የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ 2-0 ባህርዳር ከተማ

በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልቂጤ ከ ባህር ዳር ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

” ቡድናችን በአሸናፊነቱ በመቀጠሉ እጅግ ደስተኛ ነኝ ” ደግአረግ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልተቻለም ነበር። ነገር ግን ከእረፍት መልስ ውጤቱን ይዞ ለመውጣት የተጫዋች ቅያሪ አድርገናል። በተቻለን መጠን ተጭነን ለመጫወትም ሞክረናል። በዚህም ውጤታማ ነበርን። ቡድናችን በአሸናፊነቱ በመቀጠሉ እጅግ ደስተኛ ነኝ።

ስለተከታታይ ድል ሚስጥር

የዚህ ሚስጥሩ ዋናውን ድርሻ የሚወስደው ጨዋው ቡድኑ ወዳጅ ደጋፊ ነው፤ በጣም አመሰግናለሁ። ይህ ደጋፊ በእውነት ሊመስገን ይገባል። ውጤት ስናጣም ስናመጣም ከጎናችን ነበር ከዚ በተጨማሪ እንግዳውን ቡድን ተቀብለው የሚሸኙበት መንገድ እጅግ ማራኪ ነው። እጅግ እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል። ሌላው ልጆቻችን እስካሁን በተጫወቱበት ጨዋታ ለማሸነፍ የነበራቸው ጉግት በጣም ከፍተኛ ነው። በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጪ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው። ምስጢሩ ልጆቻችን ከጨዋታ ጨዋታ ለማሸነፍ የሚደርጉት ጥረት ነው።

“እኔ በግሌ ሰበብ ማቅረብ አልወድም” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታው በሁለታችንም በኩል ረጃጅም ኳስ የበዛበት ነበር። እነሱ የግብ እድል አገኙ አጋጣሚዎቹንም ተጠቀሙ። ሜዳው ላይ የነበረው እንቅስቅሴ ግን አንድ አይነት ነበር። እነሱ ግቡን ካስቆጠሩ በኋላ ከፍተኛ መነሳሳት ነበራቸው። ከዛ በፊት የነበረው እንቅስቃሴ ግን አንድ አይነት ነበር። በአጠቃላይ ወልቂጤዎች እንኳን ደስ ያላቹ ነው የምለው።

ሁለቱንም አጥቂዎቹን በጉዳት ስለማጣቱ

እኔ በዛሬው ጨዋታ ከቋሚ 11 ተሰላፊዋቼ ሰባት ተጫዋች ተጓድቶብኛል። ነገር ግን በግሌ ሰበብ ማቅረብ አልወድም። ሁሉም ተጫዋች ለመጫወት እስከመጣ ድረስ መጫወት አለበት፤ እንዲህ አይነት ነገር ያጋጥማል። ወደዚህ የመጣነው ነጥብ ለማግኘት እንጂ ተጫዋቾቼ ተጎድተዋል ብዬ ሰበብ ለመደርደር አይደለም። በእግር ኳስ እንዲህ አይነት ያጋጥማሀል።

©ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ