩል ባሳለፍነው ሳምንት በመጨረሻ ደቂቃ በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፈው ቡድን የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ግብጠባቂው ደረጀ ዓለሙ ፣ ተከላካዩ ምኞት ደበበ እና አማካዩ ከነዓን ማርክነህ በዛሬው ጨዋታ ዳግም ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት መመለስ ሲችሉ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በሸገር ደርቢ ሽንፈት ካስተናገደው ቡድን ግብጠባቂ ስፍራ ላይ ብቻ ቅያሬ በማድረግ በረከት አማረን በተሰላፊነት በመጠቀም ወደ ጨዋታው ገብተዋል።
በጨዋታው ላይ የአዳማ ከተማ ሴቶች ቡድን ተጫዋቾች በቅርቡ ጉልበቷ ላይ በደረሰባት ጉዳት ላለፉት ሦስት ወራት ከእግርኳስ ለራቀችው የጌዴኦ ዲላዋ ወጣት አጥቂ ቤዛዊት ታደሰ የቀዶ ጥገና ህክምና የሚውል ገንዘብን በስታዲየሙ ከታደሙት ተመልካቾች በመዘዋወር ማሰባሰብ ችለዋል።
በበርካታ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ የሰነበቱት አዳማ ከተማ ፍፁም የበላይ በነበረበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ አዳማ ከተማዎች የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን ኳስ እንዳይመሰርቱ ከፍተኛ ጫና ውስጥ በመክተት እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ፈጠን ያሉ ሽግግሮች ለኢትዮጵያ ቡናዎች ጨዋታውን እጅግ ከባድ አድርገውባቸው ተስተውሏል።
ገና ከማለዳው በሜዳው የላይኛው ክፍል የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን ማፈን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በ5ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ የኢትዮጵያ ቡናውን ግብ ጠባቂ ጫና ውስጥ በመክተት ያደረገውን የተሳሳተ የኳስ ማቀበል ሂደት ተጠቅሞ መልሰው ያገኙትን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ከነአን ማርክነህ ከሳጥን ውጭ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በረከት አማረ እንደምንም በያዘበት ሙከራ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በ11ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን በማፈን በተገኘው አጋጣሚ አዳማዎች ከግራ መስመር የነጠቁትንና ያሻሙትን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በእግሩ ደግፍ አድርጎ በማስቆጠር ገና ቡድኑን በማለዳ መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በደቂቃዎች ልዩነት በተመሳሳይ መልኩ ከቀኝ መስቀር ነጥቀው ወደ መሐል ያሻሙትን ኳስ ቡልቻ ሹራ በግንባሩ ቢገጭም ወደ ውጭ ወጥቶበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ እንደ ወትሮው ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳስን ይዘው ለመውጣት የተቸገሩት ቡናዎች በ18ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ከቅጣት ምት የመታውና ደረጀ አለሙ ካዳነበት ኳስ ውጭ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚን የሜዳ አጋማሽ ለመድረስ ተቸግረው ተስተውሏል።
ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት አዳማዎች በ21ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ አክርሮ የመታውና በረከት አማረ እንደምንም ባዳነበት ኳስ የቀጠለው ጥረታቸው በ23ኛው ደቂቃ ዳግም ፍሬ አፍርቷል። አዳማዎች ከመሐል የነጠቁትን ኳስ ወደ መስመር በተለጠጠ አቋቋም ላይ በነፃ አቋቋም ለነበረው ከነዓን ማርክነህ ያቀበሉትን ኳስ ተጠቅሞ ከመስመር ወደ መሀል ሰብሮ በመግባት የቡድኑን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
አሁንም በደቂቃዎች ልዩነት ከቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውና ለጥቂት በግቡ ቋሚ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። በመጀመሪያው አጋማሽ ልዩ የነበሩት አዳማዎች በ30ኛው ደቂቃ ከማዕዘን በአጭሩ የጀመሩትን ኳስ ቡልቻ ሹራ ተቀብሎ በቀጥታ ከጠበበ አንግል ወደ ግብ የላከውን ኳስ በረከት አማረ ሊያድንበት ችሏል።
በጨዋታው እጅግ ቀዝቃዛ አጀማመር የነበራቸው ቡናዎች በንፅፅር በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረዋል። በዚህም በምክንያትነት የሚቀርበው አዳማዎች ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ ጫና ይፈጥሩበት የነበረው እንቅስቃሴ በሂደት እየተዳከመ መምጣት ዋነኛ ምክንያት ነበር ። በዚህም ሂደት በ33ኛው ደቂቃ ከማእዘን በአጭሩ የተጀመረውን ኳስ ሚኪያስ መኮንን ከጎል ትይዩ ተጫዋቾችን አልፎ ያቀበለውን ኳስ ፈቱዲን ጀማል ወደ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ጨዋታው መመለስ የምትችል እጅግ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።
በመጀመሪያው አጋማሽ ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች እየታመሱ የሚገኙ የማይመስሉት አዳማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃ ላይ በፈጣን ሽግግር የተገኘችውን ኳስ ከቡልቻ ሹራ የተቀበለውን ኳስ ፉአድ ፈረጃ በረከት አማረን አንጠልጥሎ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሰምር በቀረች ሙከራ ነበር የመጀመሪያ አጋማሽ የተጠናቀቀው።
በሁለተኛው አጋማሽ በመጀመሪያው አጋማሽ በከፍተኛ ብርታት ይጫወቱ የነበሩት አዳማዎች በሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆን ወደ ራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ተሰብስበው በመከላከልና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ምስረታ ወቅት ይደርስባቸው የነበረው አፈና በመጠኑም ቢሆን ጋብ ያለላቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ አደጋ በማይፈጥሩ የሜዳው ክፍሎች ላይ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።
ምንም እንኳን ወደ ኋላ ሰብሰብ ቢሉም ከወገብ በላይ በሚገኙ የተጫዋቾች አስደናቂ ፍጥነት በመታገዝ አዳማዎች ወደ ማጥቃት የሚያደርጉት ሽግግሮች እጅግ አስፈሪ ነበሩ። በ62ኛ 65ኛው ደቂቃም የማጥቃት ሽግግሮችን በማድረግ ወደ ቡና የግብ ክልል ከቁጥር ብልጫ ጋር መድረስ የቻሉት አዳማዎች በሁለቱም አጋጣሚዎች በረከት ደስታና ዳዋ ሆቲሳ በደካማ የውሳኔ አሰጣጣቸው ኳሶቹን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ኢትዮጵያ ቡናን ሲፈተሽ የዋሉት አዳማዎች ዳዋና ቡልቻ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ የመቱዋቸውን ሁለት ግሩም ሙከራዎች በረከት አማረ ሊያድንባቸው ችሏል።
በ68ኛው ደቂቃ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በሁለተኛ አጋማሽ በተመለከተው የቀጥታ ቀይ ካርድ ያለፉትን ጨዋታዎች ቡድኑን ማገልገል ያልቻለው የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ አቤል ከበደ በጨዋታው አንዳች ነገር መፈየድ የተሳነው ሀብታሙ ታደሰን ቀይሮ በመግባት ዳግም ለቡድኑ ግልጋሎት ሰጥቷል። አቤል ተቀይሮ ከገባ በኃላ በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ከመስመር እየተነሳ አደጋ ለመፍጠር በግሉ ጥረት አድርጓል።
በ74ኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተበታተነውን የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ መስመር ያገኙት አዳማዎች በረከት ደስታ ከግራ የሳጥን ጠርዝ ወደ በተሻለ አቋቋም ላይ ይገኝ ለነበረው ሱሌይማን አቀብሎት በቀላሉ ያስቆጠራት ግብ አዳማዎችን ለጣፋጭ ድል ያበቃች ሆና ተመዝግባለች።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ የገጠመው የኃላሸት ፍቃዱ ከበረከት አማረ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ የአዳማን መሪነት ከፍ ማድረግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች።
ጨዋታው በአዳማ ከተማ 3-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ አዳማ ወደ ድል አድራጊነት ሲመልስ ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ሁለተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በሰሞነኛ የቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልሆኑ የተወሰኑ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን አሰምቷል።
©ሶከር ኢትዮጵያ